ኬንያ፡ አራስ ልጅ የሚሸጡባቸው የናይሮቢ ጉሊቶች- ልዩ የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ

በኬንያ መዲና ናይሮቢ ሕጻናት ይሸጣ። ልክ እንደ ኩንታል ስንዴ። ለዚያውም በጥቁር ገበያ ነው የሚቸበቸቡት። የቢቢሲው የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን ይህንን አሰቃቂ የሕጻናት የገበያ ሰንሰለት ደርሶበታል። የአንድ ሕጻን ዋጋም በአማካይ 300 ፓውንድ መሆኑን ተረድቷል።

የርብቃን ልጅ ያያችሁ!

የርብቃ ልጅ 10 ዓመት ይሆነዋል። የት እንዳለ እናቱ ርብቃ አታውቅም። ናይሮቢ ውስጥ ሊሆን ይችላል። አውሮፓም ሊሆን ይችላል። አውስራሊያም ሊሆን ይችላል። ብቻ የሆነ ቦታ ግን አለ።

አይበለውና ሞቶም ሊሆን ይችላል። እንዲያውም እናቱ ርብቃ ውስጧ የሚነግራት እንደዚያ ነው። "የሞተ የሞተ ይመስለኛል" ትላለች እንባ እየተናነቃት። እርሟን ግን አላወጣችም። ማውጣትስ ትችላለች? እንዲያውም የ10 ዓመት ልጅ በናይሮቢ ጎዳና በሀብታም ቤተሰቦች ታጅቦ ስታይ ልቧ ይርዳል። የእኔው ሎውረንስ ቢሆንስ? ትላለች።

ርብቃ መቼ ነው ልጇን ለመጨረሻ ጊዜ ያየችው ቢባል የዛሬ 9 ዓመት አካባቢ ነው መልሷ። ገና አንድ ዓመቱ እያለ ነው ከእጇ ያመለጠው። ያኔ እሷ 16 ዓመቷ ነበር። ያን መጥፎ ሌሊት አትረሳውም።

መጋቢት 2011 ዓ.ም። ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት አካባቢ ነበር። ርብቃ ጎዳና ነበር የምትኖረው። ብርዱ እንዳይሰማት ቤንዚን ስባ ነበር የተኛችው።

ርብቃ ይሄን ቤንዚን የምታጨሰው ድፍረት ለማግኘት ነው። አለበለዚያ ሰዎችን ሄዶ መለመን ያሳፍራታል።

ልክ 15 ዓመት ሲሞላት እናቷ የትምህርት ቤት መክፈል አቃታቸው። እሷን ማኖር አቃታቸው። ከቤት ወጣች። የጎዳና ልጅ ሆነች። ከዚያ የሆነ ትልቅ ሰውዬ "እረ ጣጣ የለም፤ እኔ አገባሻለው" አላት። ደስ ብሏት አብራው ሆነች። እንዳረገዘች ሲያውቅ ጠፋ።

የበኩር ልጇ ሎውረንስ ታዲያ ከዚህ ትልቅ ሰውዬ የወለደችው ነው። ጥሏት ከጠፋው ሰውዬ።

እና በዚያች መጥፎ ሌሊት ምን ሆነ? በቤንዚኒ በ'ጦዘችበት' እንቅልፍ ይዟት እልም። ሞተ የመሰለ እንቅልፍ።

ስትነሳ ልጇ ከእቅፏ የለም። ገና 1 ዓመቱ ነበር ያኔ።

ለ9 ዓመታት ፈለገች። አስፈለገች። የትም የለም። ያልሄደችበት የልጅ ማሳደጊያ፣ ያልገባችበት ፖሊስ ጣቢያ የለም። ኪያምቦ፣ ካዮሌ፣ ሞያሌ…ሎውረንስ ከየት ይገኝ? እምጥ ይግባ ስምጥ አልታወቀም።

ርብቃ ከዚያ በኋላ ሌሎች ልጆችን ወልዳለች። የሎውረንስ ነገር ግን ያንገበግባታል። "ለመጀመርያ ጊዜ እናት ያደረገኝ እኮ እሱ ነው። እወደዋለሁ፣ እናፍቀዋለሁ" ትላለች።

ርብቃ አሁንም ጎዳና ነው ቤቷ። 3 ልጆችን ወልዳ የጎዳና ሕይወቷን አጠናክራ ቀጥላበታለች።

ርብቃ በድጋሚ ልትሰረቅ ነበር?

