ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲስ የጸደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ምን ይዞ ይመጣል?
በቅርቡ አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁ ይታወሳል።
ይህ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት ግን በ2012 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ፖሊሲን አጽድቋል።
ይህ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ፀድቆ በሥራ ላይ የዋለ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ፖሊሲው የመገናኛ ብዙኃን ሲመራበት የቆየው ሕግ ማሻሻያ ፀድቆ ከመውጣቱ ቀድሞ መውጣቱ አይዘነጋም፡፡
ፖሊሲው ከህትመትና ከብሮድካስት ሚዲያ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በመገናኛ ብዙኃን ሕጎች ላይ ያልነበሩትን በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሰራጭ የኦንላይን ሚዲያንና እና የማህበራዊ ሚዲያን እንደ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ያካተተ ነው።
በፖሊሲው ላይ የኢትዮጵያ ሚዲያ ምን ዓይነት መልክ ሊኖረው እንደሚገባ፣ አቅጣጫው ወዴት መሄድ እንዳለበት፣ የመንግሥት ድጋፍ ምን ድረስ መሆን እንዳለበት የሚያመላክቱ ነጥቦች እንደተካተቱበት ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይተሳትፎው ምን ነበር?
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሕጋዊ ሰርተፍኬት አግኝቶ ሀገሪቱ ውስጥ ሥራ ከጀመረ የተወሰኑ ጊዜያትን አስቆጥሯል።
የምክር ቤቱ አባላት በግልና በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሚሠሩ ጋዜጠኞችና እንዲሁም የሙያ ማህበራት ናቸው።
ምክር ቤቱ ሊያሳካ ካቀዳቸው ጉዳዮች አንዱና ዋንኛው ጋዜጠኞች ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር ጠብቀው እንዲሰሩ ማስቻል መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አባልና ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ታምራት ኃይሉ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።
የፕሬስ ሕጉ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ስር አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሲሰራ እንደነበር አቶ ታምራት ያስታውሳሉ።
የዚህ ግብረ ኃይል ቀዳሚ ተግባር የነበረው ቀደም ሲል በስራ ላይ በነበረው የፕሬስ ሕግ ላይ የተስተዋሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚለውን በጥናት መለየት እንደነበር አቶ ታምራት ተናግረዋል።
በዚህ ጥናት የሕግ ማዕቀፍና የአፈጻጸም ችግሮች መለየታቸውን የሚናገሩት አቶ ታምራት፤ የተለየዩ ጋዜጠኞች ለዚህ ጥናት ግብዓት እንዲሆን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ያስረዳሉ።
ከዚህ በኋላ በተለዩ ችግሮች ዙሪያ ውይይት ተካሄዶ አዲሱ ሕግ ረቂቅ ተዘጋጀ።
ረቂቁ ለውይይት በቀረበበት ወቅት ሙያተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ሌሎች ሕጉ ላይ መግባት የለበትም አልያም አለባቸው ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ውይይቶች መካሄዳቸውን ያስታውሳሉ።
በመጨረሻም ረቂቁ ከተወያዮች ያገኛቸውን ግብዓቶች አካትቶ ወደ ሚኒስትሮች ጉባዔ ተመርቷል።
ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጉ በተመራበት ወቅት ግን በውይይት ወቅት ያልነበሩ እና የሚዲያ ካውንስሉም ሆነ ሙያተኛው ያላያቸው አንቀጾች ተጨምሮበት ማግኘታቸውን አቶ ታምራት አልሸሸጉም።
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ለተጨማሪ የውይይት ጊዜ ጥያቄ ቢያቀርቡም አዋጁ ወደ ምክር ቤቱ በተመራ በአስራ አምስት ቀናት ጊዜ ውስጥ መጽደቁን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ያስተዋላቸው አንቀጾች የትኞቹ ናቸው?
