ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ በቦይንግ 737- ማክስ 8 አደጋ ምርመራ የመጨረሻ ምዕራፍ መደረሱን አስታወቀች
መጋቢት 1/ 2013 ዓ.ም ሁለተኛ አመቱን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ምርመራ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ኢትዮጵያ አስታውቃለች።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት የአደጋውን መታሰቢያ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በወቅቱ በዓለም አቀፍ ሁኔታ በተጋረጠው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የምርመራ ሂደቱ እንደዘገየ አስታውሶ በአሁኑ ሰዓት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ ለመድረስ መቻሉንም አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅትም የጥንቃቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ ምርመራው መቀጠሉንና የበረራ ቁጥር ኢቲ-302 አስመልክቶ የመጨረሻውን ሪፖርት እና በቀጣይነት መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ሪፖርቱ እንደጠናቀቀ የሚያሳውቅ መሆኑንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-ማክስ8 በረራ ቁጥር ኢቲ 302 ከአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ማረፊያ ወደ ናይሮቢ ኬንያ ለመብረር የተነሳው መጋቢት 1፣ 2011 ዓ.ም ከጥዋቱ 2፡44 ነበር።
አውሮፕላኑ በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በቢሾፍቱና ሞጆ ከተሞች መካከል ጊምብቹ ወረዳ ልዩ ስሙ ኤጄሬ በተባለ ቀበሌ ወድቆ ተከሰከሰ።
በወቅቱም አሳዛኝ በሚባል ሁኔታ ከ157 በላይ ሰዎች ህይወትን ቀጥፏል።
በወቅቱ ተሳፍረው የነበሩት መንገደኞች ከሰላሳ አገራት የተውጣጡ ሲሆኑ ከአደጋው የተረፈ ሰው አልነበረም።
የተከሰከሰው አውሮፕላን አብራሪ ካፕቴን ያሬድ ጌታቸው ከቦሌ አየር ማረፊያ በተነሱ በደቂቃዎች ልዩነት ችግር እንዳጋጠማቸውና ተመልሰው ለማረፍ እንደሚፈልጉ ለበረራ ተቆጣጣሪዎች አስታውቆ ነበር ማለቱ ይታወሳል።
አደጋው መድረሱን ተከትሎ በትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር ያለው የኢትዮጵያ አውሮፕላን አደጋ ምርመራና ቢሮ የምርመራ ደረጃ ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃም በየጊዜው ሲያሳውቅ መቆየቱን አስታውሷል።
የመጀመሪያ ደረጃ ቅድመ ግኝት
የኢትዮጵያ የአደጋ ምርመራ ቢሮ፣ የአሜሪካ ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ፣ የፈረንሣይ ቢኢኤና የአውሮፓ አቪዬሽን ሴፍቲ ኤጀንሲ ባለሙያዎች፣ ከኢቲ302 ከመቅረፀ ድምፁና የበረራ መረጃ መቅጃ የተገለበጠውን መረጃ ተንትነውም የመጀመሪያ ደረጃ ግኝት ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
በቅድመ ምርመራው መሰረት አውሮፕላኑ መብረር በሚያስችል አቋም ላይ እንደነበር፣ ሲነሳም መብረር በሚችልበት ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንደነበር እና አብራሪዎቹ መመሪያ ተከትለው ለመቆጣጠር ጥረት እንዳደረጉ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሚኒስትሯ በወቅቱ አውሮፕላኑ ያለችግር በረራውን እንደጀመረ፣ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል ማዘቅዘቁንና ችግር ባጋጠማቸው ወቅትም አብራሪዎቹም የሚጠበቅባቸውን እንዳደረጉ፣ ይሁን እንጂ አውሮፕላኑን መቆጣጠር እንዳልቻሉ አመልክቷል።
ከዚህም በመነሳት የምርመራው ቡድን በአውሮፕላኑ ላይ ያጋጠመው "የፊተኛው ጫፍ ወይም አፍንጫ የመደፈቅ ችግርን" ለመቆጣጠር የሚያስችል የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓትን አምራቹ እንዲፈትሽ እና ይህንን ችግር ለመቆጣጠር የሚያስችለው ሥርዓትም በአግባቡ መዘርጋቱን ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት ምክረ ሃሳብ መቅረቡ ተገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ የምርመራ ሪፖርቱን በተመለከተ እንዴት ይገለፅ የሚለው ላይ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረት እንደነገሰም ብሉምበርግ በትናንትናው ዘገባው አስነብቧል።
የአሜሪካ መርማሪዎች ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የራሳቸውን አስተያየትና ማጠቃለያዎች በተናጠል ለመስራት አስበዋል ብሏል ብሉምበርግ ትናንት ባስነበበው ዘገባ።
