ጋዜጠኞች ስለ ለውጡ ማግስት ሚዲያ ምን ይላሉ?

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው። የዘንድሮው የዓለም የሚዲያ ነጻነት ቀን ሚዲያ በምርጫና በዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ያለውን አስተዋጽኦ በማጉላት እነደሚከበር ተገልጿል።

ከዚሁ የሚዲያ ነጻነት ጋር በተያያዘ በለውጡ ማግስት የኢትዮጵያ የሚዲያ ተግዳሮቶች ምንድናቸው? የወደፊት አቅጣጫውስ? የሚል ጥያቄ ለተለያዩ ጋዜጠኞችና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር አቅርበን ነበር።

ጋዜጠኞቹ በኢትዮጵያ ስላለው የሚዲያ ነጻነት ሲያነሱ በተለይ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ወደስልጣን መምጣት ጋር በተያያዘ ብዙ ነገሮች መቀየራቸውን ያነሳሉ።

በሪፖርተር ፣ በሰንደቅና በሌሎችም ጋዜጦች ለረዥም ዓመታት የሰራው ፍሬው አበበ እንደሚለው ከውጪ የሚተላለፉ ስርጭቶችን ማፈን መቆሙና በሽብር ወንጀል ተከሰው እስር ላይ የነበሩ ብዙ ጋዜጠኞች መፈታታቸው ጥሩ የሚባል እርምጃ ቢሆንም ሚዲያውን ወደፊት ለማስኬድ ግን በቂ ስራ እየተሰራ አይደለም ይላል።

''በመረጃ ነጻነት አዋጁ መሰረት መረጃ የማግነት መብት ልክ እንደ ቀድሞው የተገደበ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ብዙ የመንግስት ተቋማት በራቸው ለሚዲያው ክፍት አይደለም''ይላል።

ሚዲያዎች የሆነ ነገር እንዲዘግቡ ሲፈለጉ ብቻ እንጂ ተገቢውን ስራ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረላቸውም የሚለው ፍሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በአንድ አመት ውስጥ ጋዜጠኞችን ሁለት ጊዜ ብቻ ማግኘታቸውን በማስረጃነት ይጠቅሳል።

የአዲስ ዘመን መፅሄት ዋና አዘጋጅ የነበረችው ጋዜጠኛ ስመኝ ይግዛው በበኩሏ ሚዲያው አሁን የሚታየውን አንጻራዊ ነጻነት በአግባብ እየተጠቀመበት ስመለሆኑ እጠራጠራለው ትላለች።

''አሁን ያለውን ሚዲያ ስንመለከተው በአብዛኛው ቀድሞ ወደነበረበት የጎራ ሁኔታ እየተመለሰ ይመስላል። በጣም ትንንሽና የማይመጥኑ ሃሳቦችን ይዘው የሚያትሙና የሚያሰራጩ ተቋማት በዝተዋል።''ትላለች።

ሃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ፣ ለመንግስት አቅጣጫ የሚያሳዩና ፖሊሲዎችን የሚተቹ የሚዲያ ተቋማት እምብዛም እንደሆኑ ትገልፃለች። ሃገሪቱ በዴሞክራሲውም ሆነ ከነጻነት አንጻር ወደፊት ሊያራምድ በሚችል አይነት ደረጃ ላይ ናቸው ብላ እንደማታስብም ትናገራለች።

በትግራይ ክልል እንደ ሚድያ ተቋም መረጃ ማግኘት እጅግ አዳጋች እንደሆነ የሚናገረው በትግርኛ የምትታመው ውራይና መጽሄት አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋዊ በተለይም ከክልሉ መንግስት ፣ ከሌሎች ተቋማት ወይም ከባለሃብቶች ድጋፍ ካላገኙ በስተቀር ወጪውን መሸፈን የሚችል የግል ሚዲያ እንደሌለ ይናገራል።

''ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርእሰ መስተዳድር ሆነው በተሾሙበት ወቅት ሁሉም አካላት ሚድያዎችን እኩል የሚያስተናግዱ እና በነጻነት የሚሰሩ እንዲሆኑ እናደርጋለን ብለው የነበረ ቢሆንም አሁንም የመንግስት ሚድያዎች በነጻነት ሳይሆን በኮሚቴዎች እንዲመሩ እየተደረገ ነው'' ይላል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው ሃገሪቱ የሚዲያውን ዘርፍ ለማሳደግና ነጻ ለማድረግ ባለፈው ዓመት በሰራችው ስራ በሃገራት ደረጃ ጠቋሚ መረጃ መሰረት 40 ደረጃዎችን በማሻሻል ከ150 ወደ 110 ከፍ ብላለች ብለዋል።

