ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በሰዎች ላይ የሚደረግ የክትባት ሙከራ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈቃድ አገኘ
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ጤናማ ወጣት በጎ ፈቃደኞች በዓለማችን የመጀመሪያ ነው በተባለ ሙከራ ላይ እየተሳተፉ ነው።
በጎ ፈቃደኞቹ ኮቪድ-19 በሰዎች ላይ ምን አይነት ጉዳት እንደሚያስከትልና ክትባቱ ምን እንደሚሰራ በትክከል ለማወቅ ሆን ተብሎ በቫይረሱ እንዲያዙ ይደረጋል።
ጥናቱን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ፈቃድ የተገኘ ሲሆን በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ደግሞ እድሜያቸው ከ18 እስከ 30 የሆኑ 90 ጤናማ በጎ ፈቃደኞች ይመረጣሉ።
በጎ ፈቃደኞቹ ተመራማሪዎች ሁሉንም ነገር መቆጣጠር በሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ ለቫይረሱ እንዲጋለጡ የሚደረግ ሲሆን ጤናቸው ላይ ምንም አይነት እክል እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል ተብሏል።
ዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን ድረስ ከ15 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ክትባትን ሰጥታለች።
በሰዎች ላይ የሚደርሱ ተጽኖዎችን የሚመረምሩ ጥናቶች እንደ ወባ፣ ታይፎይድ እና ኮሌራ ላሉ በሽታዎች መድሀኒቶችን በማግኘት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
የሚደረጉት ሙከራዎች ተመራማሪዎች ምን ያክል ቅንጣት ኮሮረናቫይረስ ሰዎችን እንደሚያጋልጥ እንዲሁም የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ስርአት እንዴት ምላሽ ይሰጣል የሚሉትን ነገሮች በአግባቡ ለመመርመር ይረዳሉ።
በዚህም መሰረት ዶክተሮች በቫይረስ አማካይነት የሚመጣውን የኮቪድ-19 በሽታ በአግባቡ እንዲረዱትና ህክምናዎች እንዴት መሰጠት አለባቸው የሚለውን እንዲወስኑ ያግዛቸዋል።
ይህ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሚካሄደው የተባለለት ጥናት በዩናይትድ ኪንግደም መንግስት፣ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን አንዲሁም ሌሎች ተቋማት በሕብረት ነው የሚያካሂዱት ነው።
መጀመሪያ ላይ ሙከራው ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ባለፈው ዓመት መጋቢት አካባቢ ሲዘዋወር የነበረ የኮሮናቫይረስ አይነት ጥቅም ላይ የሚያውል ሲሆን፤ ይህ የቫይረስ አይነት ጤናማ የሆኑ አዋቂዎች ላይ የሚያሳድረው የጤና እክል እምብዛም ነው ተብሏል።
በዚህ ምክንያት ሆነ ተብሎ በቫይረሱ እንዲያዙ የሚደረጉት በጎ ፈቃደኞች ምንም ስጋት አይገባቸውም ብሏል ጥናቱን የሚያካሂደው የተመራማሪዎች ቡድን።
መንግስት በአሁኑ ሰአት በጎ ፈቃደⶉች መጥተው እንዲመዘገቡና የጥናቱ አካል እንዲሆኑ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ለጊዜያቸውና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ክፍያ እንደሚኖውም አስታውቋል።