የዲፕሎማሲ ልምድ የሌለው የትራምፕ ልጅ ባል ጃሬድ ኩሽነር ማነው?

ጃሬድ ኩሽነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጃሬድ ኩሽነር የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕን ታኮ ነው ወደ ዋይት ኃውስ የመጣው።

የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ በሆነው ግዙፉ ነጭ ቤተ መንግሥት ለመቆየትና የሚስቱን አባት ለማስደሰት ብዙ ጥሯል።

ዶናልድ ትራምፕ ሹሞቻቸውን ለመሻር ሁለት ጊዜ ማሰብ አያሻቸውም። ስንቱን ገንድሰው ጥለዋል።

ጃሬድም ይህ ዕጣ ይደርሰዋል እየተባለ ሲታማ ቢቆይም ይሄው ምንም ሳይነካው ለመጪው መንግሥት መንበሩን በሰላም አስረክቦ ሊወርድ ነው።

ጃሬድ፤ የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ሆኖ ከመሾሙ በፊት ምንም ዓይነት የዲፕሎማሲ ልምድ አልነበረውም።

የ37 ዓመቱ ጃሬድ የቀድሞ ሥራው የአባቱን ሪል ኢስቴት ማስተዳደር ነበር።

ቤቶችን ከማስተዳደር ሃገርን የሚያስተዳድር ሰው ወደማማከር የተሸጋገረው በፍጥነት ነበር።

ሰውዬው የእስራኤልና ፍልስጤምን ጉዳይ እንዲይዝ ትራምፕ አጩት። አልፎም በቻይና፣ ሜክሲኮና ካናዳ ጉዳይ የባለቤቱን አባት ያማክራል።

ስለ ሃገራት ጉዳይ ከትራምፕ ጋር ከመምከር አልፎ ጡረተኛ ወታደሮችን በተመለከተ ሃሳብ ይሰጥ ነበር።

ሆኖም የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን 'የሁሉም ነገር ዋና ፀሐፊ' ብለው የሚጠሩት ይህ ሰው መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም።

ባለፈው የካቲት ከባድ ምስጢር ወደ ሚቀመጡበት መዝገብ ቤት የሚያስገባውን የይለፍ ወረቀት ተነጠቀ።

ለጥቆ ደግሞ የኦቫል ኦፊስ [የፕሬዝደንቱ ፅ/ቤት] ስብሰባዎች ላይ እንዳይሳተፍ ታገደ።

ነገር ግን ከወራት በኋላ የማይቋረጥ የይለፍ ወረቀት ድጋሚ ተሰጠው።

ዋሽንግተን ፖስት እንደሚለው ጃሬድ የይለፍ ወረቀቱን የተነጠቀው የቻይና፣ እስራኤልና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እንዲሁም ሜክሲኮ ባለሥልጣናት ወጣቱን ዲፕሎማት ሊበዘብዙት ማሰባቸውን ተከትሎ ነው።

የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ባል የይለፍ ወረቀቱ እንዲነጠቅ ያዘዙት የዋይት ኃውስ ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ጆን ኬሊ ናቸው ይባላል።

ጆን ኬሊ የዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ኃይል አዛዥ ሳሉ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ገነዳድሰው ጥለዋል ይባልላቸዋል።

ነገር ግን እንደ ስቲቭ ባነን እና ሪንስ ፕሪበስ ያሉ ነባር የትራምፕ አማካሪዎች ከሥልጣን ሲወርዱ ጫፉ ያልተነካው ጃሬድ ለጆን ኬሊ የሚተኛ አልነበረም።

'ፖለቲካ አዋቂ'

ዶናልድ ትራምፕ በአንድ ወቅት ጃሬድ ኩሽነርን 'የበሰለ ፖለቲካ አዋቂ' ሲሉ አሞካሽተውት ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ኒኪ ሄሊ ደግሞ 'የተደበቀና ማንም ሊረዳው የማይችለው ምጡቅነት ያለው' ሲሉ ጃሬድን ገልፀውት ነበር።

ጃሬድ 'ምጡቅ' ስለመሆኑ መመስከር ባይቻልም ትራምፕ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2016 የምረጡኝ ዘመቻ ሲያደርጉ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ ይነገርለታል።

በወቅቱ የትራምፕ ዘመቻ ኃላፊ የነበሩት ኮሪ ሌዋንዶውስኪ ከሥልጣናቸው ተነስተው ነበር። ሰውዬው ከመንበራቸው እንዲፈናቀሉ ያደረገው ጃሬድ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

ጃሬድ ኩሽነር የተወለደው ሊቪንግስተን በተሰኘችው የኒው ጀርዚ ከተማ ነው።

ከሁለት እህቶቹና ከወንድሙ ጋር እየቦረቀ ያደገው ጃሬድ የአይሁድ ኦርቶዶክስ [ባሕላዊ የአይሁድ እምነት የሚከተሉ] እምነት ተከታይ ነው።