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የተቋቋመው ስህተቶች ሲሰሩ መንግሥት ጋዜጠኞችን እያሳደደ ከሚያስር እርስ በእርስ ለመተራረም እና ለመመካከር እንዲቻል በማሰብ መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ ታምራት፤ ከዚህ በፊት በሚዲያ ግድፈት ሲፈፀም የሚከታተለው ብሮድካስት ባለሥልጣን እንደሆነ ይገልጻሉ።
ከዚህ ቀደም ምክር ቤቱ ስላልነበረ ብሮድካስት ባለስልጣን ይህንን ተልዕኮ መወጣቱ አሳማኝ ነበር የሚሉት አቶ ታምራት፤ አሁን ግን ምክር ቤቱ ስላለ የሚዲያ ፖሊሲው ይህንን ተልዕኮ እንዲወጣ እውቅና እንደሰጠው ይናገራሉ።
የእርስ በእርስ ቁጥጥር (Self-Regulation) ጉዳይ መጠናከር እንዳለበትም በአዋጁ ላይ ተቀምጦ እንደሚገኝ አቶ ታምራት በመጥቀስ፤ ነገር ግን ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚታዩ ግድፈቶችን ባለሥልጣኑ ይመለከታል መባሉ፣ ረቂቅ ሕጉ ከሚዲያ ፖሊሲው ጋር የሚቃረን እንደሆነ ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።
ይህንንም አንቀጽ ምክር ቤታቸው መቃወሙን የሚገልፁት አቶ ታምራት፤ በአዋጁ ላይ ምክር ቤቱም ሆኑ ብሮድካስት ባለሥልጣን የራስን በራስ የማረም ሂደቱን በጋራ ሲያከናውኑ ቆይተው (co-regulation) በመጨረሻ መንግሥት በሚያደርገው ግምገማ ኃላፊነቱን ለምክር ቤቱ እንደሚያስተላልፍ በአዋጁ ላይ መቀመጡን ገልፀዋል፡፡
በመንግሥት ወገን ይቀርብ የነበረው ሐሳብ የሚዲያ ካውንስሉ አሁን ያለበት ቁመና ይህን ተግባር ለመፈጸም የሚያስችለው ስላልሆነ ቁጥጥሩን ብሮድካስት ባለሥልጣን ቢያንስ ለ3 ዓመታት ከካውንስሉ ጋር ሆኖ ሊመራው ይገባል የሚል ነበር።
ሆኖም በ3 ዓመታት ውስጥ የሚዲያ ካውንስሉ ቁመና ተገምግሞ ይህ ራስን በራስ የመቆጣጠር ተግባርና ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ወደ ካውንስሉ ሊተላለፍ የሚችልበት ዕድል እንደሚኖር ያመላክታል፡፡
ለአቶ ታምራት ግን ይህ የሚዋጥላቸው ሐሳብ አልሆነም፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት በሲቪል ሶሳይቲ ሕግ መሰረት የተቋቋመ ነጻና ገለልተኛ ማሕበር ነው የሚሉት አቶ ታምራት፤ መንግሥት እኛን ሊገመግም የሚችልበት አግባብ የለም ይላሉ።
በመሆኑም ይህ የአዋጁ አንቀጽ የገለልተኝነት እና የነጻነት ጥያቄ ያስነሳል በማለት እንዲሻሻል ቢጠይቁም፤ መንግሥት የተለያዩ ምክንያቶች በማቅረብ ሳይቀበላቸው መቅረቱን ይገልጻሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የተቃወሙት ሌላ ጉዳይ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን የአሠራር የሥነ ምግባር ደንብ ያወጣል የሚለውን አንቀጽ ነው።
በዚህ አዲስ አዋጅ ብሮድካስት ባለሥልጣን ስሙ የሚዲያ ባለሥልጣን ተብሎ እንደሚቀየር ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በዋናነት የተቋቋመው የሥነ ምግባር ደንብ ለማስጠበቅና ደረጃውን የጠበቀ መገናኛ ብዙኃን በአገር ውስጥ እየጎለበተ እንዲሄድ መሆኑንንም አስረድተዋል።
ለአቶ ታምራት የሥነ ምግባር ደንብ ማውጣት የባለሙያዎችና የሚዲያ ባለቤቶች እንጂ የመንግሥት ጉዳይ መሆን የለበትም።
መንግሥት ሕግ፣ መመሪያ እና ደንብ ሊያወጣ ቢችልም የሥነ ምግባር ደንብ (Code of Conduct) ግን ባለሙያዎች ራሳቸውን የሚያርሙበት ደንብ በመሆኑ ራሳቸው ማውጣት እንደሚገባቸው አጽንኦት በመስጠት ይናገራሉ።