ይህ ደግሞ እውነትም ለውጥ ስለመለኖሩ እንደማሳያ ሊወሰድ ፤ በአንድ ዓመት ውስጥ የተሰሩት ስራዎች እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ ዳይሬክተሩ።

ዳይሬክተሩ በሃገሪቱ ከመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ ሚዲያዎች እያሳዩት ያለው ባህሪ እንደ ስጋት ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ በመጠቆም ነገር ግን ችግሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገራት እንደሚያጋጥም ያስረዳሉ።

''አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ባለው ስሜታዊነትና ወገንተኝነት የሚያጠቃው አዘጋገብ በሙያዊ መነጽር በሚታዩበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ የጋዜጠኝነትን መርህና ስነምግባርና የጣሱ ናቸው።''

ሌላው ያነጋገርነው ጋዜጠኛ አስረኛ እትሙን ለአንባብያን ያበቃው የቦሌ ታይምስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ስዩም በለውጡ ማግስት ሚዲያው ነፃ እንዲሆን መደረጉ፤ ያሉት እንዲነቃቁ አዲሶችም እንዲፈጠሩ በር እንደከፈተ ያምናል።ሚዲያው ነፃና ክፍት ሲደረግ ግን አብሮ ስርዓት ተዘርግቶለት አለመሆኑ ጋዜጠኝነቱ ፣ አክቲቪዝሙና ፖለቲከኝነቱ አንድ ላይ ተደበላልቀው እየሄዱ መሆኑ የሚያስከትለው አደጋ እንዳለ ይሰማዋል።

የሚዲያ ተቋማቱ በነጻነት እንዲሰሩና ዘርፉ እንዲጎለብት መንግስትም ሆነ ሚዲያው የየራሳቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው የሚለው ሃሳብ ሁሉንም የሚያስማማ።

አሁን በሚዲያውና በመንግስት መካካል ያለው መተማመን በሚፈለገው ደረጃ አለ ብሎ የማያምነው ጋዜጠኛ ፍሬው መንግስት ከአንገት በላይ ነው ሚዲያውን እደግፋለው እያለ ያለው ይላል።

''እንደዚህ አይነት ንግግሮች ድሮም ቢሆን ነበሩ፤ መሬት ላይ ወርዶ መንግስት እውነትም ከሚዲያው ጋር መስራት አለበት። የድሮው አይነት ስርአት ተመልሶ እንዳይመጣ ስጋት አለኝ''ይላል።

ስመኝም ብትሆን የሚዲያው ሙያዊ ነጻነት ከሃላፊነት ጋር አብሮ መሄድ ካልቻለ አሁን የመጣው ነጻነት ሌላ አይነት ችግር ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ስጋቷን ታስቀምጣለች።

''አሁን ያለውን የዘር ፖለቲካና ግጭት የበለጠ እያባባሱ ሃገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይወስት ስጋት አለኝ።''

ሙያዊ ስነምግባርን ተከትሎ ካለመስራት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እስካሁን የወሰደው እርምጃ አለ ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ዳይሬክተሩ ሲመልሱ '' ከእርምጃ ይልቅ ወደ ድጋፍ ያተኮረ ስራ ነው እየሰራን ያለነው።'' ብለዋል።

የሚዲያ ተቋማቱ አሁን እያሳዩት ያለውን ባህሪ ያመጡት በቀድሞ ስርአት በቂ በሆነ መልኩ ስራቸውን እንዲሰሩ ስላልተፈቀደላቸውና አቅማቸውን በተገቢው ሁኔታ ማጎልበት ስላልቻሉ ነው ሲሉ ያብራራሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘም መንግስት ሁለት ሃላፊነቶች አሉበት ብለው ያምናሉ። አንደኛው ሆደ ሰፊ ሆኖ ነገሮችን ማሳለፍ መቻል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ድጋፍማድረግ፣ ስልጠና ማመቻቸት ናቸው።