ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፑቲን ዋነኛ ተቃዋሚ በሞትና በህይወት መካከል መሆኑን ዶክተሮቹ ተናገሩ
በሰላ ትችቱ የሚታወቀውና በእስር ላይ የሚገኘው ሩሲያው ተቃዋሚ አሌክሴ ናቫልኒ ህክምና ካላገኘ በቀናት ውስጥ ሊሞት እንደሚችል ዶክተሮቹ አስታውቀዋል።
ዶክተሮቹ እንደሚሉት በቅርብ ባደረጉት የደም ምርመራዎች የልብ ድካም ወይም የኩላሊቱ ከጥቅም ውጭ መሆን ሊያጋጥመው እንደሚችል ጠቁሟል።
ለባለፉት 18 ቀናት በረሃብ አድማ ላይ የሚገኘው አሌክሴ ክፉኛ የሆነ የጀርባ ህመምና የእግር መደንዘዝም አጋጥሞታል ተብሏል።
ለነዚህ ህመሞቹ ተገቢው ህክምና ሊሰጠኝ ይገባል በሚል ነው የረሃብ አድማውን እያደረገ ያለው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በነዚህ ቀናት 9 ኪሎ እንደቀነሰና የአሁኑ ኪሎውም 76 እንደገባ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ባለቤቱን ዩሊያን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ክፉኛ በመተቸት የሚታወቀው አሌክሴ ከገንዘብ ምዝበራ ጋር በተያያዘ ነው የካቲት ላይ ለእስር የተዳረገው።
የግል ዶክተሩ አናስታዢያ ቫሲልየቫን ጨምሮ አራት ዶክተሮች ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አሌክሴን ባስቸኳይ እንዲያዩት ፍቃድ እንዲሰጣቸው በደብዳቤ ጠይቀዋል።
ዶክተር አናስታዢያ በትዊተር ላይ ባጋሩት ደብዳቤ ላይ ዶክተሮቹ አሌክሴ በሰውነቱ ላይ ያለው ፖታሺየም የተሰኘው ንጥረ ነገር አስጊ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን ነው
"ይሄ ማለት ኩላሊቱ ከጥቅም ውጭ ሊሆን እንደሚችልና የልብ ድካም ችግር በየትኛዋም ደቂቃ ሊያጋጥመው እንደሚችል አሳይ ነው" ይላሉ።
በደም ውስጥ ያለው የፖታሺየም መጠን ከ6 በላይ ከሆነ አስቸኳይ ህክምና ያስፈልጋል። ጠበቆቹ ያገኙት የአሌክሴ የደም ምርመራ እንደሚያሳየው የፖታሺየም መጠኑ ወደ 7.1 ከፍ ማለቱን ነው።
ዶክተሮቹ የማረሚያ ቤት አስተዳደሩን እንደጠየቁት አሁን ካለው የደም ምርመራ ውጤትና ከዚህ ቀደም መመረዙ ጋር ተያይዞ አሌክሴን በአስቸኳይ ህክምና ማግኘት አለበት እያሉ ነው።
የ44 አመቱ አሌክሴ በባለፈው አመት ነሐሴ ወር ላይ ኖቪቾክ በሚባል መርዛማ ኬሚካል ተመርዞ ህይወቱ የተረፈው ለጥቂት ነው።
አሌክሴ መርዘውኛል ብሎ የሚያምነው ቭላድሚር ፑቲንን ቢሆንም የሳቸው አስተዳደር ይሄንን አይቀበለውም።