ማኅበራዊ ሚዲያ፡ ፖሊስ ታዳጊዎች ራስን ስለማጥፋት የሚወያዩበት የኢንስታግራም ቡድንን አገኘ

የእንግሊዝ ፖሊስ ታዳጊ ሴት ልጆች ራስን ወደ ማጥፋት እንዲያመሩና በራሳቸው ላይ ከባድ ጉዳት እንዲያደርሱ የሚያበረታታ የማኅበራዊ ሚዲያ ቡድንን እንዳገኘ አስታወቀ።

ይህ ነዋሪነታቸው በደቡባዊ እንግሊዝ ውስጥ የሆኑ እድሜያቸው ከ12 አስከ 16 የሚደርሱ አስራ ሁለት ታዳጊ ሴቶች አባል የሆኑበት ስያሜው እራስን ከማጥፋት ጋር የተያያዘ የኢንስታግራም የውይይት ቡድን ነው ተብሏል።

ቡድኑ የተደረሰበት ከአባላቱ መካከል ሦስቱ ጠፍተው ለንደን ውስጥ ጤናቸው ክፉኛ ተቃውሶ ከተገኙ በኋላ ነው።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠው ኢንስታግራም የቡድኑ አባላት ይለዋወጧቸው የነበሩ መልዕክቶች የማኅበራዊ ሚዲያውን ደንብ የሚጥሱ አልነበሩም ብሏል።

ቢቢሲ ያገኘው ጉዳዩን በሚመለከት ፖሊስ ያደረገው የምርመራ ሰነድ እንደሚያመለክተው "የአቻ ተጽእኖ እራስን በማጥፋትና እራስ ላይ ከባድ ጉዳትን እንዲያደርሱ ታዳጊዎችን የሚያበረታታ ነው" ብሏል።

ይህ ቡድን መኖሩ የታወቀው አባላቱ በባቡር ለንደን ውስጥ ለመገናኘት ከተቀጣጠሩ በኋላ ሦስቱ ታዳጊ ሴቶች መጥፋታቸው ለፖሊስ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ነበር።

ጠፍተው የነበሩትን ታዳጊ ሴቶች ለማግኘት ፍለጋ ከተደረገ በኋላ ጤናቸው በአሳሳቢ ሁኔታ ተቃውሶ ጎዳና ላይ በፖሊስ የተገኙ ሲሆን ለአስቸኳይ ህክምና በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስደው ነበር።

አንደኛዋ ታዳጊ ለፖሊስ እንደተናገረችው የቡድኑ አባላት መጀመሪያ የተዋወቁት በኢንተርኔት አማካኝነት መሆኑንና ራስን ስለማጥፋት መነጋገራቸውን ገልጻለች።

ይህንንም ተከትሎ ፖሊሶች ቡድኑን ለመለየትና አባላቱን ለማወቅ በታዳጊዎቹ የማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀሚያ ቁሶች ላይ ምርመራ አድርጓል።

ፖሊስ ቡድኑ ላይ ከመድረሱ በፊት ከአስራ ሁለቱ አባላት መካከል ሰባቱ በራሳቸው ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

በተለያዩ ሰባት አካባቢያዊ መስተዳደሮች ስር የሚገኙ ለህጻናት የማኅበራዊ የጥበቃ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች የቡድኑ አባላት የሆኑ ታዳጊ ሴቶችን በመደገፍና በመንከባከብ በኩል ተሳትፎ አድርገዋል።

ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ታዳጊ ሴቶቹ የተዋወቁት በሌላ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ሲሆን፤ በኢንስታግራም ላይ ዝግ የሆነ ቡድን መስርተው በቀጥታ መልዕክት ይለዋወጡ ነበር።

የቡድኑ መለያ ስም ላይም ግልጽ በሆነ ሁኔታ "ራስን ማጥፋት" እና "መጥፋትን" የሚያመለክቱ ቃላትን ይጠቀሙ ነበር።

ባለፈው ኅዳር ወር ኢንስታግራም በገጹ ላይ የሚወጡ ራስ ላይ ጉዳት ማድረስንና ራስን ማጥፋትን የሚመለከቱ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች የሚለይ አዲስ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቆ ነበር።

የኢንስታግራም ባለቤት የሆነው ፌስቡክ የታዳጊ ሴቶቹ የኢንስታግራም ቡድን ስያሜ "ራስን ማጥፋትን" የሚያመለክት መሆኑን አረጋግጦ፤ ነገር ግን የቡድኑ አባላት የሚለዋወጧቸው መልዕክቶች የመድረኩን ደንቦች የጣሱ ስላልነበሩ እገዳ እንዳልጣለባቸው ገልጿል።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጉዳዩን አስመለክቶ ባወጣው መግለጫ ከፖሊስ ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑን አመልክቷል።

"የቀረቡልንን ሪፖርቶች መርምረን ራስን በማጥፋትና በመጉዳት ዙሪያ ያለውን የማኅበራዊ መድረኩን ደንብ የሚጥስ ጉዳይ አላገኘንም። አሰቃቂ ምስሎችን ወይም ራስ ላይ ጉዳት ማድረስን የሚያበረታቱ ይዘቶችን አንፈቅድም ከተገኙም እንዲነሱ ይደረጋሉ" ብለዋል።

ከክስተቱ ጋር በተያያዘም ለፖሊስ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉና ማንኛውንም መረጃ ለማግኘት ለሚቀርቡላቸው ሕጋዊ ጥያቄዎችም ምላሽ እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል።