ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አማዞን 'ከሂትለር ጋር ይመሳሰላል' የተባለውን የመተግበሪያ አርማውን ቀየረ
አማዞን የመገበያያ መተግበሪያው አርማ አዶልፍ ሂትለር ጋር ይመሳሰላል በሚል በርካቶች አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ አርማውን መቀየሩን አስታውቋል።
ኩባንያው ይህንን የመተግበሪያ አርማ በቅርቡ ነው ያስተዋወቀው።
ጥር ላይ የተዋወቀው ይህ አርማ የአማዞን የፈገግታ ምልክት ላይ ሰማያዊ የዕቃ ማሸጊያ ፕላስተር የተለጠፈበት ነው።
ሆኖም አንዳንዶች የቀድሞውን የናዚ አምባገነን ሂትለር ፂም ጋር ይመሳሰላል በሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቴክኖሎጂ ኩባንያው ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዚግዛግ መስመር የነበረበትን ሰማያዊ ፕላስተር የታጠፈ እንዲሆን በማድረግ አሻሽሎታል።
አማዞን ለቢቢሲ እንዳስታወቀው የመጀመሪያው ዲዛይን ሲቀየር በአንዳንድ አገራት መሞከሩን ነው።
ኮሊ ፖርቴል ቤል የተባለው የማስታወቂያ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቪኪ ቡሌን በበኩላቸው "በሚያሳዝን ሁኔታ ለአማዞን በመጀመሪያ አርማቸው ላይ የተለጠፈው ሰማያዊ ፕላስተር ከሂትለር ሪዝ ጋር ተመሳሳይ ሆኗል። ይሄ ቅርፅ በህሊናችን ውስጥ የማይረሳ ሆኗል። በተለይም በየቤቱ ዕቃ ለሚያደርስ ኩባንያ ይህ ጥሩ መመሳሰል አይደለም" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በተንቀሳቃሽ ስልኮችና ታብሌቶች ላይ የሚታየው የኩባንያው መተግበሪያ አርማ የዕቃ ጋሪ ነበር።
አዲሱ ዲዛይን መነሻ ያደረገው የአማዞን ቡናማ የዕቃ መጠቅለያ ካርቶን፣ የኩባንያው ታዋቂ የፈገግታ ምልክትና ሰማያዊ ፕላስተር ነበር።
"አዲሱን አርማ ዲዛንይን ስናደርግ ደንበኞቻችን ዕቃቸው በራቸው በሚደርስበት ወቅት የሚያሳዩትን ደስታ በሚሸምቱበትም ወቅት ያንኑ እንዲያሳዩ ለማድረግ ነው" ብሏል
አንድ ደንበኛ እንዳለው "ቤተሰቦቼ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ ነው አማዞንን የሚጠቀሙት። በሚቀጥሉት ቀናትም ግራ የሚጋቡ ይመስለኛል። አማዞን የት ሄደ ሲሉኝ፤ የሂትለርን ምስል እንዲያዩ እነግራቸዋለሁ" ብሏል
ሌላ ደንበኛ በበኩሉ " ዚግዛግ ምልክት ያለው ፕላስተር ስለሆነ አይደለም ነገር ግን ቅርፁም ሆነ አጠቃላይ ነገሩ የሚስቅ አዶልፍ ሂትለርን ነው የሚመስለው" ብሏል።
የኩባንያዎች ዲዛይንን በመስራት የሚታወቀው ስቱዲዮ ኤልደብልዩ ዲ መስራች ላውራ ዌልደን በበኩላቸው "ኩባንያዎች አርማቸውን በተለያየ ጊዜ ይቀያይራሉ። አማዞን ደንበኞቹን መስማቱ መልካም ነገር ነው። ደንበኞችን ቅድሚያ በመስጠት ይህንን ማድረጋቸው የኩባንያውን ጥሩ አሰራር የሚያሳይ ነው" ብለዋል።