የሚገርመው ከ3ቱ አዳዲስ ልጆቿ ጋር ጎዳና እየኖረች አንድ ቀን ጨቅላዋን ልጇን አንድ ሰውዬ ብድግ አድርጎ አቀፋት።

ሰውየው እሷ በምትኖርበት ሰፈር ሲያውደለድል ታየዋለች።

"ምናባክና ነው ልጄን የምታዝላት" ብላ ስታንባርቅበት ጊዜ "…ኧረ ልጅሽ የሚጠጣ ነገር ግዛልኝ ብላኝ ነው! ሆ ሆ ምነካሽ አንቺ ሴትዮ! ተረጋጊ" አላት።

"ውሸቱን ነው። እንዴት እንዳወቅኩ ልንገርሽ፤ አስቢው እስኪ! እንዴት ነው የአንድ ዓመት ልጅ አንድን መንገደኛ የሚጠጣ ግዛልኝ ልትል የምትችለው? ሌባ ነው፤ የልጅ ሌባ…።"

ከዚያ በኋላ ርብቃ ቀስ ብላ ይህንን ሰውዬ መከታተል ጀመረች። በእግሩ ሄዶ ሄዶ የሆነ መኪና ውስጥ ገባ። የገባበት መኪና ውስጥ ደግሞ የሆነች ሴትዮ ነበረች።

ኤስተርና ካሮል ልጆቻቸውን ተሰርቀዋል

እንደ ርብቃ ዓይነት ብዙ ታሪኮች እሷ በምትኖርበት ጎዳና ላይ ይሰማሉ።

ለምሳሌ የኤስተር የ3 ዓመት ልጅ በተመሳሳይ መንገድ ነበር የጠፋው።

"ልጄን ካጣሁ ጀምሮ ልክ አይደለሁም፣ አእምሮዬ ታሟል" ትላለች ኤስተር። ከናይሮቢ እስከ ሞምባሳ በእግሯ ሄዳ ልጇን ፈልጋለች። የለም። በጭራሽ የለም።

ሌላኛዋ ካሮል ናት። የ2 ዓመት ወንድ ልጇን ካጣች አሁን 5 ዓመት ሊሆናት ነው።

"ከነፍሴ አስበልጬ የምወደው ልጄ ነበር። የምኖረውም ለሱ ነበር" ትላለች።

"እንዲያውም ሌቦቹ ልጄን መልሰው ቢሰጡኝ ከልቤ ይቅር እላቸዋለው፤ ክስም አልመሰርትም" ትላለች ልጇን የማግኘት ጉጉቷ ሲያይልባት።

አሁን እነ ኤስተር፣ ርብቃና ካሮል በናይሮቢ የሕጻናት ጥቁር ገበያ እንዳለ እየተረዱ መጥተዋል። ጭራውን መያዝ ነው ያልቻሉት።

ቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን ከአንድ ዓመት በላይ አድብቶ የዚህን ጥቁር ገበያ ጭራ ለመያዝ ጥረት አደረገ። ተሳክቶለታል።

ሕጻናት የሚሸጡባቸው ሆስፒታሎች

የልጆች መሸጫ ጥቁር ገበያ ሰንሰለቱ ከመንገድ ላይ ጊዜያዊ የድንኳን ክሊኒክ እስከ ደላሎች ብሎም የመንግሥት ሆስፒታሎች ጋር የተያያዘ ነው።

የመርማሪ ቡድኑ አንድ ጋዜጠኛ ማንነቱን ደብቆ ልጆች ይሸጣል ወደሚባል ሆስፒታል ሄደ። ሀብታም የልጅ ገዥ መስሎ።

ይህ ሆስፒታል በመንግሥት የሚተዳደር ነው። ልጆችን ለጉዲፈቻ በሕጋዊ መንገድ ለሁለተኛ ወገን ይሰጣል። ውስጥ ለውስጥ ግን ሕገ ወጥ ሽያጭም እንዳለ ይጠረጠራል።

