በዱባይ የእርቃን ፎቶ የተነሱ ሴቶች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በዱባይ ሕንጻ በረንዳ ላይ የእርቃን ፎቶ እየተነሱ የነበሩ ዩክሬናዊያን በቁጥጥር ሥር ውለው ‹የሕዝብን ጨዋነት እሴት በመገርሰስ› ሕግ ተከሰሱ፡፡

ባለፈው ቅዳሜ የተለቀቀ የቪዲዮ ምሥል በርከት ያሉ ሴቶች እርቃናቸውን ሆነው በረንዳ ላይ ፎቶ ሲነሱ ያሳያል፡፡

ከነዚህ መሀል 11 ዩክሬናዊያን ይገኙበታል፡፡ ሁሉም በቁጥጥር ሥር ስለመዋላቸው የዩክሬን ኤምባሲ ለቢቢሲ አረጋግጧል፡፡ ከታሳሪዎቹ መካከልም አንዲት ሩሲያዊት ትገኝበታለች፡፡

የሕዝብን ጨዋ እሴት መጣስ በዱባይ እስከ 6 ወር እስር እና 5ሺ ዲርሀም ያስቀጣል፡፡

በርካታ የተባበሩት አረብ ኢምሬት የአገሪቱ ሕጎች የሚመነጩት ከሸሪአ ሕግ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት በርካታ ጎብኚዎች በአገሬው ተቀባይነት የሌላቸው የፍቅር ንክኪዎችና በተለይም ከተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳርገዋል፡፡

በማሪና ሰፈር፣ ዱባይ በተነሳው በዚህ የእርቃን ፎቶ በርካታ ሴቶች ተሳትፈዋል፡፡

የዩክሬን ኤምባሲ ዜጎቹን ማክሰኞ እንደሚጎበኛቸው አስታውቆ ነበር፡፡

የሩሲያ ሚዲያዎች ቢያንስ 8 ሩሲያዊያን ሴቶች በዚህ የእርቃን ፎቶ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዘግበው ነበር፡፡ ነገር ግን ሪያ ዜና አገልግሎት ኃላፊዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ይህን ፎቶ ያሰናዳ አንድ ሩሲያዊት ብቻ ናት በቁጥጥር ሥር የዋለችው፡፡

ዜና አገልግሎቱ እንዳለው ሩሲያዊቷ በትንሹ 18 ወራት እስር ይጠብቃታል፡፡

የዱባይ ፖሊስ እንዳስጠነቀቀው ማንኛውም ግለሰብ የልቅ ወሲብ ፊልሞችና ፎቶዎችን እንዲሁም የሕዝብን ማኅበረሰባዊ ሞራል የሚያጎድፉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ለእስር የሚዳርጉ ናቸው፡፡

ሴቶቹ የፈጸሙት ተግባር የኢምራትን እሴትና ጨዋነት የሚጻረሩ ናቸው ብሏል ፖሊስ፡፡

ማንኛውም ዱባይ የሚኖር ሰው የአገሬውን ሕግ የማክበር ግዴታ አለበት ያለው ፖሊስ ጎብኚዎችም ቢሆኑ ከሕግ በላይ አይደሉም ብሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2017 አንዲት እንግሊዛዊት በትዳር ካልተጣመረችው ወንድ ጋር በፈቃደኝነት ወሲብ ስትፈጽም በመገኘቷ 1 ዓመት እስር ተፈርዶባት ነበር፡፡

ፖሊስ ጉዳዩን የደረሰበት ተከሳሽዋ ግለሰቡ ከግንኙነታቸው በኋላ አላስፈላጊ መልእክት እየላከ ስላስቸገራት ይህንኑ ለዱባይ ፖሊስ ሪፖርት ባደረገችበት ጊዜ ነበር፡፡