ትራምፕ በመጨረሻው ቀናቸው ለቀድሞው ረዳታቸው ስቲቭ ባነን ምህረት አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሥልጣናቸው የመጨረሻ ቀን በማጭበርበር ወንጀል ተከስሰው ለነበሩት የቀድሞ ረዳታቸው ስቲቭ ባነን ምህረት አደረጉ።
ይህ የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የተሰማው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቃለ መሃላ ከመፈፀማቸው በፊት ነው።
ትራምፕ በመጨረሻው የስልጣን ዘመናቸው ከ140 በላይ ለሚሆኑ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ምህረት ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል ራፐር ሊል ዋይኔ እና ኮዳክ ብላክ ሲገኙበት የዲትሮይት ከንቲባ ለነበሩት ክዋሜ ኪልፓትሪክ ደግሞ ቅጣታቸው ተቀንሶላቸዋል።
73 ታራሚዎች ይቅርታ ሲደረግላቸው 70 ያህሉ ደግሞ ፍርዳቸው እነዲቀነስላቸው እንደተደረገ ከዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ ያስረዳል።
ስቲቭ ባነን፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ2016 በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቁልፍ ስትራቴጂስት እና አማካሪ የነበሩ ሲሆን ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር ላይ በአሜሪካ እና በሜክሲኮ መካከል ለሚገነባው አጥር የተሰበሰበን ገንዘብ በማጭበርበር ተከስሰው ነበር።
ዐቃቢያነ ሕጎች እንዳሉት ባነን እና ሌሎች ሦስት ሰዎች በሜክሲኮ ድንበር ላይ አጥር ለመገንባት ከለጋሾች የተሰጠን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ አጭበርብረዋል።
"እንገነባዋለን" በተሰኘው በዚህ ዘመቻ 25 ሚሊዮን ዶላር ያህል ተሰብስቧል። ባነን ከ1ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀብለዋል የተባለ ሲሆን የተወሰነውን ለግል ወጪያቸው አውለውታል ተብሏል።
እርሳቸው ግን ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት የተከራከሩ ሲሆን ጉዳያቸው ገና እየታየ ነበር።
ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ባነን "በጣም ቁልፍ ሰው" በማለት ፖለቲካዊ ብቃታቸውንም አድንቋል።
ራፐሮቹ ሊል ዋይኔ እና ኮዳክ ብላክ ከጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ሲሆን ክዋሜ ኪልፓትሪክ ደግሞ በሙስና ወንጀል ተከስሰው 28 ዓመት ተፈርዶባቸው ነበር።
የሥልጣን ዘመናቸውን አጠናቅቀው ዋይት ሐውስን የሚለቅቁ ፕሬዝዳንቶች ለተከሳሾቹና ፍርደኞች ምህረት ማድረጋቸው የተለመደ ነው።
ይቅርታ የሚደረግለት ታራሚ ክሱ ውድቅ የሚደረግለት ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ የእስር ጊዜው እንዲያጥር ወይንም እንዲያበቃ ሊደረግ ይችላል። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከወንጀል ጋር በተያያዘ በፌደራል ችሎት ውስጥ ምህረት ለማድረግ ያልተገደበ ስልጣን አለው።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለበርካቶች ምህረት አድርገዋል። ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከል በርከት የሚሉት ረዳቶቻቸው አልያም የቅርብ አጋሮቻቸው የነበሩ ሰዎች ናቸው።













