ኮሮናቫይረስ፡ በዩኬ የኮሮና ፅኑ ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ተባለ

ነርስ ሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ነርስ ሆስፒታል ውስጥ

አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ መቀስቀስን ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቃች ነው።

በዚህ ምክንያትም ባለፈው ዓመት ቫይረሱ ካደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት በላይ አሁን እያስተናገደች ነው። የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም የታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው። ለአብነት በኮሮና ተኅዋሲ ለሚጠቁ ጽኑ ህሙማን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የትንፋሽ መስጫ መሳሪያ (ቬንትሌተር) የሚያስፈልጋቸው የኮሮናቫይረስ ህሙማን ቁጥር በአንድ ወር ያህል በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በዩናይትድ ኪንግደም ለመጀመሪያ ጊዜ በሜካኒካል ቬንትሌተር መተንፈሻ የሚረዱ ሰዎች ቁጥር ከ4 ሺህ ማለፉ ተገልጿል።

የመንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ እስካለፈው አርብ ባለው ጊዜ ውስጥ 4 ሺህ 76 የሚሆኑ ታማሚዎች በሆስፒታል ውስጥ በቬንትሌተር እየታገዙ የሚተነፍሱ ናቸው።

ይህ አሐዝም ከመጀመሪያው ዙር ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው። በመጀመሪያው ዙር የወረርሽኙ ስርጭት የነበረው ከፍተኛ ቬንትሌተር የሚጠቀም ታማሚ ቁጥር አጋጥሞ የነበረው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር አካባቢ ነበር።

በወቅቱም 3 ሺህ 301 ሰዎች በቬንትሌተር እየታገዙ ይተነፍሱ ነበር።

ትናንት [ቅዳሜ] በዩናይትድ ኪንግደም 1 ሺህ 348 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሲሞቱ ከ33 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ አዲስ በቫይረሱ ተጠቅተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ዋና የሳይንስ አማካሪ ሰር ፓትሪክ ቫላንስ አርብ ዕለት በሰጡት ማብራሪያ "የሞት መጠኑ አስፈሪ ነው፣ በአስፈሪነቱም ይቆያል። በጣም እሰጋለሁ። የሞት መጠኑ ሳይቀንስ በዚሁ መጠን ብዙ ሰዎችን ላልተወሰነ ጊዜ ሊቀጥፍ ይችላል" ብለዋል።

አዳዲስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጽኑ የታመሙ የኮቪድ ታካሚዎች በአልጋ እጥረት ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ እየተዘዋወሩ መሆኑ ታውቋል። በጽኑ ታመው ሆስፒታል ከሚገቡ 10 ሰዎች መካከል ቢያንስ አንዱ ወደ ሌላ ቦታ ይዘዋወራል ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት የቢቢሲው ዘጋቢ ክሊቭ ማይሬ በሮያል ለንደን ሆስፒታል ተገኝቶ እንዳረጋገጠው፣ ከሆስፒታሉ 15 ፎቆች መካከል 12ቱ በኮሮናቫይረስ ታማሚዎች የተሞሉ ናቸው።

በሜካኒካል ቬንትሌተር አልጋ ላይ የሚተኙ ሰዎች ቁጥር ከፈረንጆቹ ታኅሥስ 18 ጀምሮ በተከታታይ እየጨመረ ነው። ያኔ ከነበረበት 1 ሺህ 364 ተነስቶ ባለፈው አርብ 4 ሺህ 76 ደርሷል።

በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የተጣሉ ገደቦችን ለማላላትና ፖሊሲ ለመቀየር መንግሥት ከሚጠቀምባቸው መረጃዎች መካከል ይሄኛው ዋነኛው ነው።

ባለፈው ዓመት ወረርሽኙ በቻይና እና በጣሊያን ያደረሰውን ቀውስ በመከተል የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትም ቅድሚያ በመስጠት ሆስፒታሎች ቬንትሌተር እንዲያሟሉ ዝግጅት አድርጓል።

በዚህም በርካታ ቬንትሌተሮች የተገዙ ሲሆን አደጋው በከፋ ጊዜ በሙሉ አቅም ለመከላከል እንዲያመች ቬንትሌተር አምራቾችንም አዳዲስ ንድፍ እንዲያወጡና በፍጥነት እንዲያመርቱ ሲያበረታታ ቆይቷል።

ባለፈው መስከረም ወር ከብሔራዊ ጤና አገልግሎት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 30 ሺህ ቬንትሌተር አለ። ይህም ለ2 ሺህ 200 ሰዎች አንድ ቬንትሌተር እንደማለት ነው።

ሆስፒታል ውስጥ መጀመሪያ ወረርሽኙ ተከስቶበት ከነበረው ወቅት አንጻር ለየት ባለ ሁኔታ ነው እየተስተናገዱ ያሉት፤ በዚህም ምክንያት ባለፈው ዓመት መጋቢት፣ ሚያዚያ እና ግንቦት አካባቢ በቬንትሌተር ይታገዙ ከነበሩት ታማሚዎች አንጻር ሲታይ በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ያገግማሉ።

በዚያ ላይ በርካታ መድሃኒቶች አጋዥነታቸው ተረጋግጦ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። ይህም ዲክሳሜታዞንን ያካትታል። ይህ መድሃኒት በቬንትሌተር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሞት በአንድ ሦስተኛ የሚቀንስ ሲሆን በኦክስጅን ውስጥ ያሉትን ደግሞ በአንድ አምስተኛ ይቀንሳል።