ሆስፒታሉ በደላላ ሰንሰለት የተተበተበ ነው። ሆስፒታሉ ልጆችን እንዴት እንደሚሸጥ እንመለስበታለን። ከዚያ በፊት ግን ልጆችን በችርቻሮ ስለሚሸጡ ከበርቴዎች ጥቂት እናውራ።

እነዚህ ከበርቴዎች አቅራቢና ሰራቂ ደላሎች አሏቸው። ከእነሱ አንዷ አኒታ ናት።

አኒታ ከባድ ጠጪ ስትሆን የአደገኛ ዕጽ ሱሰኛም ናት። የምትተዳደረው ልጅ በመስረቅ ነው። እንደ ርብቃ ካሉ ጎዳና ላይ ከሚኖሩ እናቶች ልጆችን መንትፋ ለደላሎች ታስረክባለች። ወይም ራሷ ትሸጣቸዋለች።

የምትመርጣቸው ሕጻናት ከ3 ዓመት በታች የሆኑትን ነው። "እነሱ ጥሩ ዋጋ ያወጣሉ" ትላለች።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች ስለ አኒታ የሰሙት ከቅርብ ጓደኛዋ ኢማ ነው። ኢማ ስለ አኒታ በርከት ያለ መረጃን አቀበለች። ሕጻናቱን የምታጠምድባቸው ዘዴዎችን ጭምር አብራራች።

አኒታ ልጆች የምትሰርቀው ከየትእንዴት ነው?

መጀመርያ ከእናቶቻቸው ጋር ትቀራረባለች። እናቶቹን ታግባባቸዋለች። ስለሷ ማንነት እንዳይጠረጥሩ ታደርጋለች። ይዘናጉላታል። ልጆቻቸውን ከሰረቀች በኋላም ወዳጅነቷን አታቋርጥም።

የጎዳና እናቶች የጠረጠሯት ከመሰላት ደግሞ አዘናግታ አፍዝ አደንግዝ መድኃኒት ታበላቸዋለች። ምግብ ላይ ነስንሳ፣ መጠጥ ላይ ቀምማ ትሰጣቸዋለች። ድብን ያለ እንቅልፍ ላይ ሲወድቁ ልጃቸውን አንጠልጥላ ትሰወራለች።

አኒታን ለማግኘት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ከወዳጇ ኢማ ጋር ተመሳጠሩ።

አንዷ ጋዜጠኛም የልጅ ገዥ መስላ ቀረበቻትና ተቀጣጠሩ። በአንድ የናይሮቢ የገበያ ቦታ የልጅ ሻጭ ደላሎች ይበዙበታል በሚባል ጠባብና ድብቅ መጠጥ ቤት ነበር የተገናኙት።

አኒታና ጋዜጠኛዋ ተግባቡ። የምትሸጣቸው ልጆች ምን ዓይነት እንደሆኑ፣ ለጊዜው እጇ ላይ ያሉትን ልጆች መልክና ሁኔታ፣ እንዲሁም ዕድሜ ወዘተ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ አጋራች። አኒታ ዝርዝሩን ስትናገር ኮንዶሚንየም ቤት የምታከራይ እንጂ ልጅ የምትሸጥ አትመስልም።

አኒታ ስለ ሥራዋ ሳትሳቀቅ ተናገረች። በምስጢር እየተቀረጸች እንደሆነ ግን አታውቅም።

የልጆች ከበርቴ የሚባለው አለቃዋ ብዙ ልጆች እንድትሰርቅ ጫና እንደሚያደርግባት አብራራች።

"ብታዪ እናትየው ለጎዳና ሕይወት አዲስ ነበረች። ግራ የተገባች እንደሆነች ገና ሳያት አወቅኩ። ስቀርባት ወዲያው አመነችኝ። ልጇን መንትፌያት ጠፋሁ…።"

አኒታ አለቃዋ የልጆች ቢዝነስ ከበርቴ እንደሆነና ከእሷና ከሌሎች የወንጀለኛ ቡድኖች ጋር በመመሳጠር ልጆችን በጥሩ ዋጋ እንደሚረከብ አብራራችላት።

አለቃዋ የተረከባቸውን ልጆች ለማን እንደሚሸጣቸው ስትናገር፣ "ብዙውን ጊዜ መውለድ የማይችሉ ሴቶች ናቸው የሚገዙት። ለእነሱ ልክ እንደ ጉዲፈቻ ማለት ነው። ነገር ግን ለሌላ ሰይጣናዊ ተግባርም ልጆቹን የሚገዙ ሰዎች አሉ" ብላለች።

