ከጎዳና የተጠለፈችው ሴት ሞትና በመንገዶች ደኅንነት ላይ ያስነሳው ጥያቄ

በባለፈው ሳምንት "አፋልጉን! ጓደኛችን ሳራ ኤቨራርድ ጠፍታለች። እባካችሁ እርዳታችሁን እንሻለን!" የሚሉ ማስታወቂያዎች በደቡባዊቷ ለንደን በሚገኙ ጎዳናዎች ላይ እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተለጥፈው ነበር።

የ33 ዓመቷ ግለሰብ ወደ ቤቷ እየሄደች እያለች ነው የጠፋችው።

እንዲህ አይነት የአፋልጉን ተማፅኖዎች አዲስ አይደሉም፤ ብዙዎችም በሰላም ይመለሱ ይሆናል በሚልም ተስፋ ነው ማስታወቂያዎችን የሚሰቅሉት።

ከቀናት በኋላ ግን ፖሊስ ሳራ ለመጨረሻ ጊዜ ታየች የተባለችበትን የደኅንነት ካሜራ ምስል አወጣ። ወዳጅ ዘመዷቿ ስጋት ገባቸው። ከዚያ በኋላ የተከተለው ነገር ግን ፍራቻ፣ ድንጋጤና ሐዘን ነበር።

ሳራ ኤቨራርድ ከክላላፋም ኮመን ከሚባል ሰፈር ተነስታ መኖሪያ ቤቷ ወደሚገኝበት ብሪክስተን ሰፈር ለመሄድ ነበር የተነሳችው።

ሰፈሮቹም ሆነ ጎዳናዎቹ በበርካታ ሰዎች ዘንድ የሚዘወተሩ፣ የማታ መብራትም ቦግ ያለባቸውና የደመቁ ናቸው።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለይም ወጣት ሴቶች በእነዚህ ጎዳናዎች ላይ መራመድ የተለመደ ነው።

ይሁን እንጂ ሳራ የገባችበትን ለማወቅ ፖሊስ በሚያደርገው ምርመራም ሴቶች በጎዳናዎች ላይ ብቻቸውን እንዳይዘዋወሩ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

በመጨረሻም ሳራ መገደሏ ታወቀ። በግድያዋም እጁ አለበት የተባለው ፖሊስ በቁጥጥር ስር ዋለ።

በእንግሊዝ ተወልዳ ያደገችው የ33 ዓመቷ ሳራ ኤቨራርድ በአንድ የማርኬቲንግ ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚ ናት።

ጠፋች በተባለችበት ዕለት የካቲት 24/2013 ዓ.ም ምሽት ክላፋም በሚባል ሰፈር በሚገኝ የጓደኛዋ አፓርትመንት ነበረች።

ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አካባቢም ከጓደኛዋ አፓርትመንት ወጥታ ወደ ቤቷ ለመሄድ በእግሯ ጉዟዋን ጀመረች።

ከጓደኛዋ ቤት እስከ ብሪክስተን የሚባለው ሰፈሯ ለመድረስ የ50 ደቂቃ መንገድ ነው።

ከዚያ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው 3፡30 አካባቢ ካሜራ በተገጠመለት ቤት ስታልፍ ነው። ቤቷ አካባቢ ይሁን የት እንደተጠለፈች አልታወቀም።

የሳራ የወንድ ጓደኛ በነገታው እንደጠፋች አስታወቀ።

ከጠፋች ከሳምንት በኋላ ፖሊስ አስከሬን በፌስታል ተጠቅልሎ አገኘ። አስከሬኑ ሳራ ከታየችበት 90 ደቂቃ ርቀት ባለው ሥፍራ ነው የተገኘው።

ከሁለት ቀናት በኋላ አስከሬኑ የሳራ መሆኑ ታወቀ። ፖሊሶች የእሷ አስከሬን መሆኑን ያወቁት ባደረጉት የዘረ መል [ዲኤንኤ] ምርመራ ነው።

በግድያዋም ተጠርጥሮ የተያዘው የ48 ዓመቱ ዋይን ኮዝንስ የተባለ ፖሊስ ነው። ኮዝንስ የሁለት ልጆችም አባት ነው። ምንም እንኳን ምርመራው ባይጠናቀቅም ኮዞንስና ሳራ ትውውቅ እንደሌላቸው ተነግሯል።

በዚያች ምሽት እንዴት ጠልፎ እንደወሰዳትና እንደገደላትም ዝርዝሩን ፖሊስ አሳውቃለሁ ብሏል።

በጎዳናዎች ላይ ተጠልፎ መወሰድ ብዙ የተለመደ ባይሆንም፤ ክስተቱ በርካታ ሴቶችን ሊያስደነግጥና ሊያስፈራ እንደሚችል የፖሊስ ኃላፊው ክሪሲዳ ዲክ ይናገራሉ።

