የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ዘረኝነትን የተመለከቱ ጉዳዮችን "በአንክሮ" እንደሚከታተለው ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሰሴክሱ ልዑል ሃሪና ባለቤቱ ሜጋን ከኦፕራ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ወቅት የተነሳውን ዘረኝነትን የተመለከተ አስተያየትን የባኪንግሃም ቤተመንግሥት "አሳሳቢ" እና "በአንክሮ የምንከታተለው ጉዳይ" ነው በማለት ምላሽ ሰጠ።
ከቤተመንግሥቱ የወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው "የሚባሉት ነገሮች ሊለያዩ ይችላሉ" ነገር ግን ጉዳዩን በተለየ ሁኔታ እንመለከተዋለን ሲል ገልጿል።
ሜጋንን የግል ህይወቷን በዳሰሰው በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ በተለይም ልጃቸው አርቺ "ምን ያህል ጥቁር ይሆናል?" የሚል ጥያቄ ከንጉሣውያን ቤተሰብ አባል ለሃሪ መቅረቡ በህይወቷ ያስከፋት ወቅት መሆኑን ተናግራ ነበር።
ኦፕራ ከቃለ መጠይቁ በኋላ ይህንን አስተያየት የሰጡት የእንግሊዟ ንግሥት ወይም የኤደንብራው አልጋ ወራሽ አለመሆናቸውን ሃሪ መናገሩን አስታውቃለች።
ቤተመንግሥቱ ሃሪናና ባለቤቱ ሜጋን "ሁሌም የሚወደዱ የቤተሰብ አባላቶች ናቸው" ብሏል።
ይህ የቤተመንግሥቱ ምላሽ የወጣው ከፍተኛ የንጉሣውያን ቤተሰብን ያካተተ ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ ነው።
ሜጋን ከኦፕራ ጋር በነበራት ቃለ ምልልስ ወቅት የልጇ የአርቺ የቆዳ ቀለምን በሚመለከት የንጉሣውያን ቤተሰብ አባል ባለቤቷን ሃሪን መጠየቁን ከተናገረች በኋለ ቤተ መንግሥቱ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ጫና ሲደረግ ነበር።
በተያያዘ ዜና በአይቲቪ ቴሌቪዥን ላይ 'ጉድሞርኒንግ ብሪቴን' የተሰኘውን ጠጠዋት ፕሮግራም የሚያቀርበው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ፒርስ ሞርጋን ሥራውን ለመልቀቅ ተገዷል።
ፒርስ ሞርጋን የሰሴክሱ ልዑል እና ባለቤቱ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ተከትሎ በሰነዘረው ከባድ ነቀፌታ የተነሳ ነው ሥራውን ለመልቀቅ የበቃው።
አነጋጋሪውን ቃለ መጠይቅ በተመለከተ ከቤተመንግሥቱ መግለጫ የወጣው ቃለመጠይቁ ከተላለፈ ከአንድ ቀን ከግማሽ በኋላ ነው።
"መላው ቤተሰቡ ለሃሪና ሜጋን ያለፉት ዓመታት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበሩ ሲያውቅ አዝኗል" ብለዋል።
"የተነሱ ጉዳዮች በይበልጥ ደግሞ ከዘር ጋር የተያያዘው አሳስበናል፤ የሚባሉት ነገሮች ሊለያዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን በአንክሮ የምንከታተለውና ቤተሰቡ በግሉ የሚመልሰው ይሆናል፤ ሃሪ፣ ሜጋን እና አርቼ ሁሌም ተወዳጅ የቤተሰቡ አባላት ናቸው" ብሏል።
ቃለመጠይቁ እሁድ እለት በአሜሪካ ከተላለፈ በኋላ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን ቤተመንግሥቱ የእንግሊዝ ሕዝብ ሰኞ ምሽት በዩናይትድ ኪንግደም እስኪተላለፍ ድረስ ምላሽ ከመስተት ተቆጥቧል።
በዚህም ንጉሣዊ ቤተሰቡ ጉዳዩን በሚገባ በማጤን ምላሽ መስጠት መፈለጋቸው ተገምቷል።
ንጉሣውያን ቤተሰቦች ይህንን ጉዳይ የቤተሰብ እንደሆነ እና በግል ውይይት እንዲደረግበት መፈለጋቸው ተሰምቷል።
ሰኞ ዕለት ቃለ መጠይቁ በዩናይትድ ኪንግደም ሲተላለፍ 11.1 ሚሊዮን ሕዝብ ተከታትሎታል።
ተዋናይት ሜጋን መርክል በእንግሊዝ የንጉሣውያን ቤተሰብ ውስጥ የነበራት ህይወት ከመክፋቱ የተነሳ "በህይወት መቆየት አስጠልቷት" እንደነበር ይፋ አድርጋለች።
በቃለመጠይቁ ላይ ከተነሱት ነጥቦች አንደኛው የጥንዶቹ ልጅ የልዑልነት ማዕረግ አለማግኘቱ እና የፖሊስ ጥበቃም እንደሌለው ነበር።
ነገር ግን እኤአ በ1917 በወጣው ሕግ ላይ ከጥንዶቹ የሚወለዱ ልጆች ንግሥቲቷ ጣልቃ እስካልገቡ ድረስ ልዑል ወይንም ልዕልት ሊባሉ አይችሉም።