በሪፖርቱ ላይ የተካተቱትን ላይ ግኝቶችን አስመልክቶ ስምምነቶች አለመኖሩንም ኢትዮጵያና አሜሪካ የሚያደርጓቸውን ውይይቶች በቅርበት የሚከታተሉና ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚያሻው ከመሆኑም አንፃር ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ብሉምበርግ አስነብቧል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ትራስፖርት ሴፍቲ ቦርድ በአደጋው ወቅት የአብራሪዎቹን ድርጊት በተመለከተና በአውሮፕላኑ ላይ ያለውን ሲስተም በምን መንገድ መገለፅ አለበት የሚለው ላይ ስጋት እንዳጫረበት ስሙ ያልተጠቀሰ ምንጭ ለብሉምበርግ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ሪፖርት በመርማሪዎችና፣ በውጭ ባለድርሻ አካላት ውይይት እየተደረገበት እንደሆነ ኢትዮጵያ እያደረገችው ስላለው ጉዳይ በቅርበት የሚያውቅና ስሜ አይጠቀስ ያለ ግለሰብ መናገሩንም ይኸው የብሉምበርግ ዘገባ አስነብቧል።
የብሉምበርግ ዘገባ የኢትዮጵያን የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣናትና የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስቴርን አስተያየት ማካተት ባይችልም የአሜሪካ ብሔራዊ ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ በበኩሉ ለኢትዮጵያውያን መርማሪዎች "ምርመራቸውን እንዲያጠናቅቁ ድጋፍ በመስጠት ይህም ማለት ረቂቁን በመገምገምና አስተያየታችን በመስጠት እንደግፋቸዋለን" በማለት መግለጫ ማውጣቱን አስነብቧል።
በአለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ተቀፅላ 13 መሰረት የምርመራ መረጃዎቹ በሙሉ ይፋ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ባለስልጣናት አማካኝነት ነው። ተቀፅላ 13 አለም አቀፍ ምርመራዎች በሚደረጉበት ወቅት አገራቱ በምን መንገድ ማካሄድ አለባቸው የሚለውን በበላይነት የሚቆጣጠር ነው።
አደጋው ከደረሰ በኋላ ለወራትም ያህል በኢትዮጵያና አሜሪካ ባለስልጣናት መካከል አለመግባባት ነበር ተብሏል።
ከአመት በፊትም የኢትዮጵያ መርማሪዎች የአደጋውን ምክንያት ለማጠቃለል በዝግጅት ላይ የነበሩ ቢሆንም ከአሜሪካና ፈረንሳይ ባጋጠማቸው ተቃውሞ ምክንያት ሪፖርቱን እንደያዙት ብሉምበርግ አስነብቧል።
ከዚህ ቀደም የናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድና የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ አደጋ ምርመራ ቢሮ ከመቅረፀ ድምፅና ከበረራ መረጃ መቅጃ የተገለበጡ መረጃዎች እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ሪፖርተር አስነብቧል።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የመረጃ ሳጥኑ መረጃ ቅጂ እንዲሰጥ ፈቃደኝነት እንዳላሳዩና አሜሪካ ጫና ለማሳደር እየሞከረች እንደሆነም ሪፖርተር በዚሁ ዘገባ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ማስነበበቡ የሚታወስ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በፊት የኢንዶኔዥያ ላየን ኤር ከመዲናዋ ጃካርታ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከወደቀው ማክስ አውሮፕላን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ቢኤኤ አረጋግጧል።
የሁለቱም አውሮፕላኖች ከተነሱ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መከስከሳቸውንም የቦይንግ 737 -8 ማክስ አውሮፕላን መሠረታዊ የንድፍ ችግር እንዳለበትና ቦይንግ የዲዛይን ችግሩን ለማስተካከል ብሎ በሚስጥር ያስጫነው ኤምካስ የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር አውሮፕላኑን ለአደጋ እንዳጋለጠው መገለፁ የሚታወስ ነው።
በተለይም የአሜሪካ የአቪየሽን ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት (FAA) የቦይንግ ምርቶችን ደረጃና ጥራት በመቆጣጠርና በማጽደቅ ሂደት ላይ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ለቦይንግ አሳልፎ መስጠቱ ዓለምን ያስደነገጠ ክስተት ነበር።
ባጋጠመኝ የፋይናንስ አቅም መመናመን የአውሮፕላኑ አምራች ራሱ የአዳዲስ አውሮፕላኖችን ብቃት በከፊል እንዲያረጋግጥ አድርጊያለሁ በማለት ለሚዲያዎች ተናግሮም ነበር።
በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ 346 ሰዎች ያለቁበት የማክስ አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ቅጣት የተጣለበት ሲሆን በማክስ አውሮፕላን የበረራ ደኅንነት ሥጋት የገባው የዓለም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ፣ አምራች አገሯን አሜሪካ ጨምሮ አውሮፕላኑ ላልተወሰነ ጊዜ ከሥራ ውጪ እንዲሆን ማድረጉ ይታወሳል፡፡