አቶ ታምራት ይህን ይበሉ እንጂ ብሮድካስት ባለሥልጣን አሁን ይህን የሥነ ምግባር ደንብ ረቂቅ አውጥቶ ለማጽደቅ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሰዎች ሰምተናል፡፡ ደንቡም በረቂቅ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ሌላው አቶ ታምራት ያነሱት የሥነ ምግባር ደንቡ ሲወጣም ተነጥሎ ለብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆን ለኦንላየንም ሆነ ለፕሬስ ዘርፉም የሚያገለግል መሆን እንዳለበት ነው።
አሁንም ቢሆን የሥነ ምግባር ደንቡ (Code of conduct) የኅትመት ሚዲያውን አለማካተቱንና የብሮድካስት መገናኛ ብዙኀን ብቻ ማቀፉን ገልፀዋል።
አቶ ታምራት ሕጉ ላይ በረቂቅ ደረጃ ውይይት ሲደረግ ያልነበረ እና ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ሲመራ የተካተተ ነው በማለት ያነሷቸው ሌሎች ነጥቦችም አሉ።
ከነዚህ መካከል የመገናኛ ብዙኃን ዓይነቶች ይገኙበታል፡፡
በውይይቱ ወቅት የግል፣ የመንግሥት እና የማህበረሰብ የሚባሉ ሦስት መገናኛ ብዙኀን አይነቶች መኖራቸው ብቻ ያውቁ እንደነበረ የገለፁት አቶ ታምራት፤ ነገር ግን ወደ ምክር ቤት የተመራው ረቂቅ ላይ ከዚያ ቀደም ሰምተውት የማያውቁት ልዩ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን የሚል መካተቱን ተናግረዋል።
ይህ አዲስ የተካተተው የመገናኛ ብዙኃን ዓይነት በበጎ አድራጎት አዋጁ የተመዘገቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያቋቁሙት የመገናኛ ብዙኃን ዓይነት መሆኑም መጠቀሱን ያስታውሳሉ።
እነዚህ መገናኛ ብዙኃን የሚንቀሳቀሱት ከሕዝብ በልገሳ በተገኘ ገንዘብ ይሆናል የሚሉት አቶ ታምራት፤ በተጨማሪም የማስታወቂያ ውድድር ሽሚያ ውስጥ መግባታቸው የግል መገናኛ ብዙኃንን ያቀጭጫል ሲሉ ስጋታቸውን ያጋራሉ።
የመገናኛ ብዙኃን ባለቤትነት
የመገናኛ ብዙኃን ባለቤትነትን በተመለከተ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች እስከ 25 በመቶ ድረስ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል በረቂቅ ሕጉ ላይ መቀመጡን አቶ ታምራት ገልፀዋል።
አቶ ታምራት ምክር ቤታቸው ለውጪ አገር ዜጎች በአጠቃላይ ሳይሆን ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ብቻ የባለቤትነት ድርሻ መፈቀድ አለበት የሚል መከራከሪያ ማቅረቡን ያስታውሳሉ።
ይህ ከብሔራዊ ደህንነት አንጸርም አደጋ ስላለው ክርክራቸው ተቀባይነት አግኝቶ በሚዲያ ፖሊሲው ላይ በግለጽ ለዲያስፖራዎች ብቻ እንደሚፈቀድ መቀመጡን ገልፀዋል።
ነገር ግን ረቂቁ ሲመጣ ይህ ጉዳይ አዋጁ ላይ ሳይካተት መቅረቡ ስጋት እንዳጫረባቸው ይናገራሉ። አዋጁ የፀደቀው ይህ ሳይሻሻል ከሆነ ወደ ኋላ ተመልሶ ፖሊሲውን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ አክለው ተናግረዋል፡፡
የጉዳዩን አሳሳቢነት ሲያስረዱም፤ አንድ ኢትዮጵያዊ ግብጽ ሄዶ የሚዲያ ባለቤት ልሁን ቢል እንደማይችል ሁሉ አንድ ግብጻዊ ባለሀብት በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ድርሻ ሲኖረው በሉአላዊነት ጉዳይ እንዴት አደጋ ሊደቅን እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡
ይህ ስጋት እንዳለ ሆኖ ረቂቁ በውይይት ደረጃ በቀረበበት ወቅት እንደተብራራው የመገናኛ ብዙኃን ድርሻ መያዝን በተመለከተ የውጭ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በእኩል የማይታዩበት ዕድል እንዳለ ተመላክቶ ነበር፡፡
የኢትዮያን ባሕል ቋንቋና ታሪክ ማወቅ፣ ከአገሪቱ ጋር ያለ ቁርኝት እንደ ግዴታ ባይሆንም በባለቤትነት ጉዳይ ቅድሚያ ሊያሰጥ እንደሚችል የሚጠቁም አንቀጽ ተካቷል፡፡
