ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝደንት ትራምፕ ወደ ፌስቡክ በቅርቡ ይመለሱ ይሆን?
ፌስቡክ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ መድረኩ እንደሚለሱ ውሳኔ ለመስጠት የሰጠውን ቀጠሮ አራዝሟል።
ኩባንያው የቀድሞው አወዛጋቢ ፕሬዝደንት ወደ ፌስቡክና ኢንስታግራም ማሕበራዊ ድር አምባዎች እንዲመለሱ አሊያም በዚያው ቀልጠው እንዲቀሩ ውሳኔ ማሳለፍ ነበረበት።
ትራምፕ ከፌሰቡክ የተባረሩት ባለፈው ጥር የአሜሪካው ካፒቶል ፊል በአመፀኞች ከተወረረ በኋላ ነበር።
ውሳኔ ሰጪው የፌስቡክ ኦቨርሳይት ቦርድ ውሳኔው ያዘገየው 9 ሺህ ያክል በጉዳዩ ላይ ሐሳብ የሰጡ ሰዎችን አስተያየት እየመረመረ በመሆኑ ነው።
ቦርዱ ትዊተር ላይ በለቀቀው መልዕክት ውሳኔው በሚቀጥሉት ሳምንታት ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ቦርዱ መሰል ጉዳዮችን ማየት የጀመረው ባለፈው ዓመት ነው።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፌስቡክና ኢንስታግራም ይመለሱ የሚለው ውሳኔ ቦርዱ ከተመሠረተ ወዲህ የሚሰጠው ትልቁ ፍርድ ይሆናል።
20 አባላት ያሉት ኮሚቴ የተዋቀረው በፌስቡኩ አለቃ ማርክ ዛከርበርግ ሲሆን የፌስቡክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚል ቅጥያም ተሰጥቷል።
ምንም እንኳ ቦርዱ በራሱ የሚንቀሳቀስ ቢሆንም ደመወዝን ጨምሮ አበልና መሰል ወጪዎችን የሚሸፍነው ፌስቡክ ነው።
ኮሚቴው ጋዜጠኞች፣ ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች፣ የሕግ ሰዎችና ምሁራን የተሰባሰቡበት ነው።
ቦርዱ እስካሁን ዘጠኝ ያክል ጉዳዮችን መርምሮ ውሳኔ አሳልፏል።
ከነዚህ መካከል ሚዬንማር ውስጥ አንድ የፌስቡክ ልጥፍ ላይ ሙስሊሞችን ያንቋሸሸ ነው የተባለ መልዕክትን መርምሮ መልዕክቱ እስላም ጠል አይደለም ሲል በይኗል።
ፌስቡክ ከመድረኩ ያገደው ዶናልድ ጄ ትራምፕን ብቻ አይደለም።
በያዝነው ወር መባቻ ላይ የትራምፕ ልጅ ሚስት የሆነችው የፎክስ ኒውስ ባልደረባ የሆነችው ሎውራ ትራምፕ ፕሬዝደንቱን ስታነጋግር የሚያሳይ ምስል መለጠፏን ተከትሎ እግድ ተላልፏል።
ትራምፕን ከመድረካቸው ያገዱት ፌስቡክና ኢንስታግራም ብቻ አይደሉም።
ከካፒቶል ሂል አመፅ በኋላ ትራምፕ ዋና ዋና ከሚባሉ ማሕበራዊ ድር አምባዎች የታገዱ ቢሆንም ዩትዩብ የተሰኝ ድር እግዱን ሊያነሳ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።
ትዊተር የተባለው ድር አምባ ግን ትራምፕን እስከ ወዲያኛው እንዳገዳቸው አስታውቋል።
ክራውድታንግል የተሰኘው መረጃ ሰብሳቢ ድርጅት እንደሚለው የትራምፕ የፌስቡክ መልዕክቶች እጅግ በጣም ብዙ ሰው ከሚመለከታቸው መካከል ነበሩ።
ትራምፕ የራሳቸውን ማሕበራዊ ድር አምባ ለመፍጠር እንዳሰቡ ተናግረው ነበር።