ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማትሪክ፡ አራስ ልጇን እያጠባች ማትሪክ የተፈተነችው ሚሊዮን
ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ለመፈተን እየተጠባበቁ የነበሩ ተማሪዎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ፈተናው ተራዝሞባቸው ቆይቷል።
በዚህ የተነሳ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ገብተው ነበር፤ በተደጋጋሚ በመራዘሙም "የምንፈተን አልመሰለንም ነበር" ይላሉ።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ቤት ውስጥ መቀመጥ ድብርት ውስጥ ከትቷቸው፣ ተዘናግተ እንደሁም መሰልቸት የተፈጠረባቸውም እንደነበረም ተፈታኞቹ ሲናገሩ ተሰምቷል።
በመጨረሻም እንዲህ ሲጠበቅ የነበረው ፈተና ከሰኞ የካቲት 29 2013 ዓ.ም ጀምሮ የ2013 ሀገር አቀፍ ተሰጥቶ በትናንትናው ዕለት ተጠናቅቋል።
ፈተናቸውን በትናንትናው ዕለት ካጠናቀቁ ተፈታኞች መካከል ደግሞ ሚሊዮን አንዷ ናት።
ሚሊዮን ተካልኝ ገና ወገቧ ያልጠናከረ 'እርጥብ አራስ' ናት።
ሁለተኛ ልጇን የተገላገለችው ቅዳሜ፣ የካቲት 27 2013 ዓ.ም እለት እንደነበር ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ ተናግራለች
አራስ ልጇ የእርሷን ጡት አሁንም አሁንም ይፈልጋል። ያማጠችበት ወገቧ ረዥም ሰዓት አያስቀምጣትም።
የረዥም ጊዜ ሕልሟን ደግሞ የሚወስነው ይህ ፈተና ነው።
እናም ልጇን ታቅፋ፣ እንደ ሌሎቹ በዩኒፎርም ሳይሆን ጋቢ ተከናንባ ወደ መፈተኛ ክፍል አምርታለች።
በነቀምቴ ከተማ የምትኖረው ሚሊዮን፣ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በሆስፒታል የወለደች ሲሆን፣ እሁድ ከሰዓት ከሆስፒታል ወጥታ ሰኞ ጠዋት ለፈተና ተቀምጣለች።
እንደ አራስ ትኩስ ትኩሱ እየቀረበላት፣ በአልጋዋ ላይ አረፍ ብላ ጠያቂ መልካም ምኞቱን እየገለፀ ቢንከባከቧት አትጠላም ነበር።
ነገር ግን እርሷ ልታሳካው የምትፈልገው ሌላ ግዳጅ ከፊቷ ተደቅኗል። እናም ሰኞ ማለዳ እርሳሷን ቀርጻ፣ ልጇን ሸክፋ፣ ወገቧን አጥብቃ አስራ ወደ ምትፈተንበት ትምህርት ቤት አመራች።
"ዛሬ ወልዶ ነገ መፈተን በጣም ይከብዳል" የምትለው ሚሊዮን " ለመተው አስቤ ነበር። ነገር ግን ያለሁበት ሁኔታ እንድተወው አላስቻለኝም" ብላናለች።
በትምህርት ቤት የሚጠብቃት "እንኳን ማርያም ማረችሽ" የሚል ጠያቂ አይደለም፤ ሰዓት አልቋል የሚል ፈታኝ አንጂ። ቢሆንም ነገ ሩቅ አይደለም ለእርሷ ስለዚህ የነገዋን እያሰበች ለመፈተን ቆርጣ ሄደች።
ሚሊዮን ትምህርቷን የተማረችበት አልጋ በአልጋ ላይ በሆነ ሁኔታ አይደለም በተቃራኒው በአነስተኛ እና ጥቃቅን ከጓደኞቿ ጋር ተደራጅታ ቡናና እና ሻይ እየሸጠች ነው የተማረችው።
"የጉልበት ሥራ እየሰራሁ ነው የተማርኩት፤ ቡናና እና ሻይ እየሸጥኩ ነው ራሴን ያስተማርኩት። በዚህ ላይ ደግሞ ትዳር መስርቻለሁ። በዚህ ስራ ላይ የቤተሰብ ኃላፊነት ተደርቦ ትምህርቴን መከታተሌ አስቸጋሪ ነበር።" ትላለች