"ለምሳሌ ልጆችን ከጥንቆላ ጋር በተያያዘ እንደ ዶሮ ለመሰዋት።"

አኒታ ልጆቹን ትሸጣቸዋለች ወይም ለአለቃዋ ታስረክባቸዋለች እንጂ ከዚያ በኋላ በሕጻናቱ ላይ ምን ይድረስ ምን የምታውቀው ነገር የለም። ደንታም አይሰጣትም።

እሷን የሚያስጨንቃት የልጅ መሸጫ ዋጋ መውጣትና መውረድ ነው። ሰሞኑን ዋጋ ጨምሯል። ገበያውም ደርቷል።

በዚህ ቢዝነስ ለተሰማራች አንዲት የተሰረቁ ሕጻናት ተረካቢ በቅርቡ የሸጠችበትን ዋጋ በድብቅ እየተቀረጸች ስትናገር፣ "ሴት ሕጻን 50 ሺህ ሺሊንግ ወንድ ደግሞ እስከ 80 ሺህ የኬንያ ሺሊንግ አስረክቢያለሁ" ብላለች። ይህ በብር 15 ሺህ አካባቢ ይሆናል።

"ልንገርሽ አይደለ? እኔ ሕጻናቱ ለጥንቆላ ይዋሉ ለማደጎ ምን ገዶኝ? ገንዘቤን ካገኘሁ እልም ብዬ እጠፋለሁ" ብላታለች፤ ማንነቷን ለደበቀችው የቢቢሲ ጋዜጠኛ።

ድብቋ ጋዜጠኛ አኒታን ለሁለተኛ ጊዜ ቀጠረቻት። ልጅ ገዥ ሆና ስለቀረበቻት አኒታ አልጠረጠረችም።

በሁለተኛው ቀጠሯቸው አኒታ ብቻዋን አልነበረችም። ገና 5 ወር ካልሞላት እንቦቀቅላ ጋር ነበረች። "አሁን ገና ሰርቂያት መምጣቴ ነው፤ አታምርም?"

ሕጻኗ ለሌላ ገዥ ነው የተሰረቀችው። 50 ሺህ ለመክፈል እንደተስማሙ ነግራታለች።

በዚህ መሀል የአኒታ ጓደኛ ኢማ ጣልቃ ገባች። ያን ቀን አብራቸው ነበረች። "እንዴ አኒታ! እኔ 80 ሺህ የሚከፍል ሰው አገናኝሻለሁ፤ በሃምሳማ እንዳትሸጫት" አለቻት።

በዚሁ ተስማምተው ለ3ኛ ጊዜ ቀጠሮ ይዘው ተለያዩ።

አኒታ ከቢቢሲ ህቡዕ ጋዜጠኛ ጋር ለሦስተኛ ጊዜ የተቀጣጠሩት ምሽት 11 ሰዓት አካባቢ ለመገናኘት ነበር።

የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ ባለፈው ጊዜ አኒታ እጅ ላይ ያየቻት የ5 ወር ሕጻን ልጅ ሕይወት ደኅንነት አስግቷታል።

ሕይወቷን ለመታደግ ቆረጠች። ለሦስተኛው ቀጠሮ ከሲቪል ፖሊሶች ጋር በሰዓቷ የተገኘችውም ለዚሁ ነበር።

በሚያሳዝን ሁኔታ አኒታ በሦስተኛው ቀጠሮዋ ላይ ሳትገኝ ቀረች። በተደጋጋሚ አኒታን ለማግኘት ሙከራ ተደረገ። አልተሳካም።

ከሳምንታት ቆይታ በኋላ በጓደኛዋ ኢማ በኩል ወሬ ተሰማ።

ኢማ እንደምትለው አኒታ መጨረሻ ላይ በሰረቀቻት ልጅ ጥሩ ብር ስላገኘች ባለ ሁለት ክፍል የቆርቆሮ ቤት ለመሥራት ብላ ነበር የጠፋችው። ፖሊስ አኒታን አሁንም እየተከታተላት ይገኛል።

በኬንያ በእርግጥ የሕጻናት ጥቁር ገበያ አለ?

