ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በናይጄሪያ ከ1800 በላይ ታራሚዎች ከእስር ቤት ማምለጣቸው ተሰማ
በናይጄሪያ የሚገኝ እስር ቤት በታጣቂዎች ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ከ1 ሺህ 800 በላይ ታራሚዎች ማምለጣቸው ተገልጿል።
ክስተቱ ያጋጠመው በደቡብ ምስራቅ በምትገኘው ኦውሪ ግዛት ሲሆን ታጣቂዎች የእስር ቤቱን ሰብረው በመግባቱ የህንፃውን የተወሰነ ክፍልም በቦንብ አፈንድተውታል ተብሏል።
ኦውሪ ማረሚያ ማዕከል ተብሎ በሚታወቀው እስር ቤት ታጣቂዎቹ በጭነት መኪናና በአውቶብስ ተጭነው የመጡት በትናንትናው እለት ነው።
ፖሊስ ጥቃቱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ታጣቂዎች ተወንጫፊ ሮኬቶችን ጨምሮ፣ ከባድ መሳሪያዎችና ቦንቦችን ይዘው ነበር ብሏል።
በዚህም አጋጣሚ በርካታ ታራሚዎች ማምለጥ እንደቻሉም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
ለዚህ የእስር ቤት ጥቃት አድራሹ የቢያፍራ ቀደምት ህዝቦችን በመወከል የሚታገለውና በናይጄሪያ የታገደው ተገንጣዩ ቡድን ነው ሲል ፖሊስ አስታውቋል።
የናይጄሪያ ማረሚያዎች ማዕከል እንዳስታወቀው እስካሁን ድረስ ያመለጡ የታራሚዎች ቁጥር 1 ሺህ 844 መሆኑን ነው።
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ጥቃቱን "በስርዓት አልበኞች የተፈፀመ የሽብር ጥቃት" ሲሉ አውግዘውታል።
ከዚህም በተጨማሪ የፀጥታው ሁኔታ እንዲጠናከር የተጨማሪ ሃይል አስፈላጊነትን አፅንኦት በመስጠት ከመናገር በተጨማሪ፤ ጥቃቱን ያደረሱት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እንዲሁም ያመለጡት ታራሚዎችም በአስቸኳይ እንዲያዙ ብለዋል።
ኢንዲጂኒየስ ፒፕል ኦፍ ባያፍራ ተብሎ የሚታወቀው የተገንጣዩ ቡድን እንቅስቃሴ ቃለ አቀባይ በበኩላቸው የሰኞውን ጥቃት አድርሰዋል መባላቸው "ሃሰት" እንደሆነ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
በማዕከላዊው መንግሥትና በአካባቢው በሚኖሩ ኢግቦ ህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት የባላንጣ መሆኑን ተከትሎ ግዛቲቷ የተገንጣዮች ቡድን መፈልፈያ ሆናለች።
ከጥር ወር ጀምሮ በርካታ የፖሊስ ጣቢያዎች ጥቃትን ያስተናገዱ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ የፖሊስ መኪኖች ተቃጥለዋል እንዲሁም ቦምቦችና ተቀጣጣይ ፈንጆች ተዘርፈዋል።
ለዚህኛው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።