ሚሊዮን አሁን ወልዳ ለመሳም የበቃችው ሁለተኛ ልጇን ነው። የመጀመሪያ ልጇን ስታሳድግ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፋለች። ልጇ ታምሞባት ሆስፒታል ተኝቶ በሚታከምበት ወቅት አጠገቡ እያደረች ቀን ወደ ትምህርት ቤት በመሄድ ትማር እንደነበር ታስታውሳለች።
በዚያ ላይ የዕለት ጉሮሮን ለማሸነፍ፣ ቡናና ሻይ ትሸጣለች።
በሌላ በኩል በስራ ላይ እያለች የቡና መፍጫ ማሽን እጇን ቆርጧት በጣም ታማም እንደነበር ለቢቢሲ ተናግራለች።
በአንድ በኩል የሚጠዘጥዝ ቁስል፣ በሌላ በኩል የሚያለቅስ ልጅ፣ ዞር ሲሉ የጎደለ ማጀት የእርሷ የትምህርት ዘመን ፈተናዎች ነበሩ።
የትዳር አጋሯ ደግሞ የመኪና አሽከርካሪ ስለሆነ፣ አብዛኛውን ጊዜ ቤት ስለማይገኝ ከጎኗ መቆም አልቻለም።
"እነዚህ ገጠመኞች ናቸው እንግዲህ ጥንካሬ የሆኑኝ፤ ለዚህም ነው አልቀርም በማለት በእልህ ፈተና ላይ የተገኘሁት።" ትላለች።
ምንም እንኳን እንዲህ በጥንካሬ እዚህ ደረጃ ላይ ብትደርስም እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ሲደራረቡባት ትምህርቷን ማቋረጥ አስባ እንደነበር ትናገራለች።
" ነገር ግን እዚህ እቀራለሁ የሚለው ሃሳብ ያስጨንቀኝ ነበር። እስከመቼ ይህንን ቡና ይዤ በየበረንዳው እንከራተታለሁ የሚለው ሃሳብ ጭንቀት ይፈጥርብኛል። ይህ ሁኔታ የቆሰለው እጄን ይዤ ትምህርቴን እንድከታተል አድርጎኛል" በማለት ጥንካሬ ስለሆናት ጉዳይ ትናገራለች
ሚሊዮን ትዳር የመሰረተችው በ2008 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱም የአስረኛ ክፍል ተማሪ ነበረች።
ሚሊዮን ቡናና እና ሻይ መሸጥንም በዚያው ዓመት ነው የጀመረችው።
በዚያው ዓመት ኑሮ ከብዷት ትምህርት አቋርጣ ነበር።
በ2009 ዓ.ም ተመልሳ ትምህርቷን ጀምራ የነበረ ቢሆንም እንደገና ለመቀጠል ሳትችል ቀርታ ዳግም አቋርጣለች።
የመጀመሪያ ልጇንም የወለደችው በ2009 ዓ.ም ነው።
ከዚያ በፅናት እንደገና በ2010 ዓ.ም ዳግም ትምህርት ቤት ተመልሳ የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ተፈተነች።
በተደጋጋሚ ትምህርቷን በማቋረጧ ከጓደኞቿ በሁለት ዓመት ወደኋላ መቅረቷ የሚያብሰለስላት ጉዳይ ነው
ስለዚህ የዚህን ዓመት የ12ኛ መልቀቂያ ፈተና አለመውሰድ ለእርሷ በሕይወቷ የምታመክነው ሶስተኛ እድል መሆኑ እንደማታባክነውም ወሰነች።
በዚያ ላይ የቡና ማሽን እጇን የቆረጣት 12ኛ ክፍል መማር እንደጀመረች ነው። እና በዚህ ከሕመም ጋር የሚታገለው ልጇ፣ በሌላ በኩል አልሞላ ብሎ ያስቸገራት የእለት ሕይወትን ለማሸነፍ፣ በሌላ ወገን ከጀማው ወደ ኋላ የመቅረት እልህ ወጥሮ ይዟት ትምህርቷን ተከታተለች።
በዚህ ሁሉ መሃል አለም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕበል ተመታች። የነበረው እንዳልነበር ሆነ። ሁሉም ያቀደውን ሁሉ ጣጥሎ ቤቱ ተከተተ። ፈተናዎች ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘሙ።
