ከእስር ቤት ያመለጠው የናይሮቢ የቀድሞ አገረ ገዢ

ማይክ ሶንኮ ይባላል። ማይክ ሶንኮ ረዥም ስም ነው። ደጋፊዎቹ ረዥም ነገር አይወዱም። ስለዚህ ሶንኮ ይበቃል።

ትምህርት የለውም ሶንኮ። ዲግሪ የለውም ሶንኮ። ደጋፊዎቹ ትምህርትም ዲግሪም አይስጨንቃቸውም።

ከእስር ቤት ያለፈ ታሪክ የለውም ሶንኮ። ደጋፊዎቹም ታሪክ አይወዱም።

ሶንኮ በኬንያ ዝነኛ ስም ነው። ምናልባት ኡሁሩ ኬንያታ ወይም ራይላ ኦዲንጋ ሊበልጡት ይችላሉ።

ቀጥሎ የሚመጣው ስም ግን ያለጥርጥር ሶንኮ የሚለው ነው። ጉግል ራሱ እንደ ሶንኮ በደንብ የሚያውቀው የኬንያዊ ስም የለም።

ሶንኮ ወጣት ነው። አሁን የጎልማሳ ዕድሜ ቀጠና ውስጥ ገብቷል። ዕድሜ ቁጥር ነው። ዋናው እሱ ራሱን እንዴት ያያል የሚለው ነው።

ሶንኮ ነገረ ሥራውም አስተሳሰቡም የጎረምሳ ነው። የ30ዎቹ ነገር አንድም አይታይበትም።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአፍሪካ ሸቅርቅረዋ ከተማ የናይሮቢ ገዥ ነበር። በቀደም ነው ተጎትቶ የወጣው።

ቢሮ አልለቅም ብሎ በስንት ትግል፣ በስንትና ስንት ፖሊስ ነው የወጣው። ሶንኮ የራሱ ፖሊስ አለው። ሰንሰለት እጁ ላይ ሊያጠልቁለት የነበሩ ፖሊሶችን ነክሷቸው ዜና ሆኖ ነበር። እሱን ማሰር በራሱ ፈተና ነበር።

ሶንኮ ሳይታሰብ ለሽቅርቅሯ ናይሮቢ ገዢ ሆነ። የናይሮቢ አውራጃ ከንቲባ እንደማለት ነው ገዢ። ፈላጭ ቆራጭ ነው ገዢ።

እሱም ሽቅርቅር፣ ናይሮቢም ሽቅርቅር።

ናይሮቢ አሁን ገና የሚመጥናትን ገዢ አገኘች ተባለ፤ ሶንኮ ወደ ፖለቲካ የመጣ ሰሞን።

እውነት ለመናገር ሶንኮ ምኑም የአንድ ግዛት ገዢ (Governor) አይመስልም።

ማንም ሰው ገና እንዳየው "የት ክለብ ነው ዲጄ የምትሰራው?" ብሎ ሊጠይቀው ይችል ይሆናል እንጂ ክቡር ከንቲባ/ገዢ ሊለው? በፍጹም!

ሲጀመር እንደ ጎረምሳ ሎቲ የሚያንጠለጥል የአገረ ገዢ ከየት መጥቶ ያውቃል?

አንገቱን ለማየት ሰንሰለቶቹን መፈልቀቅ ያስፈልጋል። ኮፍያ ቀኝ ወደኋላ አዙሮ በቄንጥ ነው የሚያጠልቀው።

ቀበቶውን ከራፐር '50 ሴንት' የተዋሰው ነው የሚመስለው። ሶንኮ ምኑ አገረ ገዢ ይመስላል?

መሸታ ቤት እያዘጋ በአስረሽ ምቺው ነግቶበት ነው ቢሮ የሚገባው ይሉታል የናይሮቢ ሐሜተኛ ጋዜጦች።

የተከበሩ የናይሮቢ አገረ ገዢ ሶንኮ ሎቲ ብቻ አይደለም መለያው።

ቅንጡ የእጅ አንባሩ፣ አሎሎ የሚያካክሉ የነጠሩ የጣት ቀለበቶቹ ወዘተ ነጥሮ እንዲታይ አድርገውታል።

ደረቱ ላይ ያጠለቀው የሃብታም ውሻ መጎተቻ የሚመስለው የወርቅ ሰንሰለቱ ብቻውን በናይሮቢ ውስጥ ካሉ ውድ የመኖሪያ አካባቢዎች የተንጣለለ የመኖሪያ አፓርትመንት አይገዛም?

