ሰሜን ኮርያ፡ ኪም ጆንግ ኡን ለእህታቸው ዮ ጆንግ 'በርካታ ኃላፊነቶችን" ሰጡ

ኪም ዩ ጆንግ የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ታናሽ እህት ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ዩ ጆንግ የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ታናሽ እህት ናቸው

የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን፣ ለታናሽ እህታቸውና ለቅርብ ረዳታቸው በርካታ ኃላፊነቶችን መስጠታቸውን የደቡብ ኮርያ የስለላ ኤጀንሲ ገለፀ።

ኪም በሰሜን ኮርያ ውስጥ አሁንም "ፈላጭ ቆራጩ" ቢሆኑም ያለባቸውን የሥራ ጫና ለመቀነስ በሚል የተለየዩ የፖሊሲ ጉዳዮችን ለሌሎች መስጠታቸውን የደቡብ ኮርያ ስለላ ኤጀንሲ ጨምሮ ገልጿል።

ብሄራዊ የደህንነት አገልግሎቱ አክሎም ኪም ጆንግ ኡን " አጠቃላይ የአገሪቱን ጉዳይ የሚያስኬዱት ራሳቸው ናቸው" ብሏል።

ይሁን እንጂ የደቡብ ኮርያ የስለላ ድርጅት ከዚህ ቀደም ስለ ሰሜን ኮሪያ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች ስህተት ይሰራ ነበር።

የደቡብ ኮርያ ብሄራዊ ጉባዔ ሐሙስ እለት ዝግ ስብሰባ ካደረገ በኋላ የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳው፣ የሰሜን ኮርያው ፕሬዝዳንት ለታናሽ እህታቸውና ለቅርብ ረዳታቸው የተለያዩ ትልልቅ የሚባሉ ኃላፊነቶችን ሰጥተዋል።

የሕግ አውጪዎች ይህንን ሪፖርት ተከትሎ ከጋዜጠኞች ጋር ተወያይተዋል።

" ኪም ጆንግ ኡን አሁንም የፈላጭ ቆራጭነቱን ስፍራ እንደያዙ ነው፣ ነገር ግን የተወሰነውን ስልጣናቸውን ቀስ በቀስ ለሌሎች እያስረከቡ ነው" ኤጀንሲው ማለቱ ተዘግቧል።

ታናሽ እህታቸው ወይዘሪት ኪም ፒዮንግያንግ አሜሪካ እና ደቡብ ኮርያ ላይ የምትከተለውን ፖሊስ እንዲሁም ሌሎች የፖሊሲ ጉዳዮችን ጨምራ በበላይነት ትመራለች።

በተጨማሪም ምንም እንኳ ፕሬዝዳንቱ የሚተካቸውን በይፋ ያልመረጡ ቢሆንም የፕሬዝዳንቱ ቀኝ እጅ እና "ሁለተኛዋ መሪ" ሆና እንደምትታይ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ኪም እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት " ያለባቸውን ጫና ለመቀነስ እንዲሁም ፖሊሲዎች ባይሳኩ ከተጠያቂነት ራሳቸውን ገለል ለማድረግ" እንደሆነ ተገልጿል።

ነገር ግን የደቡብ ኮርያ ደህንነት መሥሪያ ቤት መረጃን ደረት ተነፍቶ እምነት የሚጣልበት ነው ማለት ለስህተት ያጋልጣል የሚሉ ወገኖች አሉ።

እንደውም ከመሾም ይልቅ በዚህ ወር ሁለት ወሳኝ ስብሰባዎች ላይ አለመገኘቷን በመጥቀስ፣ ከነበራት ኃላፊነትም ዝቅ ብላ እንድትሰራ ሳይደረግ አይቀርም የሚሉ የሰሜን ኮርያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች አሉ።

ኪም ዮ ጆንግ ማን ናት?

ኪም ጆንግ ኡን እና ኪም ዮ ጆንግ በጣም ቅርብ መሆናቸው ይነገራል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ጆንግ ኡን እና ኪም ዮ ጆንግ በጣም ቅርብ መሆናቸው ይነገራል

የኪም ጆንግ ኡን ታናሽ እህት ሆነችው ኪም ዮ ጆንግ፣ የፕሬዝዳንቱ በጣም ቅርብ እና ተሰሚነቷ ጠንካራ የሆነ አጋሩ ናት ትባላለች።

እኤአ በ1987 የተወለደች ሲሆን ከፕሬዝዳንት ኪም በአራት ዓመት ታንሳለች።

ሁለቱ ወንድምና እህት በተመሳሳይ ሰዓት በስዊዘርላንድ በርን ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ወይዘሪት ኪም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብን ትኩረት ውስጥ የገባችው በ2018 ሲሆን ከቤተሰቦቿ መካከል ደቡብ ኮርያን በመጎብኘት የመጀመሪያዋ ናት።

ደቡብ እና ሰሜን ኮርያ በጋራ የተሳተፉበት የክረምት ኦሎምፒክ ላይ የልዑካን ቡድኑ ወደ ደቡብ ኮርያ ሲያመራ አባል ነበረች።

ከወንድምዋ ጎን በመሆንም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ላይ ተሳትፋለች፣ ይህ ስብሰባ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናውና የደቡብ ኮርያው አቻዎቻቸው ወንድሟን ያገኙበትንም ወቅት ያካትታል።

Presentational grey line

የደቡብ ኮርያ የስለላ ድርጅት ምን ያህል ይታመናል?

ሰሜን ኮርያ ሁሉ ነገሯ ምስጢር የሆነ አገር ናት።

የደቡብ ኮርያ ደህንነት ተቋም ከማንኛውም አገር በተሻለ ስለ ሰሜን ኮርያ መረጃ ሊኖረው እንደሚችል ይታወቃል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ሁለት መልክ ያለው ታሪክ ነው ያለው።

ለምሳሌ በ2016 የደቡብ ኮርያ መገናኛ ብዙኀን በደህንነት ተቋሙ ያገኙትን መረጃ ተጠቅመው የጦር ኃይል ኢታማዦር ሹሙ ሪ ዮንግ ጊል ተገደሉ ብለው ዘገቡ።

ከሶስት ወር በኋላ፣ የደቡብ ኮርያ መንግሥት በሕይወት መኖራቸውን አረጋግጫለሁ ብሎ ተናገረ።

በ2017 ደግሞ ደቡብ ኮርያ የ2012 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ለመለወጥ ሙከራ አድርጋ እንደነበር ገልጿል።