ባይደን በመጀመሪያ ቀናቸው አወዛጋቢ የተባለውን የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ፕሮጀክት ይሰርዛሉ ተባለ

ኪስቶን ኤክስኤል የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በነገው ዕለት በዓለ ሲመታቸውን የሚፈፅሙት ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በስልጣን የመጀመሪያ ቀናቸው አወዛጋቢ የሆነውን ኪስቶን ኤክስ ኤል የተባለውን የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ፕሮጀክት እንደሚሰርዙ የአሜሪካ ሚዲያዎች ሪፖርት አድርገዋል።

የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧው ፕሮጀክት አልሞ የነበረው የካናዳዊቷን ግዛት አልበርታንና የአሜሪካን ኔብራስካን ግዛትን የሚሸፍን 1 ሺህ 900 ኪሎሜትር እርዝማኔ እንዲኖረው ታቅዶ ነበር።

የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች እንዲሁም ቀደምት አሜሪካውያን ይህ ፕሮጀክት እውን እንዳይሆን ለአስር አመታት ያህል ታግለዋል።

ፕሮጀክቱ በነበረበትም ጫና በተወሰነ መልኩ ስራዎች ተቋርጠው የነበረ ቢሆንም ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት አመታት በፊት እንዲጀመር አድርገውታል።

ከትራምፕ በፊት በስልጣን ላይ የነበሩት ባራክ ኦባማ የማስተላላፊያ ቧንቧ ግንባታ ስራ እንዲቋረጥ የሚያዘውን ህግ በከፍተኛ ድምፅ እንዲፀድቅ ቢያደርጉም ትራምፕ ያንን ውሳኔ ቀልብሰውታል።

የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ፕሪጀክቱ 8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያስወጣልም ተብሎ ነበር።

ባይደን ምን ሊሰሩ አቅደዋል?

ከተመራጩ ፕሬዚዳንት ቢሮ የተገኘ ደብዳቤ አይነተናል ያሉት የካናዳና አሜሪካ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ጆ ባይደን በበዓለ ሲመታቸው ቀን የኪስቶን ኤክስኤል ነዳጅ ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ፈቃድን ለመሰረዝ ፍፁማዊ ስልጣናቸውን እንደሚጠቀሙ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የካርበን ልቀትን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የተፈረመውን አለም አቀፉን የፓሪስ ስምምነት አገራቸው እንድትመለስ ያደርጓታል።

ትራምፕ ከአለም አቀፉ የፓሪስ ስምምነት አገራቸውን ያስወጧት በያዝነው አመት ህዳር ወር ላይ ነበር።

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የአየር ንብረት ለውጥን መታገል አስተዳደራቸው የሚያስቀድመው ዋነኛ ተግባር ነው በማለትም አስምረዋል ።

ከነዳጁ ማስተላለፊያ ቧንቧ ጋር በተያያዘም የአልበርታው መሪ ጃሰን ኬኒ የጆ ባይደን እቅድ ከፍተኛ ስጋት እንዳጨረባቸው ገልፀው የቧንቧ ዝርጋታው ፕሮጀክት የሚታጠፍ ከሆነ መንግሥታቸው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስበዋል።

የኪስቶን ኤክስኤል የነዳጅ ቧንቧ 830 ሺህ በርሜል ያልተጣራ የነዳጅ ድፍድፍ ከአልበርታ ወደ ኔብራስካ እንዲያስተላልፍ ታቅዶ ነበር። ኔብራስካም ከደረሰም በኋላ እዚያው ያለው የማስተላለፊያ ቧንቧ ጋር በማገናኘት ሜክሲኮ ገልፍ ወዳለው ማጣሪያ ቦታም ይወሰዳል።

የአልበርታ ነዳጅ ከአሸዋ፣ ውሃ፣ ሸክላ ጋር የተቀላቀለ በይዘቱም ወፈር ያለ ሲሆን፤ ነዳጁንም ለማጣራት ከፍተኛ የሆነ ኃይል ጉልበትና ወጪውም ጣራ የነካ እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህም የተነሳ እንደ ግሪን ፒስ ያሉ የአካባቢ መብት ጥበቃ ተሟጋቾች ከዚህ ነዳጅ የሚለቀቀው ጋዝ በተለምዶ ከሚታወቀው 30 በመቶ ጭማሬ አለው ይላሉ።

ነገር ግን የካናዳ መንግሥት በበኩሉ ከባቢን በማይጎዳና ኃይልንም በማይጨርስ መልኩ ማጣራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ አለ በማለት ይከራከራል።

ቀደምት የአሜሪካ ህዝቦች በበኩላቸው የአልበርታን አካባቢ እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱን ድፍድፍ ነዳጅ ለማውጣት በሚል ለ15 አመታት ላደረሱት ጉዳት ከሰዋል።

ሰርተው የሚበሉበትንና መሬታቸውን ያለነሱ ፈቃድ ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጎታልም በማለት ይከሳሉ።