"ከዚያ በኋላ ፈተና መቼ ይሆናል በሚል በጉጉት ስጠብቅ ነበር። የፈተና ጊዜ መተላለፉን ስሰማ ልጅ መውለድ እንዳለብኝ ወሰንኩ፤ ነገር ግን ፈተና ለመሰጠት ይህ ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለውን አስቤ አላውቅም" ትላለች።
ከመውለዷ በፊት ፈተናው ይሰጣል ብላ ተስፋ ያደረገችው ሚሊዮን፣ እያጠናች ቆየች። ነገር ግን ፈተናው በጥር ወር ይሰጣል ቢባልም ዳግም ተራዘመ። ይኼኔ በእርግዝናው ላይ ሌላ ጭንቀት ሚሊዮንን ጎበኛት።
"ፈተናው በ29 ነው መባሉን ስሰማ በጣም ነው የደነገጥኩት"
"እኔ የምወልደው የካቲት 27 መሆኑ ተነግሮኛል" የምትለው ሚሊዮን" ፈተና ደግሞ በ29 ይሰጣል መባሉን ከመገናኛ ብዙኀን ስሰማ በጣም ነው የደነገጥኩት ምን ማድረግ እንዳለብኝም ግራ ተጋባሁኝ" ትላለች
ለመምህራኖቿ አማከረች። በአገር አቀፍ ደረጃ የተቆረጠውን ቀን ማንም ማጠፍ አይችልም። ሁሉም በርቺ አሏት።
"ተስፋ አልቆረጥኩም፤ ምጥ እንኳን ቢይዘኝ ሄጄ እፈተናለሁ። ብዬ ራሴን አሳምኜ ነበር" በማለት በወቅቱ የነበራትን ቁርጠኝነት ታስታውሳለች።
በዚህ መካከል የዋህ ሃሳብ አእምሮዋን ሽው ብሎት ነበር።
ከወለደች በኋላ በጣም ደክሟት ስለነበር "ቤት አልጋዬ ላይ ይፈትኑኛል ብዬ አስቤ ነበር" ያለችው ሚሊዮን፣ እነርሱ ግን በምጥ ላይ እያለሽ እንደሆነ እንጂ ከወለድሽ በኋለ ተማሪዎች መካከል ሆነሽ ነው መፈተን አለብሽ አሉኝ" ብላናለች።
ሰኞ እለት፣ የካቲት 29 2013 ዓ.ም አራስ ወገቧን ሸብ አድርጋ፣ ጋቢ ለብሳ፣ ከጡት የማይነጠለውን ልጇን በመያዝ ወደ ፈተና መስጫው አመራች።
ሚሊዮን ሁለተኛ ልጇን አምጣ በሰላም ስትገላገል የተሰማት ደስታን ያህል በፈተና ክፍል መገኘቷም አስደስቷታል።
በዚህ የፈተና ክፍለ ንፋስ እንዳይነካሽ አትገላለጭ የሚል ቤተሰብ የለም። መኮራረጅ ክልክል ነው የሚል መምህር እንጂ።
እዚህ ልጁ ጠብቷል፤ አንቺስ በልተሻል የምትል እናት የለችም። መልሱን አጥቁራችኋል፤ ስማችሁን መጻፍ አትርሱ፤ ሰዓት አልቋል። እርሳሳችሁን አስቀምጡ የሚል ፈታኝ እንጂ።
ለእርሷ ግን ይህ ደስታ ከምንም በላይ ነው። ቢሆንም የስጋት ቀጭን ነፋስ በአእምሯ ውስጥ መንፈሱ አልቀረም።
"በተቀላቀለ ስሜት ውስጥ ነበርኩኝ" የምትለው ሚሊዮን በፈተና ላይ መገኘቷ ቢያስደስታትም ጨቅላ ልጇን ይዛ ከተማሪዎች መካከል ሆና መፈተኗ የአእምሮ ጫና እንደፈጠረባት ትናገራለች።
"አብሬ የተፈተንኳቸው ልጆች አብረን የተማርናቸው ስላልሆኑ አንተዋወቅም። ይህም ሲያስጨንቀኝ ነበር።"
ራሷን ችላ ለመሄድ አቅም እንዳልነበራት የምትናገረው ሚሊዮን፣ በቅርብ ስለወለደች ደም እንዳይፈሳት እንዳስጨነቃትም አልሸሸገችም።
በዚያ ላይ ደግሞ ፈታኞቿ ወንዶች መሆናቸው፣ ሴት ልጆች አጠገቧም ስላልነበሩ በመናገር ስጋት ውስጥ ሆና መፈተኗን ትናገራለች።
ፈተናው የተጀመረ ዕለት እነዚህ ስጋቶች ቢኖርባትም እያደር ግን ቀለል ብሏት ፈተናዋን ማጠናቀቋን ትናገራለች።
በስተመጨረሻም "ፈጣሪ ከፈቀደ እና የመግቢያ ነጥብ ማስመዝገብ ከቻልኩኝ፣ ዩኒቨርስቲ መግባት እፈልጋለሁኝ ፤ ነገር ግን ልጆቼን ስለማሳድግ ርቄ መሄድ አልፈልግም።" ብላለች።
እኛም ለአራስ የሚገባውን ይዘን፣ ለጨቅላው ጥብቆ ገዝተን ባንጠይቃትም መልካም እድል እንዲገጥማት ተመኘን።