ሶንኮ ሃብታም አገረ ገዢ ነው። ወይም ነበር። አሁን የፍርድ ቤት ክስ ተከምሮበት አብዛኛው ጊዜውን በጆሮ ማዳመጫ የትዝታ ራፕ ሙዚቃ እያዳመጠ ነው የሚውለው። ራፕ ትዝታ የሚባል ቅኝት ካለው።

አስደናቂው ሶንኮ፣ 'ዱርዬው አገረ ገዢ' የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል። ለምን ብለን ከጠየቅን የሚከተለው ታሪኩን ማንበብ ይኖርብናል።

ከወንጀለኝነት እስከ እንደራሴነት

ሽቅርቅሩ ሶንኮ አሁን የተከሰሰበት የወንጀል ዶሴ ቢሸከሙትን ቢያነቡትም አታካች ነው።

አላግባብ ገንዘብ ወጪ ከማድረግ ጀምሮ በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማድረግ፣ በሥልጣን መባለግ እንዲሁም የሽብር ክስን ያካትታል።

ከሥልጣን የወረደበት መንገድ ልክ እንደ አወጣጡ ድራማ የሚመስል ነበር።

ሶንኮ አልተማረም።

እርግጥ ነው 2ኛ ደረጃ ትምህርቴን በጥሩ ውጤት ጨርሻለሁ ይላል። ብዙ ሰው ግን አያምነውም። ደጋፊዎቹ ግን እንዲያውም 'በትምህርት መግፋቱ' ያበሳጫቸዋል። ይሄ ሁሉ ትምህርት ምን ይሰራልሃል ሳይሉት አይቀሩም።

በጭርንቁስ የናይሮቢ ሰፈሮች ሶንኮ ተወዳጅ ነው። እነሱም ናቸው ድምጽ ሰጥተው ምክር ቤት ያስገቡት።

ሶንኮ ብዙ ሚኒባስ ታክሲዎች (ማታቱ) አለው። ረዳትና ሾፌር እየቀጠረ ያሰራል። ብዙዎቹ ታክሲዎች መስመራቸው ወደነዚህ ጭርንቁስ ሰፈር ነው። ወደ ቡሩቡሩ ሰፈር፣ ወደ ኪቢራ የጭቁኖች መንደር።

የእሱን ታክሲ የሚነዱ ሾፌሮችና ረዳቶች አለባበሳቸው እንደሱ ነው። ከእሱ የሚለዩት በትንሹ ነው። ለምሳሌ የእሱ ሀብል ወፍራም ወርቅ ሲሆን የእነሱ ደግሞ ቀጭንና አርቴፊሻል ነው። በአስተሳሰብ ግን ከእሱ አይለዩም። ከድህነት ትልቅ ቦታ መድረስ ይቻላል ብለው ያስባሉ።

ማይክ ሶንኮ እውነተኛ ስሙ አይደለም። አባት እናቱ ያወጡለት ስም ጌዲዮን ኪዮኮ ነበር።

ሶንኮ ማለት በስዋሂሊ የአራዳ ቋንቋ፣ "ሞጃ፣ የናጠጠ፣ ፈረንካ ያለው፤ ሽቅርቅር" እንደማለት ነው።

ሞምባሳ የተወለደው ሶንኮ ስለልጅነቱ ዘርዘር ያለ መረጃ የለም። ምናልባት በድህነት ነው ያደገው። አባቱ ግን ጎበዝ የሪልስቴት ደላላ ነበሩ ይባላል።

ድንገት ሶንኮ ሚሊየነር ሆነ። በኬንያ ሰው እንዴት ሀብት አፈራ ተብሎ አይጠየቅም። በቃ ሃብታም ሆነ። ተቃዋሚዎቹ "አደገኛ ዕጽ ቸብችቦ ነው" ይሉታል። እሱ ግን ጥሬ ግሬ ላቤን አንጠፍጥፌ ያመጣሁት ነው ይላል።

