ልዑል ፊሊፕ፡ የዓለም መሪዎች በልዑል ፊሊፕ ሞት ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው

ንግሥት ኤልዛቤት እና ልዑል ፊሊፕ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የልዑል ፊሊፕን ሞት ተከትሎ የዓለም መሪዎች የተሰማቸውን ሐዘን ለንጉሣዊው ቤተሰብ እየገለጹና ትውስታቸውን እያጋሩ ነው።

የባኪንግሃም ቤተመንግሥት ዛሬ እንዳስታወቀው የንግሥት ኤልዛቤት ባለቤት ልዑል ፊሊፕ በ99 ዓመታቸው አርፈዋል።

ልዑሉ ንግሥቲቱን በዓለም ዙሪያ ባደረጓቸው በመቶዎቹ በሚቆጠሩ የባሕር ማዶ ጉብኝቶች ላይ አብረዋቸው ተገኝተዋል።

"ዓለማችን ከዚህ በኋላ ፈጽማ የማታየው ትውልድ መገለጫ ነበሩ" በማለት የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹት የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ናቸው።

የቀድሞዋ የአውስትራሊያ መሪ ጁሊያ ጊላርድ ደግሞ ልዑሉ "የተግባር ሰው ከመሆናቸው ጎን ለጎን ተጫዋችም ነበሩ" ሲሉ አስታውሰዋቸዋል።

የቤልጂየሙ ንጉሥ ፊሊፕ ደግሞ የሐዘን መግለጫቸውን ለንግሥቲቱ በግል የላኩ ሲሆን፤ ግርማዊነታቸው አመቺ ጊዜ ሲያገኙ ሊያናግሯቸው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

"ማልታን ቤታቸው አድርገው በተደጋጋሚ ሲመጡ በነበሩት በልዑል ፊሊፕ ሞት ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል። ሕዝባችንም ትተውት ያለፉትን ትዝታ ዘወትር ያስታውሳል" ሲሉ የማልታው ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቤርት አቤላ ጽፈዋል።

"በዚህ ከባድ ሰዓት ውስጥ ሐሳቤና ጸሎቴ ከእርስዎና ከዩናይትድ ኪንግደም ሕዝብ ጋር ነው" ሲሉ ሊቱዋንያው ፕሬዝዳንት ጊታናስ ኑሴዳ ለንግሥቲቱ ጽፈዋል።

የስዊዲኑ ንጉሥ ካርል ጉስታፍ "ልዑሉ ትልቅ ዋጋ የምንሰጠው ግንኙነት የነበረን ሲሆን፤ ለበርካታ ዓመታት የቤተሰባችን ታላቅ ወዳጅ ነበሩ" ብለዋል።

የኔዘርላንድስ ንጉሣዊ ቤተሰብ ልዑል ፊሊፕን በታላቅ አክብሮት እንደሚያስታውሳቸው ገልጾ "ልዑሉ ሕይወታቸውን የብሪታኒያን ሕዝብና በርካታ ተግባራትና ኃላፊነቶችን ለመወጣት አውለውታል። ህያው ስብዕናቸው የማይረሳ ትውስታን ትቷል" ብለዋል።

የኒው ዚላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርንም "በኒው ዚላንድ ሕዝብና መንግሥት ስም ልባዊ ሐዘኔን ለግርማዊነታቸውና ለመላው ንጉሣዊ ቤተሰብ መግለጽ እወዳለሁ" ሲሉ የሐዘን መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲም ሐዘናቸውን ኀብሪታኒያ ሕዝብና ለንጉሣዊው ቤተሰብ ገልጸው፤ ልዑሉ "የላቀ ወታደራዊ ሙያና በማኅበረሰብ አገልግሎትም ውስጥ ቀዳሚ ነበሩ" ሲሉ አስታውሰዋቸዋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የኤደንብራውን መሥፍን "የቤተሰብ እሴቶች ከፍታ እንዲሁም የእንግሊዝ ሕዝብ እና የዓለም ሕዝብ አንድነት ተምሳሌት " ሲሉ ገልፀዋቸዋል።

አክለውም " የሰው ልጅ በሰላም አብሮ እንዲኖር " አበክረው መስራታቸውን ገልፀዋል።

ከአፍሪካ መሪዎች መካከል ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ውጣ ውረድ የበዛበት ግንኙነት ያሳለፈችው ዚምባብዌ እንዲሁም በቅርቡ መሪዋን ያጣችው ታንዛንያ የሐዘን መግለጫ አስተላልፈዋል።

አዲሷ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚኣ ሱሉሁ ሐሳን "ጥልቅ የሆነ ሐዘናቸውን" ባለቤታቸውን ላጡት ለንግሥቲቱ፣ ለንጉሣዊው ቤተሰብና ለዩናይትድ ኪንግደም ሕዝብ ገልጸዋል። ጨምረውም "በዚህ አስቸጋሪ የሐዘን ጊዜ አብረናቸው እንቆማለን" ብለዋል።

ታንዛኒያ ባለፈው መጋቢት ወር የ61 ዓመቱን ፕሬዝዳንቷን ጆን ፖምቤ ማጉፉሊን በሞት መነጠቋ ይታወሳል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ልዑሉ "ለአገራችንና ለዓለም ማኅበራዊ መስተጋብር በርካታ አስተዋጽኦን አብርክተዋል" በማለት ልዑሉ የታላቅ አላማና መርህ ሰው በመሆን "ለሌሎች መልካም ነገሮችን በማድረግ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ነበሩ። እኛም በንግሥታችን ህይወት ውስጥ አንድ ምሰሶ እንደሆኑ በክብር እንዘክራቸዋልን" ብለዋል።

ልዑሉ "እንከን አልባ የሕዝብ አገልጋይ ነበሩ። እስራኤልም ሆነ ዓለም በእሳቸው ሞት በጣሙን ይጎዳሉ" ያሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ናቸው።

በ1969 (እአአ) ያረፉት የልዑሉ እናት የባተንበርጓ ልዕልት አሊስ ቀብራቸው የተፈጸመው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው በማሪያም መቅደላዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ነበር።