ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ፡ የፑቲን ባላንጣ አሌክሴ አገሩ ሲገባ "የእስር አቀባበል" ተደረገለት
የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን የሰላ ተቺ ነው የሚባለው አሌክሴ ናቫልኒ ታሰረ። አሌክሴ የታሰረው ከጀርመን ወደ ሩሲያ በገባበት ቅጽበት ነው።
አሌክሴ በአደገኛ መርዝ የግድያ ሙከራ ተደርጎበት በተአምር ከተረፈ ወዲህ ነው በድጋሚ ወደ አገሩ ሩሲያ የተመለሰው።
ብዙዎች አሌክሴ ወደ ሩሲያ ከተመለሰ ሊገደል ስለሚችል ሐሳቡን እንዲቀይር ቢወተውቱትም እሱ ግን አሻፈረኝ ብሏል።
የ44 ዓመቱ አሌክሴ ናቫልኒ ልክ ሼርሜትዯቮ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርስ፣ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎታል። አብራው የነበረችው ሚስቱን ጉንጮቿን ስሞ በፖሊስ ታጅቦ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስዷል።
አሌክሴ ወደ ሩሲያ ለመመለስ ሲወስን በሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ በሞስኮ አየር ማረፍያ በጉጉት ሲጠብቁትና ደማቅ አቀባበል ሊያደርጉለት ነበር። ሆኖም እሱ የተሳፈረበት ከጀርመን የተነሳው አውሮፕላን አቅጣጫውን እንዲቀይር ተገዷል።
ይህም ከደጋፊዎቹ ጋር እንዳይገናኝ የሩሲያ ባለሥልጣናት ያደረጉት ነው።
የቭላድሚር ፑቲን ተቀናቃኝ አሌክሴ ከ5 ወራት በፊት የመረዙኝ እሳቸው ናቸው ይላል። ክሬምሊን በበኩሉ እጄ የለበትም ሲል ያስተባብላል።
አሌክሴ በአደገኛ የነርቭ መርዝ መመረዙን የጀርመን ሐኪሞች አረጋግጠዋል። ይህን ሊያደርጉ አቅሙ ያላቸው ቭላድሚር ፑቲንና አስተዳደራቸው ብቻ ስለመሆኑ ደግሞ በርካታ የምርመራ ጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።
የአሌክሴ ናቫልኒ ወደ ሩሲያ መመለስ ዓለምን ያስገረመ ጉዳይ ሆኖ የሚጠበቀው እስሩ እንደተሰማ ግን የአውሮጳ ኅብረት፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ሌሎች በርካታ አገሮች ድርጊቱን አውግዘዋል።
ከሰሞኑ ነጩ ቤተ መንግሥት የሚገቡት 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተመራጭ ጆ ባይደን የመረጧቸው የደኅንነት አማካሪ ጃክ ሰሊቫን፣ የሩሲያ ድርጊት ያፈጠጠ የሰብአዊ መብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን የሩሲያን ሕዝብ ድምጽ የማፈን ተግባር ነው ሲሉ ኮንነዋል።
አሌክሴ ባለፈው ነሐሴ ወር የአገር ውስጥ በረራ ላይ ሳለ አውሮፕላን ውስጥ ራሱን ሲስት፣ በሰርቢያ ሕክምና ከጀመረ በኋላ ወደ ጀርመን ለተሻለ ሕክምና ተወስዶ ነበር። በርካቶች ግን ሕይወቱ ትተርፋለች አላሉም።
ሆኖም ውጤታማ ሕክምና አድርጎ ነፍሱ ከተመለሰች በኋላ ትናንት እሑድ ወደ ሩሲያ ሲሳፈር ብዙዎችን አስደንግጧል።
እሱ ወደ ሩሲያ የተሳፈረበት አውሮፕላን በርካታ ጋዜጠኞች ተሞልቶ ነበር። የኛ የቢቢሲ ዘጋቢ አንድሬ ኮዜንኮ ከተሳፋሪዎቹ አንዱ ነበር።
ልክ አውሮፕላኑ ሊያርፍ ሲቃረብ ግን ፓይለቱ "የቴክኒክ ችግር ስለገጠመን" በሚል ከቭኑኮቮ አየር ማረፍያ ወደ ሼርሜትየቮ መዳረሻችንን ቀይረናል ሲል አስታውቋል።
አሌክሴ አየር ማረፍያው እንደደረሰ ፖሊሶች ሲከቡት "ብዙ አስጠበቅኳችሁ እንዴ ሲል መቀለዱ ተዘግቧል።