ይህን ገንዘቡን ታዲያ ድሆች ሰፈር ሄዶ መርጨት ጀመረ። ለተሰበሰበው ሰው ረብጣ ሽልንግ ወደ ሰማይ ሻሞ እያለ ይበትን ጀመር። የናይሮቢ ጭርንቁስ ሰፈር ነዋሪዎች ወደዱት።

የዚያ ሰፈር ልጆች ሶንኮ መጣ እያሉ መጨፈር ጀመሩ። በዚያው ወጣት ጌዲዮን ስሙ ሚስተር ሶንኮ ሆኖ ቀረ።

አሁን ጌዲዮንን ማንም አያውቀውም። ሶንኮን ግን መላ ናይሮቢያዊያን ያውቁታል። ከሊቅ እስከ ደቂቅ።

ስለ ሶንኮ የቀድሞ ሕይወት ብዙም አይታወቅም ነበር።

የሰው ምስጢር አውጥተው ያሰጣሉ የሚባሉት ቦርቧሪ የኬንያ ጋዜጦች ራሱ የሶንኮን የኋላ ታሪክ ማግኘት ተቸግረዋል።

ሆኖም ዘግይቶ አንድ መረጃ አፈተለከ።

እንደአውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ ሶንኮ ከአንድ መሬት ካርታ ጋር በተያያዘ ሰነድ አጭበርብሮ ታስሮ ነበር። ዘለግ ያለ እስርም ተፈርዶበት ነበር። ድንገት ግን ከእስር አመለጠ።

መጀመሪያ በሳምሶናይት ገንዘብ ወደ እስር ቤቱ አሾልኮ አስገባ። ከዚያ ገንዘቡን ለእስር ቤቱ ጠባቂዎች አሳያቸው። ባዩት ነገር ነሆለሉ። "እነሱ ተባብረውኝ ነው ያመለጥኩት" ብሏል ሶንኮ ቅንጣት ታህል እንኳ ሀፍረት ሳይሰማው።

ከዚያ በኋላ በድጋሚ ተይዞ ታሰረ። ብዙም አልቆየም። በዚያም በዚህም ብሎ በምህረት እንዲፈታ አስደረገ።

ከእስር ቤት እንደወጣ ማን ይቻለው። ቢዝነሱ ደራለት።

መጀመሪያ ማታቱ ገዛ። ማታቱ ማለት በኬንያ የጭቁን ሕዝብ ታክሲ ማለት ነው። "ሃይገር ባስ" እንደማለት ነው። ልዩነቱ ማታቱዎች ቴሌቪዥን ከፍተው የሙዚቃ ድምጻቸውን ካለልክ ከፍተው በጠራራ ፀሐይ መሸታ ቤት መስለው ነው የሚጓዙት።

እዚህ "ማነህ ሾፌር ድምጹን ቀንሰው!" ማለት አይቻልም።

በኬንያ ማታቱዎች ውስጣቸው ብቻ አይደለም የሚጮኸው። የመኪኖቹ ውጫዊ አካላቸውም በቀለም ያበደ ነው።

ሶንኮ በርከት ያሉ ማታቱዎችን ገዝቶ ወደ ቡርቡሩና ወደ ኪቢራ ጭርንቁስ ሰፈር ካሰማራቸው በኋላ አዱኛ ዘነበለት። ከ50 በላይ ማታቱዎች ነበሩት።

እነዚህ ማታቱዎች መሀል ከተማ እንዳይገቡ የሚል ሕግ ወጣ። ሶንኮና ባለማታቱዎች አበዱ። የማታቱ ታክሲ ማኅበር ፕሬዝዳንት ነበር ያን ጊዜ ሶንኮ።

ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወሰደውና አሸነፈ። ማታቱ ታክሲዎች መሀል ከተማ ገብተው መሥራት መብታቸው ነው ተባለ። ረዳትና ሾፌር ሶንኮን ንጉሥ አደረጉት።

ወዲያው ውድ የምሽት ክለብ ከፈተ። ካፌ፣ ሬስቶራንት፣ ቡቲክ መቆመርያ ቤት ሁሉም አለው። ከዚያ ሪልስቴት ውስጥ ገባ። ከዚያ ገንዘቡ ከቁጥጥሩ ውጭ ሆነ። ምን ቀረው?