አያቶቹ በርካታ አይደሁዶች ከተጨፈጨፉበት የሆሎኮስት ግድያ ተርፈው ነው በ1949 ወደ አሜሪካ የመጡት።

አባቱ ቻርልስ ኒው ጀርዚ ውስጥ ቤት ንብረት በመሸጥ ነው ሃብት ያካበቱት።

ጃሬድ ምንም እንኳ የትምህርት ቤት ውጤቱ አመርቂ ባይሆንም ስመ ገናናው ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ። ይህን የፃፈው ዳንዔል ጎልደን የተባለው ፀሐፊ ነው።

ፀሐፊው 'የአሜሪካ ገዥው መደብ ወደ ግዙፍ ኮሌጆች እንዴት እንደሚያቀኑ' የሚተነትን መፅሐፍ አለው።

ፀሐፊው እንደሚለው ጃሬድ ወደ ሃርቫርድ ከመግባቱ በፊት 2.5 ሚሊዮን ዶላር በእርዳታ መልክ ለዩኒቨርሲቲው አበርክቷል።

በተመሳሳይ ኮርኔል እና ፕሪንስተን ለተሰኙት ነባር ኮሌጆች ሚሊየን ዶላሮች ለግሷል።

በ2006 የ25 ዓመቱ ጃሬድ ዘ ኒው ዮርክ ኦብዘርቨር የተሰኘውን ጋዜጣ ገዛ።

ጃሬድ ኩሽነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሶስት ዓመታት በኋላ ለ15 ዓመታት የጋዜጣው አርታዒ የነበሩት ታዋቂው ፒተር ካፕላን ከጃሬድ ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ሥራቸውን ለቀቁ።

ጃሬድ ጋዜጣውን ትቶ ወደ ዋይት ኃውስ ከማቅናቱ በፊት ባሉት ሰባት ዓመታት ጋዜጣው ስድስት ጊዜ አርታዒዎች ቀይሯል።

ጃሬድና ትራምፕ - የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች?

2008 ላይ አባቱ በታክስ ማጭበርበር፣ ለምርጫ ዘመቻ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ በመለገስና ምስክሮች ላይ ጫና በማሳደር ወንጀል ከርቸሌ ገቡ።

ይሄኔ ጃሬድ የቤተሰቡን ሃብትና ንብረት ተቆጣጠረ።

የጃሬድ አባት የእህታቸውን ባል ከአንዲት ሴተኛ አዳሪ ጋር እንዲገናኝ አድርገው ቪድዮ ከቀረፁት በኋላ እሳቸው ላይ ምስክር እንዳይሆን ጫና ማሳደራቸውን አምነው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት ቻርልስ ኩሽነር በነፃ እንዲለቀቁ ምህረት አድርገውላቸዋል።

በ2009 ጃሬድ ከኢቫንካ ትራምፕ ጋር ተጋባ።

ሠርጉ ኒው ጀርዚ በሚገኘው የትራምፕ ጎልፍ ክለብ ነበር የተደረገው። ጥንዶቹ ሶስት ልጆች አሏቸው።

ዶናልድ ትራምፕና ጃሬድ ኩሽነር ያግባባቸው ምናልባት ተመሳሳይ ፍላጎት ስላላቸው ሊሆን ይችላል ይላሉ የአሜሪካ ፖለቲካ ተንታኞች።

ሁለቱም ለፖለቲካ ሩቅ የሆኑና የአባቶቻቸውን ሃብት የወረሱ ናቸው።

የጃሬድ ቤተሰቦች ከማንሃታን ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች መካከል 666 ጎዳና ላይ ያለውን አንገተ ረዥም ሕንፃ ገንብተዋል።

ከነጃሬድ ሕንፃ ትንሽ ፈቀቅ ብሎ የትራምፕ ታወር አለ።

የትራምፕ አባት ፍሬድሪክ ክራይስት ትራምፕ ልክ እንደ ጃሬድ አባት አነጋጋሪ ተግባራትን የከወኑ ናቸው። ቤቶችን ሲሸጡ የቆዳ ቀለም ለይተው ነው እየተባሉ ይታሙም ነበር።

ጃሬድ የአሜሪካ ሴኔት፤ በ2016 የአሜሪካ ምርጫ የሩስያ እጅ አለበት። ለዚህም የተባበሩ አሜሪካዊያን አሉ ብሎ ከጠረጠራቸው ሰዎች መካከል ነው።

ጃሬድ ታኅሣሥ 2016 ከሩስያ አምባሳደር ጋር ተናግሮ ነበር። አልፎም አሜሪካ ቅጣት ከጣለችበት የሩስያ መንግሥት ባንክ ኃላፊ ጋር ተገናኝቷል።

ጃሬድና ትራምፕ የሚያመሳስላቸውም የሚያገኛቸውም ነገር ብዙ ነው። ወደፊትም አብረው ሊሠሩ አቅደው ይሆናል።

ማን ያውቃል ትራምፕ በ2024 ምርጫ እወዳደራለሁ ብለው ብቅ ካሉ ጃሬድ ከጎናቸው ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

ጃሬድንና ትራምፕን የማያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ - ጃሬድ ከትራምፕ ባህሪ ወጣ ባለ መልኩ ጃሬድ ካሜራ አይወድም።