የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በትግራይ ሁኔታ' ከፍተኛ ስጋት አድሮባቸዋል'-ዋይት ሐውስ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በትግራይ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ "ከፍተኛ ስጋት እንዳደረባቸው" የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ሳኪ ተናገሩ።

የፕሬስ ሴክሬታሪዋ ይህንን የተናገሩት በትናንትናው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

"ፕሬዚዳንቱ በሁኔታው ከፍተኛ ስጋት ገብቷቸዋል፤ ጉዳዩንም በጥልቀት እየተከታተሉት ነው" በማለት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ አስረድተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በክልሉ ላይ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ እንደተረዱትና አስተዳዳራቸውም በአካባቢው ያለው ነገር ተሻሽሎ ማየት ፍላጎት እንዳለው ተገልጿል።

ለዚህም በክልሉ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እንዲቻል ያልተገደበ የእርዳታ ሠራተኞች መግባትንም አስፈላጊነትም እንደተነሳ ተጠቁሟል።

በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ኃይሎች መካከል በተነሳው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል እንዲሁም በመቶ ሺዎች ደግሞ ከመኖያቸው መፈናቀላቸውን የረድኤት ድርጅቶች ገልጸዋል።

በዚሁ በያዝነው ሳምንት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትግራይ ሕዝብ ላይ "የዘር ማፅዳት ወንጀል" መፈጸሙን ተናግረዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን ከማስቆም በተጨማሪ የጎረቤት አገር ኤርትራ ወታደሮችና የአጎራባቹ ክልል አማራ ሚሊሺያ እንዲወጡም ጠይቀዋል።

"በትግራይ ክልል ውስጥ ከኤርትራ የመጡ የውጭ አገር ሠራዊት አባላት አሉ እንዲሁም ከአጎራባቹ ክልል አማራ ክልል የገቡ ወታደሮች አሉ። እነዚህ ኃይሎች ሊወጡ ይገባል" በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተጠቀሱት ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡና ተኩስ አቁም እንዲደረግ በመጠየቅ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በሰጠው ምላሽ "እንደ ሉዓላዊት አገር ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ኃላፊነት ነው" ያለ ሲሆን፤ "ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የትኛውንም የጸጥታ መዋቅር ማሰማራት የመንግሥት ኃላፊነት ነው" ብሏል በመግለጫው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ "አሜሪካ በኢትዯጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለባትም" የሚሉና የመንግሥትን አቋም የሚደግፉ ሰልፎች በአሜሪካ የተካሄዱ ሲሆን፤ በተቃራኒው "ጦርነቱ የትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ነው" የሚሉ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት ኃይል መካከል ያለው ቁርሾ ተባብሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲካሄድ ያዘዙት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወታደራዊ ዘመቻውን ያዘዙት ህወሓት በክልሉ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ጥቃት በመፈፀሙ እንደሆነ ተናግረዋል።

ህወሓት በበኩሉ የሰሜን ዕዝን የተቆጣጠረውና ድንገተኛ ጥቃት ያደረሰው የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ያለውን ጣልቃ ገብነት በመፍራት እንደሆነ ይናገራል።