ገና ወጣት ነው። ለምን ፖለቲካ ውስጥ አልገባም ብሎ አሰበ። በኬንያ ፖለቲከኛ ሆኖ ድሀ መሆን አስቸጋሪ ነው።

ፖለቲከኛ መሆን ልክ አዲስ የገበያ አዳራሽ የመክፈት ያህል ነው። 'እንዴት ያለ የሚያበላ ሙያ መሰለህ' ይሉታል አንዳንዶች፤ ፖለቲከኝነትን።

ሶንኮ ዕድሜው 35 ሲደርስ በ2010 መሆኑ ነው፣ የከተማዋ ምክር ቤት ገባ። ከሦስት ዓመት በኋላ ሴናተር ሆነ። በ2017 ደግሞ የናይሮቢ ገዢ ሆኖ ተመረጠ።

ምርጫ ላይ ለሕዝቡ ያልገባው ቃል አልነበረም። ናይሮቢን ገነት አደርጋታለሁ፤ ሕዝቧም ተንደላቆ በፍሰሐና በደስታ ይኖራል ሲል አወጀ።

እርግጥ ብዙ ሰዎች የምርም ተስፋ ጥለውበት ነበር።

የሕዝብ ልጅ ነው፤ የሕዝቡ ችግር ይገባዋል ብለው አስበውም ነበር። በወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች የተሰላቹ ወጣቶች አፈንጋጩን ሶንኮ 'ወርቁ ልጃችን' ሲሉትም ነበር።

እንዲያ ያሉት በወርቅ ስለተንቆጠቆጠ አልነበረም። ለወጣቱ መንፈስ ቅርብ ስለነበረ ነው።

ሌሎች ነዋሪዎች ግን ይሄ የጎረምሳ መንፈስ አስፈርቷቸው ነበር።

"አንደኛ ይሄ ሰው ትምህርት የለው፤ ሁለተኛ ግብረገብነት የለው፤ እንዴት ነው ናይሮቢን የሚያክል ውስብስብና ግዙፍ ከተማን የሚመራው?" ሲሉ ፍርሃትና ስጋታቸውን አስተጋቡ።

ሶንኮም የዋዛ አልነበረም። ይህን ያለበትን የትምህርትና የዕውቀት ችግር ለመሸፈን የቀድሞ የነዳጅ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ የነበሩ ዕውቅ ሰው ምክትሉ አድርጎ ሾመ።

የሶንኮ አወራረድ

በዚህ ዓመት ታኅሣሥ ወር ሶንኮ ችግር ውስጥ ገባ። ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም ክስ ተመሰረተበት።

እንደሚባለው ከሆነ የሶንኮ ዋና ጽህፈት ቤት የገባ ሰው ሚሊዮን ሺሊንግ በኪሶ አጭቆ ነው የሚወጣው። በየአካባቢው እሱን ለሚደግፉ ብር ይረጫል ይሉታል።

ተጠያቂነት የሚባል ነገር አልነበረም። የግል ጋዜጦች ሶንኮ ላይ ክፉ እንዳይጽፉ ማስፈራሪያም ማባበያም ነበር የሚቸራቸው።

ክሶቹ በየዕለቱ እየጨመሩ ሄዱና በመጨረሻም ከሽብር ጋር ተያያዙ።

ክሶቹ እንደሚያሳዩት ሶንኮ ወዳጅ ዘመዶቹን ሚሊዮነር ሲያደርግ ነው የኖረው። ብዙ ሃብትና ንብረት ሳይመዘብር አልቀረም።

አንድን የናይሮቢ መንገድ አሰራለሁ ሲል ያውጃል። በፍጥነት በጨረታም ያለጨረታም ለጓደኞቹ ኮንትራት ይሰጣል። ገንዘቡ ከከተማው ካዝና ወጪ ያስደርጋል።