ሁኔታው ብዙዎችን ያስደነገጠ ሆኗል።

በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ስርጭቱን ለመግታት ከወጡ መመሪያዎች መካከል፤ ፈቃድ ያለው ለብቻ ንፋስ ለመቀበል መውጣት ከመሆኑ ጋርም ተያይዞ "እኔ ብሆንስ?" የሚለውን ጥያቄ አጭሯል።

በርካታ ሴቶችም በጎዳናዎች ላይ ሲረማመዱ ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አጋርተዋል።

ብዙዎችም በመንገዶች ላይ ወንዶች እንደሚከተሏቸው፣ ስድቦችን፣ በርካታ ጥቃትንም እንደሚያስተናግዱ ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከል ሄለና ዋዲያ አንዷ ናት። ለቢቢሲ ሬድዮ 5 እንደተናገረችው በመንገድ ላይ የመጀመሪያ ስድብ ያስተናገደችው የ12 ዓመት ልጅ እያለች ነበር።

"ከዚያች ዕለት ጀምሮ ከቤቴ ስወጣ የማደርገውን ነገር በሙሉ ተጠንቅቄ ነው። ስለምለብሰው ልብስ ያስጨንቀኛል። አንዳንድ ጊዜም ውድ ቢሆንም ኮንትራት ታክሲ እንይዛለን። በእጃችን ቁልፋችንን ይዘን ነው የምንንቀሳቀሰው። ስንሮጥም ሆነ ስንራመድ የሙዚቃ ማዳመጫ ሄድፎን አናደርግም። ጨለምለም ባሉ ቦታዎች ላይ አንራመድም። ብዙ ነው ዝርዝሩ። ከጥቃት ለማምለጥ ስንል የምናደርጋቸው ነገሮች አድካሚ ናቸው" ትላለች ሄለና።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተለጠፈ አንድ ጽሁፍ ላይ፤ አንዲት ሴት መንገድ ላይ ወንዶች ጥቃት ያደርሱብናል በሚል ፍራቻ የሚሄዱበትን መስመር የቀየሩ፣ ያልጠራ ስልክ እንደተደወለ አስመስለው ያነሱ፣ ድንገት የሮጡ ካሉ ብላ መጠየቋን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ምላሽ ሰጥተዋል። በአሳዛኝ ሁኔታም የበርካታ ሴቶች የየቀኑ እውነታ ነው።

አንዳንዶችም በጎዳናዎች ላይ ደኅንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ የተሰሩ መተግበሪያዎችንም አጋርተዋል።

በቅርቡ ከሴቶች የጎዳና ላይ ደኅንነት ጋር ተያይዞ ድምፃቸውን ከሚያሰሙ ሴቶች መካከል አንዷ አና ቢርሌይ ናት።

"በጣም የሚያበሳጨው ነገር ይህ የኛ ችግር መሆን አልነበረበትም" በማለት ለቢቢሲ ሬድዮ 5 የተናገረችው አና "የኛ ስህተት አይደለም። ጥቃት የሚደርስብን በራሳችን ምክንያት አይደለም" ትላለች።

ከሰሞኑም ሕይወቷን በአሰቃቂ ሁኔታ ላጣችው ሳራ ክላፋሃም መታሰቢያነት የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓትንም አስተባብራለች። ለሳራ መታሰቢያነትም በርካታ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት በአገሪቷ ውስጥ ለመካሄድ እቅድ ተይዞ ነበር።

ከዚህ ሥነ ስርዓት ጀርባ ያለው ዋነኛ መልዕክት "ሕዝባዊ ቦታዎችም የሴቶች ሊሆኑ ይገባል። ሴቶች በጎዳናዎች ላይ በሚጓዙበት ወቅት ደኅንነት እንዲሰማቸው ድምጻችንን እናሰማ" የሚልና የመተባበርና አንድ ላይ የመሆን መልዕክትን አዝሏል።

ለሳራ፣ ክላፋሃም ሰፈር ሊደረግ የታሰበው የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መመሪያ ምክንያት መሰረዙን ተከትሎ አና ፖሊስን ተችታለች።

ፖሊስ አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ ሥነ ሥርዓት እንዲካሄድ ማድረግ ይችል ነበረም ትላለች። ሳራንም ለማሰብ ሕዝቡ የሻማም ሆነ ሌሎች መብራቶችን የማብራት ሥነ ሥርዓት በየቤታቸው በር አድርጉ ተብሏል።

ምንም እንኳን ፖሊስ ስብሰባን ቢከለክልም በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በክላፋም ኮመን ሰፈር ላይ ተሰባስበው ሳራን ዘክረዋታል።

ነገር ግን በቦታው ላይ የነበሩ ሰዎችን ፖሊስ ለመበተን ያደረገው ሙከራ ከፍተኛ ውግዘት አጋጥሞታል። በተለይም የወንዶች ጥቃትን ለማውገዝ በተደረገው የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ ወንድ ፖሊሶች ሴቶችን ለመበተን ኃይል መጠቀማቸው በበርካቶች ዘንድ ንዴትን ፈጥሯል።