ይህም ምናልባት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚዲያ ድርሻ የማግኘት ዕድላቸውን የሚያሰፋ ተደርጎ በበጎ የሚነሳ ሊሆን ይችላል፡፡
"የስም ማጥፋት ወንጀል" ድሮና ዘንድሮ
እንደ አቶ ታምራት ገለፃ ከሆነ ይህ የተሻሻለው የፕሬስ ሕግ በሚዲያ ስም ማጥፋትን የወንጀል ተጠያቂነትን ማስቀረቱ ትልቅ ልዩነት ነው።
ከዚህ በፊት በነበረው አዋጅ ግን በሥም ማጥፋት የሚከሰሱ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን የወንጀል ክስ ይቀርብባቸው እንደነበር አቶ ታምራት ያስታውሳሉ።
በዚህ አዋጅ ስም ማጥፋት እንደ ወንጀል ተቆጥሮ መጠየቃቸው ተገቢ አለመሆኑ ክርክር በመቅረቡ ማሻሻያው መደረጉን ገልፀዋል።
ስም ማጥፋት በመገናኛ ብዙኃን ላይ ሲሆን ከፍትሃ ብሔር ተጠያቂነት ውጪ የወንጀል ተጠያቂነት አያስከትልም ሲሉም ያክላሉ።
ስለዚህ አንድ ጋዜጠኛ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሌላ ሰውን ስም ቢያጠፋ የወንጀል ተጠያቂነት ሳይሆን የፍትሃ ብሔር ተጠያቂነት ብቻ ይኖርበታል ማለት ነው።
ነገር ግን ይላሉ አቶ ታምራት፤ ግለሰቡ ያንኑ ተመሳሳይ ንግግር ከመገናኛ ብዙኃን ውጪ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ቢናገረው በወንጀል እንደሚጠየቅ አስረድተዋል።
ይህም ሰዎችን የወንጀል ተጠያቂነትን ለማስቀረት በሚል በሚዲያ ላይ ስም ማጥፋትን እንዲመርጡ ሊያደርግ ይችል ይሆን በማለት ስጋታቸውን ይናገራሉ።
በሚዲያ ስም ማጥፋት የፍትሀ ብሔርም ተጠያቂነቱ የገንዘብ ቅጣቱ እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ ከፍ ማለቱንም አክለው ገልፀዋል።
የጥቅም ትስስር ከብሮድካስት ባለሥልጣን ጋር
የመገናኛ ብዙኃንን በባለቤትን መያዝ የሚችሉ ሰዎችን በተመለከተ የብሮድካስት ባለሥልጣን ሰራተኞች በአዋጁ መገለላቸውን አቶ ታምራት ያስረዳሉ፡፡
ይህም የሆነው የብሮድካስት ባለስልጣን ሰራተኞች የጥቅም ትስስርን ለማስቀረት በሚል በመገናኛ ብዙኃን ላይ ድርሻ እንዳይኖራቸው አዋጁ መከልከሉ ነው፡፡
ይህ ግን ለአቶ ታምራት ሌላው ቅሬታ የፈጠረባቸው ጉዳይ ነው።
የጥቅም ግጭት ሊፈጠር የሚችልበት ሁኔታ ስለመኖሩ የማይክዱት አቶ ታምራት፤ ያ ግን በከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ ደረጃ ላይ ባሉ የብሮድካስት ባለሥልጣናት ደረጃ እንጂ በዝቅተኛ በባለሥልጣኑ ሰራተኞች ጋር የሚገናኝ አይደለም ይላሉ፡፡
በአዋጁ ውስጥ ‹‹የብሮድካስት ሰራተኞች›› የሚል ሀረግ ማካተቱ ሙሉ ሰራተኞች በሚፈልጉት ሥራ ላይ ለመሰማራት ያላቸውን መብት የሚያግድ ነው በሚል ይገልፃሉ።
በዚህ አዋጅ ብዙ ሚዲያዎች ያብባሉ ሲባል ለመክሰማቸው ምክንያት የሆነው የማስታወቂያ እጦት በምን ሁኔታ እንደተካተተ ማወቅ አልተቻለም፡፡
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በማስታወቂያ ብዛት ለደንበኞች ወረፋ በሚሰጡበት ሁኔታ የግል መገናኛ ብዙኃን ግን ይህ የሩቅ ህልማቸው ሆኖ ቆይቷል፡፡ የዚህ አንድ ምክንያት ተብሎ የሚነሳው ደግሞ የመንግሥት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ማስታወቂያ ለማስነገር የመንግሥት ሚዲያዎችን መምረጣቸው ነው፡፡
በረቂቁ የማስታወቂያ ቅርምት ፍትሐዊ እንዲሆን በርከት ያሉ ድምጾች ተሰምተው የነበረ ሲሆን ይህ ምን ያህል ተመልሷል የሚለው በሂደት የሚታይ ነው፡፡
አዲስ የጸደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ባለመውጣቱ የትኞቹ የካውንስሉ ቅሬታዎች ወይም ገንቢ ሐሳቦች ተካተዋል፣ የትኞቹስ ቸል ተብለዋል የሚለውን ነቅሶ ለማውጣት አልተቻለም፡፡
ይህ አዲሱ አዋጅ ብሮድካስት ሚዲያዎች በይዘታቸው እስከ 80 ከመቶ የሚሆነው አገራዊ እንዲሆኑ እንዲያበረታቱም ያስገድዳል፡፡