ጓደኞቹ መንገዱን እንደነገሩ ሠርተው ገንዘቡን ወደ ሶንኮ ሒሳብ ያዘዋውራሉ። በዚህ መንገድ 300 ሚሊዮን ሺሊንግ መዝብሯል ነው የሚባለው። ገና ክሱ እየታየ ስለሆነ ለጊዜው ወንጀሉን እሱ ላይ ባንደፈድፍ ይሻላል።

በቅርቡ ደግሞ ሚሊሻ መልምሎ በማስታጠቅ፤ ከዚያም ደግሞ የወታደር ልብስ አሰፍቶ የራሱን ሠራዊት ሲያደራጅ ነበር ተብሏል። ከሽብር ጋር ግንኙነት ላላቸው አማጺ ቡድኖችም ይህን የደንብ ልብስ ንግድ ይነግዳል፤ ዕቃ ያቀርባል የሚል ውንጀላም ቀርቦበታል።

ሶንኮ ግን እነዚህ ክሶች በሙሉ ፖለቲካዊ ናቸው ይላል። እኔን ከፖለቲካው ገለል ለማድረግ የተቀናበሩ ናቸው ሲል ፍርድ ቤት ቀርቦ በውድ መሀረብ እንባውን እየጠረገ ተናግሯል።

ፕሬዝዳንቱ በ"ላውድ ስፒከር"

ሶንኮ ያልተለመዱ ነገሮችን በማድረግ ስሙ ገናና ነው። የኬንያ ጋዜጦች እሱን ከፊት ዜና ካላደረጉ ዜና የሰሩ ሁሉ አይመስላቸውም።

በ2014 ዓ.ም የኬንያ ባለሥልጣናት ሕገ ወጥ ግንባታ ናቸው በሚል በወንዝ ዳርቻ የተገነቡ ቤትና ሱቆችን ማፍረስ ጀመሩ። በርከት ያሉ መኖርያ ቤቶችና የንግድ ማዕከላትን በቡልዶዘር አፈራረሱ።

የከተማው ሕዝብ ለሁለት ተከፈለ። ከፊሉ የወንዝ ዳርቻ ግንባታ ሕገ ወጥ ነው ደግ አደረገ ሲሉ ሌሎች ደግሞ እንዴት ሚሊዮን የተከሰከሰበት ሕንጻ ከወንዝ ተጠግቷል ተብሎ ይፈርሳል በሚል ተከራከሩ።

ድርጊቱ ቀጠለ። ሶንኮ አይደለም የሚያስፈርሰው። የአገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር ነበር።

ይህ ሲሆን በርካታ ሰዎች ድርጊቱን ተሰብስበው ይመለከቱ ነበር። የሚፈርሰውን ንብረታቸውን ሊከላከሉ አልቻሉም። ምክንያቱም በፖሊስ ታጅቦ ነበር የማፍረስ ሥራው ሲካሄድ የነበረው።

በዚህ ጊዜ ድንገት ሶንኮ ከእነ አጀቡ በወርቅ ሀብል ተንቆጥቁጦ ተከሰተ። ያኔ ሶንኮ የከተማው ሴናተር ነበር።

ሰዎች እሱን ሲያዩ ግር ብለው ከበቡት።

ይሄን ሕገ ወጥ ተግባር አሁኑኑ ለፕሬዝዳንቱ አሳውቃለሁ ብሎ ስልክ ደወለ። የተሰበሰቡት ሰዎች ተደናገሩ። ግማሾች ውሹቱን ነው ጉረኛ አሉት፤ ሌሎች ከቁምነገርም አልቆጠሩትም ነበር።

ሶንኮ ግን የዋዛ አልነበረም። ስልኩ ጠራ። ቀጥታ ወደ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ነበር የደወለው። የምርም ስልኩ ተነሳ።

"ክቡር ፕሬዝዳንት፣ አወቁኝ? ሶንኮ ነኝ። እዚህ ባሎዚ ሪልስቴት አካባቢ ነኝ። በቢሊዮን ሽሊንግ የሚገመቱ ቤቶች እንደዋዛ እየፈረሱ ነው። እዚያ ሆኜ ነው የምደውልልዎ።"

"ማነው የሚያፈርሳቸው?" ፕሬዝዳንቱ ኮስተር ብለው ጠየቁ።

"የግብርና ሚኒስቴር ነው እያፈረሳቸው ያለው። ደብዳቤ ብጽፍላቸውም አልሰሙኝም። እባክዎ አንድ ነገር ያድርጉ።"

