ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሸቀጦችን የጫኑ መርከቦች በሱዊዝ ቦይ መቆማቸው ተነገረ

መርከቧን ለማንቀሳቀስ ጥረት በተደረገበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, መርከቧን ለማንቀሳቀስ ጥረት በተደረገበት ጊዜ

ካለፈው ማክሰኞ ጠዋት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ለሚደርስ ጊዜ ተዘግቶ በቆየው የግብጹ ሱዊዝ መተላለፊያ ላይ ሁለት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ጭነት የያዙ መርከቦች መቆማቸውን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተለያዩ ጭነቶችን ይዘው በሜዲትራኒያን ባሕር በኩል ወደ ጂቡቲ በማምራት ላይ የነበሩ መርከቦች መተላለፊያው በመዘጋቱ ጉዟቸው ተስተጓጉሏል።

የሱዊዝ መተላላፊያ ቦይን ዘግታው የነበረችው ግዙፍ መርከብ ለመንቀሳቀስ እንዳትችል ካደረጋት የባሕር ዳርቻው አሸዋ ውስጥ የፊተኛ ክፍሏን ለቀናት በተደረገ ጥረት ዛሬ ለማውጣት ተችሎ አብዛኛው ክፍሏ በባሕሩ ላይ እየተንሳፈፈ በመሆኑ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ መርከቦች ወደ መድረሻቸው መጓዝ ይጀምራሉ ተብሏል።

ነገር ግን ከ350 በላይ ጭነት የያዙ መርከቦች በሁለቱም የመተላለፊያ መስመሩ ላይ ተሰልፈው በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸው መርከቦቹን ተራ በተራ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ሁለቱ መርከቦች ጭነታቸውን ይዘው ወደ ሱዊዝ ቦይ የደረሱት ረቡዕና ሐሙስ ዕለት እንደሆነ የገለጹት አቶ ሮባ ቢያንስ ለአምስት ቀናት ባሉበት ለመቆም መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሸቀጦችን ከጫኑት ሁለት መርከቦች መካከል አንደኛው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በኪራይ አገልግሎት የሚሰጥ የሌላ አገር መርከብ እንደሆነ ታውቋል።

አሶሳ የተባለችው መርከብ ከቱርክ የጥቁር ባሕር የተለያዩ ሸቀጦችን የያዙ ኮንቴይነሮችን ጭነት በመያዝ እየተጓዘች የነበረ ሲሆን፣ ሌላኛዋ የኪራይ መርከብ ደግሞ ከሰሜን ምዕራብ የአፍሪካ ጫፍ ከምትገኘው ከሞሮኮ በሜዲትራኒያን ባሕር በኩል ማዳበሪያ ይዛ በመምጣት ላይ እንደነበረች ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

መርከቦቹ የሚበላሽና ጊዜ የሚያልፍባቸው ሸቀጦችን እንዳልጫኑ የተናገሩት አቶ ሮባ መገርሳ ጭነቶቹን ለማራገፍ ከተያዘላቸው ጊዜ መዘግየት ውጪ ብዙም ችግር እንደማይገጥም ተናግረዋል።

እንዲህ አይነቱ መዘግየት ደግሞ በባሕር መተላለፊያዎችና በወደቦች ላይ ወረፋ የመጠበቅ ሁኔታ ሲኖር የሚያጋጥም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ነዳጅ በሱዊዝ ቦይ በኩል የሚያልፍ ባለመሆኑ በነዳጅ አቅርቦት ላይ እክል እንዳላጋጠመ የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጹ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ አብዛኛውን የነዳጅ ፍጆታዋን የምታገኘው ከመካከለኛው ምሥራቅ ከቀይ ባሕር ባሻገር ከሳዑዲ አረቢያ እና ከባሕረ ሰላጤዋ አገር ኩዌት ስለሆነ የሱዊዝ መተላለፊያ ላይ የተፈጠረው ችግር በአገሪቱ የነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ እንደሌለ ተገልጿል።

ኤቨር ጊቭን የተባለች ግዙፍ የጭነት መርከብ የጉዞ መስመሯን ስታ አግድም መተላላፊያውን በመዝጋቷ በዓለም ላይ በርካታ የንደግድ መርከቦች የሚተላለፉበትን ሱዊዝ ቦይን ዘግታ መቆየቷ ይታወሳል።

በዚህም ሳቢያ ከ367 በላይ የጭነት መርከቦች ማለፊያ አጥተው በመተላለፊያው ሰሜናዊና ደቡባዊ መግቢያ ላይ በመቆማቸው በየቀኑ 9.6 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች ወደ መድረሻቸው ለመሄድ ሳይችሉ ለቀናት ተስተጓጉለዋል።

አንዳንድ መርከቦችም ወደኋላቸው በመመለስ በደቡብ አፍሪካ በኩል ቀናት የሚፈጅ ጉዞን ለማድረግ መገደዳቸው ተነግሯል።

የመተላላፊያ መስመሩ በመዘጋቱ ሳቢያ ከባሕረ ሰላጤው አገራትና ከመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ወደ አውሮፓ የሚሄደው የነዳጅ አቅርቦት በመስተጓጎሉና ይህም ችግር ለሳምንታት ይዘልቃል ተብሎ ተሰግቶ ስለነበረ የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪን አስከትሏል።

ባለቤቷ ጃፓናዊ የሆነውና 200 ሺህ ቶን የምትመዝነው ግዙፏ ኤቨር ጊቭን መርከብ ባለፈው ማክሰኞ የሱዊዝ መተላለፊያን የዘጋችው በአካባቢው በተከሰተ ከባድ አሸዋ አዘል አውሎ ነፋስ ሳቢያ መስመሯን ስታ የፊት ክፍሏ አሸዋ ውስጥ በመስመጡ ነበር።

መርከቧ ጭነቷ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ከያዘችው መካከል 20 ሺህ ኮንቴይነር በማንሳት ክብደቷን ለመቀነስ እየተዘጋጁ ነበር። መርከቧን ከመተላለፊያው ለማንሳት የሳምንታት ሥራ ሊጠይቅ ይችላል ተብሎ ተሰግቶ ነበር።

የመተላለፊያውን መከፈት ከሚጠብቁት ከ350 በላይ መርከቦች መካከል ጥቂቱ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የመተላለፊያውን መከፈት ከሚጠብቁት ከ350 በላይ መርከቦች መካከል ጥቂቱ