'ጥቃት አድራሾቹ ወንዶች ናቸው'

የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በምትከበርበት ዕለት የእንግሊዟ የምክር ቤት አባል ጄስ ፊሊፕስ በባለፈው ዓመት የተገደሉ ሴቶችን ስም ዘርዝረዋል። እነዚህን ሴቶች በመግደልም ክስ የቀረበባቸው ወንዶች ናቸው።

በተለይም በዚች ቀን ላይ የሳራ አስከሬን የተገኘበት ቀን ጋር ከመገጣጠሙ ጋር ተያይዞ የፓርላማ አባሏ በወንዶች ጥቃት የተገደሉ የ118 ሴቶችን ስም ጠቅሰዋል።

"በወንዶች የሚገደሉ ሴቶችን እንደተለመደ ጉዳይ አድርገን ተቀብለነዋል" በማለት ለምክር ቤቱ የተናገሩት ጄስ "የሴቶች መገደል በአሳዛኝ ሁኔታ ተለምዷል" ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፓርላማው ላዕላይ ምክር ቤት ወንዶች በጎዳና ላይ የሚወጡበት ሰዓት ላይ የሰዓት እላፊ አዋጅ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። ወንዶች ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ በቤታቸው እንዲወሰኑ ነው ጥያቄው የቀረበው።

ጄስ ፊሊፕስ ከዚህ ጥሪ በኋላ ከስካይ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህ ጥሪ መልዕክት ለማስተላለፍና ጥያቄ ለማጫር ሲባል ያቀረቡት እንደሆነ ተናግረዋል።

"ሴቶች ጥቃት በሚደርስባቸው ወቅት ፖሊሶች ተጠቂዎችን ጥፋተኛ ባደረገ መልኩ 'ለምን አርፋችሁ ቤታችሁ አትቀመጡም ነበር?' ሲሉ ምንም አንልም። በተለመደ መልኩ ተቀብለነዋል" ይላሉ።

የወንዶች ምላሽ ምን ይመስላል?

'ቢ ኤ ማን' (ወንድ ሁን) የሚለው መጽሐፍ ደራሲ ክሪስ ሄሚንግስ እንደሚለው እስከዛሬ የነበሩ ክርክሮችን ማስተካከል እንደሚያስፈልግና ወንዶች የጥቃቱ አድራሾች እንደመሆናቸው መጠን የዚህም ጉዳይ ማዕከል ሊሆኑ ይገባል ይላል።

"ጥቃት አድራሾቹ እኛ ነን። ወደድንም ጠላንም ይሄ ስለ ወንዶች ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።

መረጃዎችን በማጣቀስም 90 በመቶ የሚገደሉት ሴቶች በወንዶች እንደሆነም ይናገራል።

"እንደ ወንዶች ማድረግ የምንችለው ምንድን ነው። ወንድሞቻችን ገዳይ፣ ደፋሪ ተብለው ወይም ጥቃት አድራሾች እንዳይሆኑ ምን ማድረግ እንችላለን የሚለው ላይ መነጋገር ያስፈልጋል" ብሏል።

ሳራ ከጠፋችበት ጎዳና በአምስት ደቂቃ ርቀት የሚኖረው ስቱዋርት ኤድዋርድስ የተባለ ግለሰብ "በፀጥታ በተሞሉ ጎዳናዎች ላይ ሴቶች ሲራመዱ ወንዶች ፊታቸውን ማሳየት እንዲሁም በቅርበት ካለመከታተል ውጭ ሴቶች ደኅንነት እንዲሰማቸው ምን ማድረግ እንችላለን?" በማለት በትዊተር የጠየቀው ጥያቄ 27 ሺህ ሰዎች ወደውታል።

ነዋሪነቱን በደቡብ ለንደን ያደረገው የሬስቶራንቶች ምግብ ገምጋሚ ጄይ ሬይነር በበኩሉ "ፀጥ ረጭ ባለ ጎዳና ላይ ብቻዋን የምትራመድ ሴት ካየሁኝ ከኋላዋ አልከተላትም መንገዱን ተሻግሬ በሌላ አቅጣጫ እሄዳለሁ። ሰውነቴ ገዘፍ ያለ ወንድ ነኝ እና በጨለማ ላይ ሴቶች ሲያዩኝ ሊፈጠርባቸው የሚችለው ፍራቻ ይገባኛል" በማለት ምላሽ ሰጥቷል።

አንዳንዶች በበኩላቸው በተቃራኒው ሁሉም ወንዶች አይደሉም ጥቃት አድራሾች በማለትም በትዊተር ላይ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት የዩናይትድ ኪንግደም ችግር አይደለም፤ ዓለም አቀፋዊ ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት በዚህ ሳምንት ባወጣው መረጃ በዓለም ላይ ከሦስት ሴቶች አንዷ ወይም 736 ሚሊዮን ሴቶች አካላዊ፣ ወይም ወሲባዊ ጥቃቶችን ያስተናግዳሉ ብሏል።