ፕሬዝዳንቱ ኡሁሩ ኬንያታ ድርጊቱን እንደሚያስቆሙ ተናግረው ስልኩን ዘጉት።

እንዳሉትም ፕሬዝዳንቱ ወዲያውኑ የማፍረስ ተግባሩ እንዲቆም አደረጉ።

ይህን ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ጋር የነበረውን የስልክ ልውውጣቸው ሶንኮ በቀጥታ ለሕዝቡ በድምጽ ማጉያ እያሰማ ነበር።

ሰዎች ተደነቁ። እንዴት ፕሬዝዳንቱ ጋር ስልክ ደውሎ ተነሳለት፡፡ እንዴትስ 'ላውድስፒከር' ላይ ለማድረግ ደፈረ?

ሶንኮ ስልኩ እንደተዘጋ ወደ ሕዝቡ ዞሮ እንዲህ አለ።

"አላልኳችሁም? ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ጓደኛዬ ነው። ላውድስፒከር ላይ ያረኩት ስለምተማመንበት ነው። በዓለም ላይ እንደሱ ስልክ የሚያነሳ ፕሬዝዳንት የለም።"

ሎቲ የሚያንጠለጥለው የሕዝብ እንደራሴ

ሶንኮ ፖለቲካን የጀመረው በ2010 ነበር። የማሟያ ምርጫ ላይ ተሳትፎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳደረ። በቀላሉ አሸነፈ።

ከዚያ በፊት የሚያውቀው ሰው አልነበረም። ነገር ግን ለየት ያለ አለባበሱና አፈንጋጭነቱ ቶሎ ወደ ዝና ማማ ሰቀሉት።

በ2011 አዲስ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆኖ ፓርላማ ሲገባ ደረቱ በወርቅ ሰንሰለት፣ ጣቶቹ በወርቅ ቀለበት ተንቆጥቁጠው ነበር። ጆሮውን ተበሳስቶ ሎቲ ደርድሮበታል። በዚህ ላይ ደግሞ ጥቁር የዝነጣ መነጽር አጥልቋል።

የከተማው ፓርላማ ሲከፈት እንደራሴዎች ደነገጡ። ይሄ ራፐር እዚህ ምን ይሰራል ሲሉም ጠየቁ። ከፓርላማ በዘበኛ ተጎትቶ ወጣ።

ያን ጊዜ ሶንኮ ለቢቢሲ እንደተናገረው በሥልጣን ዘመኑ የአለባበስ ሥነ ሥርዓት እንዲቀር እታገላለሁ፤ እኔ የምወክለው ወጣቱን ነው። ይህን ሕግ አስቀይራለሁ ብሎ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ሳያሳከው ቀረ እንጂ።

የከተማ ምክር ቤት ከገባ በኋላ አስገራሚ ድርጊቶች ላይ ተሳትፏል። ተቃውሞ ሲኖር ቶሎ ከሕዝብ ጋር ይሰለፋል። መንገድ ላይ ከሕዝቡ ጋር ለተቃውሞ ይንከባለላል። ግድግዳና መስታወት በቡጢ ይነርታል። የአደባባይ ተቃውሞዎች ነፍሱ ነበሩ።

ሶንኮ ሌላው ባህሪው ከባለሥልጣናት ጋር ያደረገውን የግል የስልክ ንግግር ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማስጣቱ ነበር። ከሆነ ጊዜ በኋላ ባለሥልጣናት የእሱን ስልክ ማንሳት ፈርተው ነበር።

ስብሰባም ላይ ሆነ የኢመደበኛ ንግግሮችን መነጽሩ ሥር ማይክ ቀብሮ ይቀዳል። ቀለበቱም ምስጢራዊ መቅጃ መሣሪያ ተገጥሞላታል እየተባለ ይወራ ነበር።

