አሜሪካዊው ራፐርና የፊልም ተዋናይ ዲኤምኤክስ አረፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካዊው የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝና የፊልም ተዋናይ ዲኤምኤክስ ለአምስት ቀናት በልብ ህመም ህክምና ላይ ከቆየ በበኋላ በ50 ዓመቱ አረፈ።
በትክክለኛ ስሙ ኧርል ሲሞንስ በሚል የሚታወቀው ዲኤምኤክስ ሆስፒታል ውስጥ ቤተሰቦቹ ባሉበት በስትንፋስ ማቆያ መሳሪያ ሲረዳ ቢቆይም ህይወቱ አልፏል።
ቤተሰቡ ከህልፈቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ ዲኤምኤክስ "አስከመጨረሻው ድረስ የተፋለመ ጠንካራ ነበር" ብሏል።
"ሙዚቃው በመላው ዓለም ያሉ ለቁጥር የሚታክቱ አድናቂዎቹን ያነቃቃ ሲሆን ጥሎት ያለፈው የተለየው ውርስም ለዘላለሙ ይኖራል" ሲል ጨምረዋል።
ዳርክ ማን ኤክስ ወይም ዲኤምኤክስ፤ ጄይዚን፣ ጃ ሩልን እና ኤልኤል ኩል ጄን ከመሳሰሉ አርቲስቶች ጋር በመተባበር የሰራ ግንባር ቀደም የሂፕ ሆፕ አቀንቃኝ ነበረ።
በሙዚቃ ሰንጠረዦች ላይ በቀዳሚነት የተቀመጡ በርካታ ሙዚቃዎችን ያቀነቀነው ዲኤምኤክስ ከሙዚቃ ሥራው በተጨማሪ በፊልሙ ዘርፍም ዝናን አግኝቶ ነበር።
በዚህም ክራድል ቱ ዘ ግሬቭ፣ ሮሚዮ መስት ዳይ እና ኤግዚት ዉንድስ በተሰኙ ፊልሞች ላይም በትወና ተሳትፏል።
እኤአ በ1970 በኒው ዮርክ ማውንት ቬርኖን የተወለደው ዲኤምኤክስ ለረዥም ዓመታት በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ውስጥ የነበረ ሲሆን በተደጋጋሚም ወደ ማገገሚያ ገብቷል።
የ15 ልጆች አባት የሆነው ዲኤምኤክስ እንስሳት ላይ ጭካኔ የተመላበት ድርጊት በመፈፀም፣ በግዴለሽነት በማሽከርከር፣ እንዲሁም አደንዛዥ እፅ እና የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት እስር ቤት ገብቶ ያውቃል።
እንደ ቤተሰቡ ከሆነ ዲኤምኤክስ የሞተው አርብ ዕለት ኒው ዮርክ ዋይት ፕሌንስ ውስጥ በሚገኘው በዋይት ፕሌይንስ ሆስፒታል ነው።
"በሙሉ ልቡ ቤተሰቡን ይወድ ነበር። እኛም ከእርሱ ጋር ያሳለፍነውን ጊዜ ታላቅ ስፍራ አለን" ሲል ቤተሰቡ መግለጫው ላይ አስፍረዋል።
"በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ፍቅራችሁንና ድጋፋችሁን ላሳያችሁን ሁሉ ምስጋናችን ይድረሳችሁ" ሲሉም ምስጋና አቅርበዋል።