በኬንያ በሚሰረቁ ልጆች ዙርያ ምንም አስተማማኝ መረጃ የለም። መንግሥትም ሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የማያወላዳ አሐዝ የላቸውም።

አንዳንድ የጠፉ ልጆችን በማግኘት ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶች በቂ የሚባል በጀት የላቸውም። የሰው ኃይልም የላቸውም።

ልጆቻቸው ከተሰረቁባቸው እናቶች ጋር በቅንጅት ከሚሰሩ ድርጅቶች አንዱ "ሚሲንግ ቻይልድ ኬንያ" ይባላል።

መሥራቿ ማሪያ ሙንየንዶ ናት። ላለፉት 4 ዓመታት በሥራ ላይ ነበረች። 600 እናቶች ልጆቻቸው ተሰርቀውባቸው እሷ ዘንድ ሪፖርት አድርገዋል።

"የልጆች ሰርቆት በኬንያ ትልቅ መነጋገርያ ነው። ነገር ግን ሪፖርት አይደረግም" ትላለች ማሪያና።

ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸው የሚሰረቁባቸው እናቶች ሀብታሞች አይደሉም። የጎዳና ዜጎች ናቸው። ስለዚህ ጉዳያቸውን ለመከታተልም ሆነ ሪፖርት እንኳ ለማድረግ ጉልበቱ የላቸውም። የሚዲያና የመንግሥትን ትኩረትም ለመሳብ አይችሉም።

የብልጹግ ዜጎች ልጆች እየተሰረቁ ቢሆን ግን ነገሩ አገራዊ መልክ ይኖረው ነበር።

"ድሆች ናቸው። ታክሲ ተሳፍረው እንኳን ሪፖርት ለማድረግ አቅሙና ጉልበቱ የሌላቸው ናቸው። የልጆቻቸውን መሰረቅ የሕግ አካላት ዘንድ እየሄዱ ለመከታተል እንዴት ችለው? በየት በኩል?" ትላለች ማሪያና።

እንዴት በኬንያ ይህ የልጆች ጥቁር ገበያ ሊፈጠር ቻለ?

ማርያና ምላሽ አላት።

"የባሕል ጉዳይ ነው" ትላለች። "…ሴት ልጅ ቆሞ ቀር መሆን አትፈልግም። በትዳር ውስጥ ያለች ሴት ደግሞ ካልወለደች ለእሷ ሞት ነው። በአፍሪካ ይሄ የተለመደ ነው።

"ሴት ልጅ ማግባት አለባት፣ ካገባች መውለድ አለባት፣ ከወለደች ወንድ ልጅ መሆን አለበት። ይህን ማሳካት ያልቻለች ሚስት ከትዳሯ ትፈናቀላለች። ስለዚህ ያላት አማራጭ አራስ ልጅ መስረቅ ይሆናል።"

መውለድ ያልቻሉ ሴቶች እንደ አኒታ ዓይነት የልጅ ደላሎችን በእግር በፈረስ የሚፈልጉትም ለዚሁ ነው።

ከሆስፒታል ነርሶች በኩል የሚሸጡ ሕጻናት

የቢቢሲ የህቡዕ ጋዜጠኛ ወደ ማማ ሉሲ ኪባኪ ሆስፒታል ሄደ። እዚያ ፍሬድ ሊፓራን የሚባል ሠራተኛ አለ። የልጆች ጤና ተንከባካቢ ነው።

ራሱን የደበቀው ጋዜጠኛ ፍሬድን አንድ ምሽት አገኘው። አንዲት የሚያውቃት ሴት ጓደኛው፤ ልጅ በጣም እንደምትፈልግ አግባብቶ ነገረው። "እንዴት ልትተባበራት ትችላለህ?"