ከሰዎች ጋር በወዳጅነት ያወራውን ወሬ በሙሉ ለሕዝብ ይዘረግፈዋል። የኋላ ኋላ ከእሱ ጋር የሚገጥም ፖለቲከኛ እየጠፋ መጣ።

ሶንኮ በሌላ ጉዳይም ይታወሳል።

በቅርቡ ከሥልጣን ከመውረዱ በፊት ኮሮናቫይረስ ኬንያ ሲገባ ሶንኮ 'ሔነሲ ኮኛክ' መጠጥ ከምግብ ጋር ለተቸገሩ የናይሮቢ ነዋሪዎች እንዲታደል አደረገ።

ለምን እንደዚህ ታደርጋለህ ሲባል "አልኮል ኮሮናቫይረስን የማጥፋት ኃይል እንዳለው አረጋግጫለሁ" ሲል መለሰ።

የዓለም ጤና ድርጅት ግን አልኮል የበሽታ መከላከል አቅምን እንደሚቀንስ ነው የሚናገረው። ሶንኮ የዓለም ጤና ድርጅትን የሚሰማ ሰው አይደለም።

በ2012 የኬንያ የአስተዳደር ፍትሕ ኮሚቴ ተቋቋመ።

ይህ ኮሚቴ በሕዝብ የአግልግሎት ቅሬታዎችን የሚቀበልና ባለሥልጣናትን ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። ይህ ኮሚቴ "ሶንኮን ለዚህ ስልጣን የማይመጥን" ብሎት ነበር።

ሶንኮ ግን አልተቀበለውም።

"እርግጥ ነው እኔ የቀድሞ ከባድ ፍርደኛና እስረኛ ነበርኩ። አሁን ደግሞ የናይሮቢ ከባዱ ገዢ ነኝ" ሲል ተናግሯል።

'ልጁ ጉራ ብቻ ነው'

ናይሮቢን ገነት አደርጋታለሁ ሲል የፎከረው ሶንኮ የከተማዋውን አስተዳደር አመሰው። ይህን ጊዜ ብቁ ባለሙያዎች ሥልጣን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቅ ጀመሩ።

"ሶንኮ መደበኛ አስተዳደር እንዴት መሆን እንዳለበት አያውቅም" ይላሉ ሴናተር ኢሳክ መዋኑራ።

በመጨረሻ ነገሮች ሁሉ ከቁጥጥሩ ውጪ ሆኑበት። በዚህ ጊዜ ዋና ዋና የከተማዋ አገልግሎቶች በማዕከላዊው መንግሥት በተቋቋመው የናይሮቢ ከተማ አገልግሎት በተባለ ቢሮ በኩል እንዲከወኑ የሚያደርግ ስምምነት ተገዶ ፈረመ።

ይህን ተከትሎ ፍርድ ቤት ሶንኮ በምንም መልኩ ቢሮ እንዳይገባና የመንግሥትን ካዝና እንዳይጠጋ አገደው።

ሶንኮ ሙሉ ሥልጣኑን አሳልፎ ላለመስጠት ብዙ ታግሏል። ፕሬዝዳንቱ ጣልቃ ገብተው ከተማዋን ከሶንኮ እጅ በማውጣት ላቋቋሙት ቢሮ በመስጠታቸው አሁን በዚህ መልኩ ናይሮቢ እየተተደዳረች ነው።

"ወዳጄን ሶንኮን ነግሬዋለሁ። ማንኛውንም እገዛ ከፈለክ አለሁልህ ብዬው ነበር። እሱ ግን ቅንጡ መነጽር አድርጎ መንቀባረር ብቻ ሆነ ሥራው" ብለውታል ፕሬዝዳንት ኡሁሩ።

ፕሬዝዳንቱ በመጨረሻ ዘናጩን ሶንኮን ከእነ ዝነጣ መነጽሩ ከሥልጣኑ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ አድርገዋል።

ሶንኮ አሁን ምንም የሚያደርገው ነገር የለም።

በዋስ ከእስር ወጥቶ ፍርድ ቤት መመላለስ ሆኗል ሥራው። ለሸክምም ለንባብብ አታካች የሆነውን የክስ ዶሴውን ለማንበብ ግን በቂ ጊዜ አግኝቷል።

ክሱን ጥቁር የዝነጣ መነጽሩን ሳያወልቅ እያነበበ ነው፤ ጠዋት ማታ። ነጋ ጠባ።