ለቀናት ባሕር ላይ ቆመው የነበሩ መርከቦች በሱዊዝ ቦይ ማቋረጥ ጀመሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለማችን ዋነኛው የንግድ መርከቦች መተላለፊያ የሆነው የሱዊዝ ቦይን ዘግታው የነበረችው ግዙፍ መርከብ እንድትነሳ ከተደረገ ከአንድ ቀን በኋላ ለቀናት ቆመው የነበሩ መርከቦች ጉዟቸውን ጀመሩ።
በአሁኑ መተላለፊያው በተዘጋበት ጊዜ ወደ ማቋረጫው ገብተው ባሉበት ቆመው የነበሩ 37 የጭነት መርከቦች ቅድሚያውን አግኝተው እንዲያልፉ የተደረገ ሲሆን፤ ሌሎች 70 መርከቦች ደግሞ ዛሬ ማክሰኞ በሱዊዝ ቦይ በኩል ያልፋሉ ተብሏል።
የመተላለፊያው ባለስልጣናት የባሕር መስመሩ በተዘጋባቸው ባለፉት ቀናት ውስጥ ባሉበት ቆመው ለመጠበቅ ተገድደው የነበሩትን ከ300 በላይ መርከቦች አስተላልፎ ለመጨረስ ሦስት ቀን ተኩል ይፈልጋል ብለዋል።
ከእነዚህ መርከቦች መካከል ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ከሞሮኮ ማዳበሪያና ከቱርክ ደግሞ የተለያዩ ሸቀጦችን የጫኑ ሁለት መርከቦች በሜዲትራኒያን ላይ ቆመው እንደቆዩ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ለቢቢሲ መግለጹ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በመተላላፊያው የሚያቋርጡ መርከቦች ለባሕር ጉዞ ብቁ መሆናቸው በባለሙያዎች ይመረመራሉ ተብሏል።
400 ሜትር ርዝመትና 200 ሺህ ቶን የምትመዝነው ኤቨር ጊቭን የተባለችው መርከብ ባለፈው ማክሰኞ ጠዋት በመተላለፊያው በኩል እያቋረጠች ሳለ አሸዋ በቀላቀለ ከባድ ንፋስ ሳቢያ መስመሯን ስታ ነበር አግድም የባሕር ማቋረጫውን የዘጋችው።
መስመሩ ከተዘጋ ከሰባት ቀናት በኋላ በአሸዋ መቆፈሪያ ከባድ መሳሪያዎችና በጎታች ጀልባዎች እየተረዳች ግዙፏ መርከብ ተቀርቅራበት ከነበረው የባሕሩ ዳርቻ አሸዋ ውስጥ ሰኞ ዕለት ለማውጣት ተችሏል።
የሱዊዝ መተላለፊያ ቦይ በግብጽ ግዛት ውስጥ 193 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ የዓለማችን 12 በመቶ የንግድ ጭነት የሚያልፍበት መስመር ነው።
የባሕር ላይ መስመሩ የሜዲትራንያንና የቀይ ባሕርን በማገናኘት ከእስያ ወደ አውሮፓ የሚደረግን ጉዞ አጭር አድርጎታል።
በመተላለፊያው ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዳሉት እስከ ማክሰኞ ጠዋት ድረስ 306 መርከቦች ለማለፍ እየተጠባበቁ ናቸው።
ከእነዚህም ውስጥ 163 በቦዩ ደቡባዊ የቀይ ባሕር ክፍል ላይ ሲገኙ ቀሪዎቹ 137ቱ ደግሞ በሰሜን በኩል ሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
በሱዊዝ መተላለፊያ ቦይ በኩል ለማለፍ ተሰልፈው እየተጠባበቁ ያሉትን መርከቦች በማስተናገድ እንዲያልፉ ለማድረግ ረጅም ሠዓት የሚጠይቅ ሲሆን ሁሉም አልፈው እስኪያበቁ ድረስ ከሦስት ቀን በላይ እንደሚፈጅ ይጠበቃል።