"እንግዲህ ነገሩ ትንሽ አስቸጋሪ ነው። ጥንቃቄን ይሻል። ለጊዜው አንድ ወንድ ልጅ እጄ ላይ አለ። እናቱ ከሁለት ሳምንት በፊት እኛ ጋር ጥላው ጠፍታለች" አለው ፍሬድ ለህብዑ የቢቢሲ ጋዜጠኛ።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ በድብቅ ፍሬድን እየቀረጸው ነበር። "ማናችንንም ችግር ውስጥ በማይከት መልኩ ጓደኛህን ባለ ልጅ ልናደርጋት እንችላለን።"

የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ የሚጣሉ ሕጻናት በሕጉ መሠረት ለተገቢው አሳዳጊ ድርጅት ይሰጣሉ። ወይም ደግሞ ሕጋዊና ዘለግ ያለ የጀርባ ጥናት ከተደረገ በኋላ ለሕጋዊ ጉዲፈቻ ይሰጣሉ። ደንቡ የሚያዘው ይህንን ነው። የሆስፒታል ሠራተኞች ግን ይህን ቀዳዳ በመጠቀም ልጆቹን አውጥተው በደላሎች በኩል ለጥቁር ገበያ ያቀርቧቸዋል።

ማንነቱን የደበቀው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ለሁለተኛ ቀጠሮው ባልደረባውን ሮዛን ይዟት ሄደ። ሮዛ ልጅ የምትፈልግ ሴት ሆና ቀረበች። ፍሬይድ ሮዛን አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠየቃት።

ትዳር እንደመሰረተችና ነገር ግን ለመፀነስ እንደተቸገረች፤ በዚህም ጭንቀት እንደገባት ነገረችው።

"ጉዲፈቻ ሞክረሻል?" አላት።

"ከባለቤቴ ጋር ተማክረንበት ነበር፤ ነገር ግን ውስጥብ ስለሆነ ትተነዋል" አለች።

እንግዲያውስ ሌላው ዘዴ ሕጻናትን መግዛት እንደሆነ ገልጾ የእሱ የመጨረሻ ዋጋው 300 ሺህ ሺልንግ እንደሆነ ገለጸላት። 80 ሺህ ብር አካባቢ ማለት ነው።

"በዚህ ከተስማማሽ ስለ ጉዳዩ የምናውቀው እኔ፣ አንቺና ይህ ያመጣሽ ሰው ብቻ ይሆናል።"

ከዚህ በኋላ ሽያጩን ለማካሄድ ቀጠሮ ያዙ።

በድንኳን ክሊኒኮች ውስጥ የሚሸጡ ልጆች

እንደ አኒታ ልጅ ከመንገድ የሚሰርቁ አሉ። እንደ ፍሬይድ ሁሉ ልጅ ከሆስፒታል የሚያሻሽጡ አሉ። ሦስተኛው የልጅ ገበያ በኬንያ ጭርንቁስ ሰፈር በሚቀለሱ የጎዳና የድንኳን ክሊኒኮች ውስጥ የሚካሄድ ነው።

እነዚህ ክሊኒኮች የማዋለድ አገልግሎት ለድሆች ይሰጣሉ።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ካዮሊ ወደሚባለው ጭርንቁስ ሰፈር ሄደች። ጋዜጠኛዋን ወደዚህ የወሰደቻት የጌቶ ራዲዮ አቅራቢ ጁዲዝ ናት።

ካዮሌ የልጅ ጉሊት ያለበት ሰፈር ነው ማለት ይቻላል።

ጁዲዝ ወደ አንዱ ክሊኒክ ልጅ ገዥ መስላ ቀረበች። የዚህ ክሊኒክ አስተዳዳሪ ሜሪ ኦማ ትባላለች። በኬንያ ትልልቅ ሆስፒታሎች ነርስ ሆና ማገልገሏን ትናገራለች።

ማንነቷን የደበቀችው ጋዜጠኛ ወደተጠቀለሰው ክሊኒክ ስትገባ ሁለት ሴቶች በማማጥ ላይ ነበሩ።

አዋላጇ ከሚያምጡት ሴቶች ሌላ ወረፋ ወደሚጠብቁት እየጠቆመች፣ "ያቺ የ8 ወር ተኩል ነፍሰ ጡር ናት። ደርሳለች። ልጇን 45 ሺህ ሺሊንግ ልሸጠልሽ እችላሁ" ስትል ገና ሆድ ውስጥ ያለን ጽንስ ማሻሻጥ ጀመረች።

"አታስቢ፣ እናትየው ልክ ገንዘቧን እንደሰጠሻት ከዚህ እልም ብላ ነው የምትጠፋው።"

"ለሁሉም እናቶች እቅጩን ነግረናቸዋል። በዚህ ድርድር የለም። ልጄን፣ ማቄን ጨርቄን ብለው መመለስ አይችሉም፤ ተሸጠመ፣ ተሸጠ ነው።"

