ኮሮናቫይረስ፡ በታንዛኒያ 'የኮቪድ-19 ምልክቶችን ያሳዩ' በርካታ መነኮሳትና ካህናት መሞታቸው ተሰማ

በታንዛኒያ ስድሳ መነኮሳትና 25 ካህናት ባለፉት ሁለት ወራት መሞታቸውን የአገሪቱ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስታወቀች። እነዚህ ካህናትና መነኮሳት የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ታይቶባቸው ነበር ተብሏል።

በአገሪቱ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ህሙማን መረጃ ይፋ በማይሆንባት ታንዛኒያ ቤተ ክርስቲያኗ የአገሬው ሰው ከወረርሽኙ እንዲጠነቀቅ ምክሯን ለግሳለች።

የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ወረርሽኙን ሲያጣጥሉ የተሰሙ ሲሆን ባለፈው ወር የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ታንዛኒያ ወረርሽኙን ለመከላከል ክትባት የመስጠት ዕቅድ የላትም ብለዋል። በተቃራኒው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ስጋት ስትገልፅ ቆይታለች።

የታንዛኒያ የካቶሊክ ኤፒስኮፓል ጉባኤ ፀሐፊ ቄስ ቻርለስ ኪቲማ እንዳስታወቁት የኮቪድ-19 ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆኑትን ጥንቃቄዎች ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። በተለይም የእድሜ ባለፀጎችንና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸውን ሰዎች ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል" በማለት በዳሬሰላምከተማ በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ቄስ ቻርለስ እንዳሉት መነኮሳቱና ካህናቱ ምርመራ ባለማድረጋቸው በኮሮናቫይረስ ሞተዋል ብላ ለማወጅ ቤተ ክርስቲያኗ ብትቸገርም ሁሉም የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ታይቶባቸዋል ተብሏል። በርካቶችም በከፍተኛ ሁኔታ ለመተንፈስ ተቸግረው እንደነበር ተገልጿል።

"ዜጎች እየተመረመሩ አይደለም። ይሄ ትልቁ ፈተና ነው። ቤተ ክርስቲያኗ በአገሪቱ ውስጥ 500 የጤና ማዕከላት ቢኖሯትም ኮሮናቫይረስ መመርመር አልተፈቀደላትም። እንዲሁም የመመርመሪያ መሳሪያውም የለንም" ብለዋል።

ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን በተመለከተ ከመንግሥታቸው በኩል የሚሰጡ አስተያየቶች በቅርቡ እንደተቀየረ ቢናገርም፤ ነገር ግን ታንዛኒያ ግልፅ የሆኑ መመሪያዎችን ባለማስቀመጧ ብዙዎች እንደማይጠነቀቁ ተናግረዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ የወረርሽኙን አስከፊነት በተመለከተ በተደጋጋሚ የምትናገር ሲሆን ጥር ወር ላይ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ገልፃለች።

ታንዛኒያ ካለፈው ዓመት የግንቦት ወር በኋላ የታማሚዎችን ቁጥር ማሳወቅ አቁማለች።

የዓለም ጤና ድርጅት የታማሚዎችን ቁጥር እንድታሳውቅና በክትባቱ ላይ ያላትን አቋም እንድትቀይር ተማፅኗል።