ኮሮናቫይረስ፡ ጆ ባይደን የትራምፕን ትዕዛዝ በመተላለፍ የኮቪድ-19 ጉዞ ገደብ እንደሚቀጥል አስታወቁ

መንገደኞች በቺካጎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በነገው ዕለት ስልጣን የሚረከቡት የአሜሪካው ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቃል አቀባይ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአውሮፓ ህብረትና በብራዚል የተጣለው የጉዞ ገደብ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፉት የጉዞ ገደቡ ይነሳ የሚለውን የተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ትራምፕን ትዕዛዝ በመተላለፍ ነው።

በያዝነው ሳምንት ሰኞ ዋይት ሃውስ የጉዞ ገደቡ ጥር 18፣ 2013 መነሳት አለበት የሚል ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ይህም ማለት ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ስልጣን ከያዙ ከስድስት ቀናት በኋላ ማለት ነው።

ነገር ግን የጆ ባይደን ቃለ አቀባይ ጄን ፕሳኪ በበኩላቸው ወቅቱ የጉዞ ገደብ የሚላላበት አይደለም በማለት በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

የ ጆ ባይደን በዓለ ሲመት በነገው እለት ጥቅምት 12፣ 2013 ዓ.ም ይፈፀማል።

አሜሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ለመግታት በሚል አውሮፓ ላይ የጉዞ ገደብ የጣለችው በባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ሲሆን በብራዚል ደግሞ ግንቦት ወር ላይ ነበር።

"የጤና ባለሙያዎቻችን በመከሩን መሰረት አዲሱ አስተዳደር የተጣለውን የጉዞ ገደብ በጥር 18 አያነሳም" በማለትም ቃለ አቀባይዋ የፕሬዚዳንት ትራምፕ የጉዞ እገዳ ይነሳ የሚለው ውሳኔ እንደተላለፈው ወዲያውኑ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

"በመሰረቱ የማህበረሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ እቅድ አለን። የኮቪድ-19 ስርጭትንም ለመግታት አለም አቀፍ ጉዞዎችን በጥብቅ እንቆጣጠራለን" ያሉት ቃለ አቀባይዋ

አክለውም " በተለይም የተለያዩ አይነት አዳዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች እተከሰቱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት አለም አቀፍ ጉዞዎች የሚላሉበት አይደለም" ብለዋል።

ቃለ አቀባይዋ ይህንን መልዕክት ከማስተላለፋቸው ከደቂቃዎች በፊት ዋይት ሃውስ በዩናይትድ ኪንግደም፣ አየር ላንድ፣ የአውሮፓ አገራትና ብራዚል ላይ የተጣለው የጉዞ ገደብ ጥር 18 እንዲነሳ የሚያዘውን የተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ በመግለጫው አውጥቶ ነበር።

ውሳኔው አክሎም በቻይናና በኢራን ላይ የተጣለው የጉዞ ገደብም ይቀጥላል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካው የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) ባወጣው አዲስ መመሪያ መሰረት ከጥር 18 ጀምሮ ማንኛውም አለም አቀፍ መንገደኛ ነፃ የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት ሊያሳይ ይገባል።