ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የናይሮቢው ገዢ ለችግረኞች አልኮል ጭምር አቀርባለሁ አሉ
የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ላልቻሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ጋር አብሮ መጠጥ ሊያቀርብ እንደሆነ የከተማው ገዢ መናገራቸው መነጋገሪያ አድርጓቸዋል።
አገረ ገዢው ማይክ ሶንኮ ይህንን የተናገሩት ማክሰኞ ዕለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነበር።
ሶንኮ "አነስተኛ ጠርሙስ ሄኒሴ [የኮኛክ መጠጥ ዓይነት ነው] በምግብ እድላው ላይ ጨምረን ለሕዝባችን እናቀርባለን" ማለታቸው ተሰምቷል።
የከተማዋ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በዚህ የአገረ ገዢው ንግግር ሲሳለቁ ተስተውሏል።
አገረ ገዢው አክለውም "በዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ በሌሎች የጤና ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አልኮል ኮሮናቫይረስንም ሆነ ሌሎች ቫይረሱችን ይገላል" ብለዋል።
በአገሪቱ በሚሰራጨው ሲትዝን ቲቪ የአገረ ገዢው አስተያየት ተደምጧል።
የመዲናዋ ናይሮቢ ገዢ በተናገሩት ነገር ላይ በርካታ ኬንያዊያን በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ እየተሳለቁበት ነው።
በሚያደርጉት ንግግርና በድርጊታቸው ውዝግብ ውስጥ በመግባት አዲስ ያልሆኑት ገዢው፤ ቀደም ሲል እሳቸው ቢያስተባብሉትም በዕፅ ማዘዋወርና ሕገ ወጥ ገንዘብ ወደ ሕጋዊነት በማስገባት ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
በተጨማሪም የአገሪቱ እስር ቤት ባለስልጣናት የአሁኑ የናይሮቢ ገዢ ከ20 ዓመታት በፊት ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት አምልጠዋል ብለው ይከሷቸዋል።
ባለፈው ታኅሳስ ወር ፍርድ ቤት የከተማዋ ገዢ 3.3 ሚሊዮን ዶላር አባክነዋል በሚል ወደ ጽህፈት ቤታቸው እንዳይገቡ መከልከሉን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በየካቲት ወር የከተማዋን ቁልፍ ኃላፊነቶች የአገሪቱ መንግሥት ወስዶ እንዲያስተዳድር አድርገዋል።
ነገር ግን ይህም ቢሆን ማይክ ሶንኮ ምንም አይነት መጥፎ ተግባር አልፈጸምኩም ብለው ይከራከራሉ።
የኬንያ ማዕከላዊ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ የናይሮቢ ከተማን የጤና፣ የትራንስፖርትና ሌሎች የሕዝብ አገልግሎቶችን ሥራ ተረክቦ እያከናወነ ይገኛል።