ይቺ ሆዷ ውስጥ ያለውን ጽንስ ትሸጣለች የተባለችው ሴት አዳማ ትባላለች። አዳማ ቤሳቤስቲን የላትም። ልክ እንደ ርብቃ ለአንድ ሰውዬ አረገዘችለትና ሰውየው ብን ብሎ ጠፋ።

እርጉዙ ስትሆን ከሥራ ተባረረች። በአንድ ተቋራጭ ውስጥ ሲሚንቶ ተሸካሚ ነበረች። ለወራት ያህል ቤት አከራይዋ ታገሳት። ከዚያም ግን አውጥቶ ጣላት።

አዳማ እጇ ላይ ያለው ሀብት ሆዷ ውስጥ ያለው ጽንስ ብቻ ነው። ለመሸጥ ወሰነች። እዚህ የጎዳና የዳስ ውስጥ ክሊኒክ የመጣችውም ዋጋ ለመደራደር ነው። የክሊኒኩ ባለቤት 45ሺ ሺሊንግ ብትደራደርም ለአዳማ የምትሰጣት ግን 10 ሺህ ሺሊንጉን ብቻ መሆኑ ያማል።

የጽንስና የልጅ ገበያ ለጥንቆላ

ነርሱ ፍሬይድ በመጨረሻ ደወለ። ልጁ ዝግጁ ነው ኑና ውሰዱ ብሎ ደወለ።

ከሆስፒታሉ አንዳንድ የወረቀት ፎርሞች ከሞላላ በኋላ ውጭ መኪና ውስጥ ወደምትጠብቀው ሮዛ ሄደ።

ለባልደረቦቹ ሮዛ ሕጻናት ተንከባካቢ ድርጅት ውስጥ የምትሰራ ሴት ናት ብሎ ዋሻቸው።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሮዛ ገንዘቡን አቀበለችውና የገዛችውን ልጅ ይዛ ከሆስፒታሉ ወጣች። በእርግጥ መኪናዋ ውስጥ ከገዛችው ልጅ ሌላ ተጨማሪ ሁለት ጨቅላዎች ነበሩ። እነሱ ወደ ማደጎ የሚወሰዱ ናቸው።

ሆን ተብሎ ሕጋዊነት ለማላበስ ነው አብረው እንዲወጡ የተደረገው።

እናቶቹ ልጆቻቸውን ከሸጡ በኋላ ስቃይ ውስጥ ይገባሉ። ገንዘቡን ሲጨርሱ የሚተርፋቸው ጸጸትና ድህነት ነው።

እንደ ርብቃ የተሰረቁት ግን ዕድሜያቸውን ሙሉ እንደባተቱ ነው።

ርብቃ ባለፈው ዓመት አንድ የሰፈሯ ሰው ልጅሽን የሆነ ሰፈር አየሁት አላት። እንቅልፍ ባይኗ አልዞረም። ተቅበጠበጠች።

"እንዴት ልጄ እንደሆነ አወቅክ?" ስትለው "ቁጭ ላውረንስን የሚመስል ልጅ ነው ያየሁት" አላት።

ሀብታም ሰፈር ውስጥ ነው ያየው ልጁን። ሄደች። ፈለገችው ተንከራተተች። ጠብ ያለ ነገር አልነበረም። ስቀይዋ ግን በዛ።

"ብዙ ሰዎች የጎዳና እናቶች ለልጃቸው ብዙም ስሜት ያላቸው አይመስለውም፤ ድህነታቸው ስሜታቸውን የቀማቸው ይመስለዋል። ድህነት እናትነታቸውን አልነጠቀም" ትላለች ማሪያና።

ርብቃ የሚገርማት ግን ሌላ ነው።

"የተሰረቀ ልጅ ገዝተው የሚያሳድጉት እናቶች ግን እንዴት እናት ሊሆኑ ይችላሉ? የሆነ ቦታ የልጁ እናት ስቃይ ላይ መሆኗን ሲያስቡ አይረበሹም?" እያለች ትገረማለች።

ኤስተርና ካሮል ግን እዬዬም ሲደላ ነው ባይ ናቸው።

የፎቶ ባለሙያ ብሪያን ኢንጋንጋ