አሜሪካ፡ የትራምፕ የቀድሞ አማካሪ ስፒቭ ባነን በማጭበርበር ወንጀል ተከሰሱ

ስቲቭ ባነን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ስቲቭ ባነን በአንድ ወቅት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ታማኝ አማካሪ ነበሩ

የቀድሞው የትራምፕ አማካሪ ስቲቭ ባነን አሜሪካ ራሷን ከሜክሲኮ ለመነጠል ለምትገነባው ግንብ ከተዋጣው ላይ በመቆንጠር ወደ ግል ኪሳቸው አስገብተዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ባነን እና ሌሎች ሶስት ሰዎች "እንገነባዋለን" በተሰኘው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ወቅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለጋሾችን አጭበርብረዋል በሚልም ተከስሰዋል።

በወቅቱ በዘመቻው 25 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ተችሎ እንደነበር የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ አስታውቋል።

ባነን ግን ለግል ኑሯቸው መደጎሚያ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ መቀበላቸውና ማጥፋታቸው ተገልጿል።

ስቲቭ ባነንና ሌሎቹ ተከሳሶች ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ እየተገለፀ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ2016 የምረጡኝ ቅስቃሳቸው ወቅት አሜሪካንና ሜክሲኮን በሚያዋስነው ድንበር ላይ ግንብ ለመገንባት ቃል የገቡ ሲሆን "እንገነባዋለን" የተሰኘው ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻም ብራያን በሚባሉ ግለሰብ ነበር የተጀመረው።

እንደ ኒውዩርክ ግዛት አቃቤ ህግ ኦድሪ ስትራውስ ከሆነ፤ ባነንና ሌሎች ሶስት ግለሰቦች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለጋሾችን ግድቡን ለመገንባት በሚሊዮን ዶላሮች እንዲያዋጡ ቢያደርጉም፣ የግል ፍላጎታቸውን በማስቀደም እና፤ "የሚሰበሰበው ገንዘብ ሁሉ ለግንባታው ይውላል በሚል በመዋሸት አጭበርብረዋል።"

ስቲቭ ባነን በሚቆጣጠሩት አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በኩል ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀብለዋል፤ ቢያንስ ደግሞ "በመቶ ሺዎች የሚቇጠር ዶላር ለግል ጥቅማቸው ወጪ አድርገዋል" ሲል የፍትህ ቢሮው አስታውቋል።

የ 'እንገነባዋለን' ዘመቻ መስራች ሆኑት ብራያን ኮልፋግ በበኩላቸው 350,000 ዶላር ለግልጥ ቅማቸው ማዋላቸውን መግለጫው ያመለክታል።

ከ እንገነባዋለን ድረገጽ ተወሰደ ምስል

የፎቶው ባለመብት, We Build the Wall

የምስሉ መግለጫ, በዘመቻው ግለሰቦችን "ጡብ ይግዙ" በማለት ይቀሰቀስ ነበር

አቃቤ ህግ ስትራውስ "የእንገነባዋለን ዘመቻ መስራችና ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑት ብራያን ኮልፋግ ሰባራ ሳንቲም እንዳልተከፈላቸው ቢናገሩም፣ በምስጢር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ለተቀናጣ ኑሯቸው መደጎሚያ እንዲውል አድርገዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

አራቱ ተከሳሶች ወንጀላቸውንም ለመደበቅ "ለህግና ለእውነት ደንታ ቢስ ሆነው ከለጋሾች የሚሰበሰበውን ገንዘብ በተጭበረበረ ሰነድ ይሰበስቡ ነበር" ያሉት ደግሞ ጉዳዩን በመመርመር ላይ የተሳተፉት ፍሊፕ አር ባርትሌት ናቸው።

"ይህ ለሌሎች አጭበርባሪዎች ማንም ሰው ከህግ በላይ እንደማይሆን ትምህርት ሊሆን ይገባል፣ . . . ሚሊየነር የፖለቲካ ስልት ነዳፊ ቢሆንም" ብለዋል።

አራቱም ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል እስከ 20 ኣመት ድረስ በእስራት የሚያስቀጣ ነው።

የ66 ዓመቱ ስቲቭ ባነን ኒውዮርክ ሌሎቹ ደግሞ ፍሎሪዳ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ ይሆናል።