ሰሜን ኮሪያ ለቶክዮ ኦሎምፒክ "እንዳትጠብቁኝ አልመጣም" አለች

ሰሜን ኮሪያ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በሚደረገው የቶክዮ ኦሎምፒክ አልሳተፍም ብላለች፡፡

የማልሳተፈውም ‹ስፖርተኞቼ በኮቪድ ይለከፉብኛል ብዬ ስለምሰጋ ነው› ብላለች፡፡

ይህ የሰሜን ኮሪያ ውሳኔ ከየትኛው አገር በላይ ልቧን የሰበረው የደቡብ ኮሪያን ነው፡፡

ምክንያቱም ደቡብ ኮሪያ ይህን የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን አጋጣሚ በመጠቀም ከባላንጣዋ ጋር የመቀራረብ ፍላጎትና ተስፋን አሳድራ ስለነበረ ነው፡፡

በ2018 ሁለቱ አገሮች ለዊንተር ኦሎምፒክ የጋራ ቡድን ማሰለፋቸው አይዘነጋም፡፡ ያ አጋጣሚ ሁለቱን አገሮች እንዲቀራረቡ ረድቷቸው ነበር፡፡

ፒዮንግያንግ አሁንም ድረስ ቫይረሱ ወደ አገሬ ድርሽ አላለም ብላ ትሟገታለች፡፡

የወረርሽኝና ተያያዥ የጤና ጉዳዮችን በውል የሚያውቁ ባለሙያዎች ግን ይህ የማይመስል ነገር ነው ይላሉ፡፡

የሰሜን ኮሪያ ቴሌቪዥን ይህን ‹ከኦሎምፒክ ወጥተናል› ውሳኔ ይፋ ያደረገው በመጋቢት 25 የሰሜን ኮሪያ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት የወረርሽኙን መቀስቀስ ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ ጥብቅ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምራ ነበር፡፡

ድንበሮቿን የዘጋችው ቀደም ብላ በጥር ወር ነበር፡፡ ወደ አገሯ የሚገቡ የውጭ ዜጎችንም ለይታ ማዋል ማሳደርም ጀምራ ነበር፡፡

በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ባቡሮችና የሕዝብ ማመላለሻ መኪናዎች ወደ አገሯ እንዳይገቡ እግድ አስቀምጣ ነበር፡፡

በሁለቱ ወንድም-እህት ሕዝቦች መካከል በ1953 የኮሪያዎች ጦርነት ሲያበቃ የሰላም ስምምነት ባለመደረሱ ሰሜን ኮሪያ አሁንም ከደቡብ ኮሪያ ጋር በጦርነት ላይ እንዳለች ነው የምታምነው፡፡