ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጋዜጣ አዘጋጁ ስለ ቤንያሚን ኔታንያሁ አሉታዊ ዜናዎች "እንዳላትም ታዝዣለሁ" አለ
በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሙስና ክስ የፍርድ ሂደት ላይ ምስክር ሆኖ የቀረበው አዘጋጅና የቀድሞ ስራ አስፈፃሚ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ አሉታዊ ዜናዎችን እንዳያትም ትእዛዝ እንደተሰጠው ተናግሯል።
ኢላን የሹዋ የተባለው የዋላ ድረ-ገፅ የቀድሞ ስራ አስፈፃሚ ችሎት ፊት ቀርቦ እንዳስረዳው አሉታዊ ፅሁፎችን ከመከልከል በተጨማሪ ሻውል ኢሎቪትች የተባሉት የድረገፁ ባለቤት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተቀናቃኞችን የሚያጥላላ ፅሁፎች እንዲያወጣ ታዝዣለሁ ብሏል።
አቃቤ ህግ እንደሚለው ቤንያሚን ኔታንያሁ እርሳቸውን የሚደግፍና የሚያሟካሽ ፅሁፍ እንዲወጣ በማለት በሚሊዮን ዶላሮች የሚያስወጣ ውሳኔን አስተላልፈዋል በማለት ይከሳቸዋል።
የድረገፁም ባለቤት ይሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም አይነት ስህተት አልፈፀምንም ሲሉ ይናገራሉ።
በሙስና፣ በማጭበርበርና እምነት በማጉደል በሶስት ተነጣጣይ ወንጀሎች የተከሰሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው ክሱን "ሽፋን" ነው በማለት በተፃራራው አቃቤ ህግ መንግሥታቸውን ለመጣል የሚያደርገው ሙከራ ነው ብለውታል።
የባለፈውን ወር ምርጫ ተከትሎ ቀጣዩን መንግሥት የሚመሰርተውን አካል ለመወሰን የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት የምክር ቤቱ እንደራሴዎቹን ሰብስበው ነበር ተብሏል።
በዚህም ወቅት በተደረገው የድምፅ መስጫ ስነ ስርዓት አገሪቷ በሁለት አመት ውስጥ አራት ምርጫዎችን እንድታደርግ ያስገደዳትን ፖለቲካዊ አጣብቂኝ መፍታት ሳይቻል ቀርቷል ተብሏል።
የቀኝ ክንፍ መሪው ኔታንያሁና በአንድ ጎራ እንዲሁም በሌላ ጎራ ያሉት ተቀናቃኞቻቸው ቀጣዩን መንግሥት ለመመስረት ከፍተኛ ድምፅ ማግኘት አልቻሉም ተብሏል።
የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ሩቨን ሪቭሊን በሚቀጥለው ሳምንት የፓርቲውን አመራሮች ጋሮች ለመምከር ቀጠሮ የያዙ ሲሆን በመቀጠልም ቀጣዩን የጥምር መንግሥት ለመመስረት ትልቅ እድል ያለውን አካል እጩ ያቀርባሉ ተብሏል።
ክሶቹ ምንድንናቸው?
አንደኛው የተነሳባቸው ጉዳይ አንድ የእስራኤል ጋዜጣ በአዎንታዊ መልክ ስለሳቸው እንዲዘግብ አድርገዋል ነው።
እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የህትመቱ አዘጋጅም ክስ እንደሚጠብቃቸው ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።
ሁለተኛው ውንጀላም ወደ 300 ሺ ዶላር የሚያወጣ ስጦታ ከታዋቂው ባለሀብትና በሆሊውድ ታዋቂ የፊልም ኩባንያ ባለቤትና አርኖን ሚልቻንና ከሌሎች ደጋፊዎቻቸው ተቀብለዋል የሚል ነው።
ጀሩሳሌም ፖስት እንደዘገበው ስጦታዎቹ ሻምፓኝ፣ ሲጋራና ሌሎች ሲሆኑ በምላሹም አርኖን የአሜሪካ ቪዛ እንዲያገኙ አመቻችተዋል የሚል ነው።
ፖሊስ ጨምሮ እንደገለፀውም ኔታንያሁ ስጦታውን ከተቀበሉ በኋላ የአርኖን ሚልቻን ህግ እንዲፀድቅ ግፊት አድርገዋል ይላል።
ይህም ከአስራኤል ውጭ የሚኖሩ እስራኤላውያን ሀገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ ለአስር ዓመታት ከግብር ነፃ እንዲሆኑ ነው። ይህ ረቂቅም በገንዘብ ሚኒስትሩ ውድቅ ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ ከአውስትራሊያዊው ቢሊየነር ጄምስ ፓከር ጋር በተያያዘ በማጭበርበር እንዲሁም እምነትን በመጣስ ተከሰዋል።
የእስራኤሉ ቻናል 10 የተባለው ሚዲያ እንደዘገበውም ቢሊየነሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለባለቤታቸው ስጦታ እንደሰጡ ለመርማሪዎች እንደተናገሩ ነው።