ማኅበራዊ ሚዲያ፡ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች ወደ ቴሌግራም ለምንድን ነው እየፈለሱ ያሉት?

ለመልዕክት ደኅንነት አስተማማኝ እንደሆነ ሲነገርለት የቆየው ዋትስአፕ የተሰኘው መተግሪያ በአጠቃቀም ደንብና መመሪያው ላይ ለውጥ ማድረጉን ተከትሎ በርካታ ተጠቃሚዎች ወደ ሌሎች አማራጭ መተግበሪያዎች እያማተሩ ነው።

ዋትስአፕ በዓለም ዙሪያ ሁለት ቢሊዮን ያህል ተጠቃሚዎች እንዳሉት የሚነገር ሲሆን ተጠቃሚዎች የሚለዋወጧቸው መልዕክቶች ምስጢራዊነታቸው ከየትኛውም ወገን የተጠበቀና አስተማማኝ እንደሆነ ስለሚታመን በርካታ ተጠቃሚን ማፍራት ችሎ ነበር።

ነገር ግን በቅርቡ ዋትስአፕ የተጠቃሚዎቹን ግላዊ መረጃዎች ለሚያስተዳድረው ፌስቡክ እንደሚያጋራ በመጥቀስ የአጠቃቀም ደንቡና መመሪያውን እንዳሻሻለ አሳውቆ፤ በዚህ የሚስማማ አብሮት እንዲቀጥል ካልሆነም መተግበሪያውን መተቀም እንዲያቆም አስከ የካቲት መጀመሪያ ሳምንት ድረስ ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር።

ይህ ውሳኔ ከብዙዎች ዘንድ ተቃውሞና ትችትን ያስከተለበት ዋትስአፕ ውሳኔው እንደማይለወጥ በመግለጽ ነገር ግን የተቀመጠው የጊዜ ገደብ እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ እንሚቆይ ገልጿል።

ግላዊ መረጃቸውና የሚለዋወጡት መልዕክት ደኅንነት ያሰጋቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች አማራጭ መተግበሪያዎችን በመፈለግ ወደዚያው እያቀኑ ነው፤ በተለይ ሲግናልና ቴሌግራም የተባሉት የመልዕክት መለዋወጫዎች የተጠቃሚያቸው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው ተብሏል።

ይህ መሆኑ ለምን ያሳስበናል? የግል መረጃዎቻችንን ደኅንነትስ እንዴት መጠበቅ አለብን? የዘርፉ ባለሙያ ከሆነችው ብርሃን ታዬ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ብርሃን ታዬ 'አክሰስ ናው' በሚባል ሲቪክ ማኅበራት ውስጥ የአፍሪካ ፖሊሲ ማናጀር ናት። ድርጅቱ ሰዎች ከኢንተርኔት ውጭ መብት እንዳላቸው ሁሉ ኢንተርኔት ሲጠቀሙም መብቶቻቸው [ዲጂታል ራይትስ] እንዲከበር ይሰራል።

ብርሃን ያጠናችው ፖለቲካ ሳይንስና ሰብዓዊ መብት ትምህርት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ናይሮቢ በሚገኘው ስትራትሞር ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ አጥኝ ናት።

ቢቢሲ፡ ዋና ዋና የሚባሉት የማበራዊ ሚዲያ መድረኮች የትኞቹ ናቸው?

ብርሃን፡ በዓለም ላይ ዋና ዋና የሚባሉት የማኅበራዊ ድረ ገፆች ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም ሲሆኑ ሦስቱም በፌስቡክ ድርጅት ስር የሚተዳደሩ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ትዊተርና ዩቲዩብ ወደ ቻይና ስንሄድ ደግሞ የራሳቸው የሆነው ዊቻትንና ቲክቶክን መጥቀስ ይቻላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው የሚጠቀመው ፌስቡክን ነው። ፌስቡክ በኢትዮጵያ ከ6 እስከ 8 ሚሊዮን ተጠቃሚ አለው ተብሎ ይገመታል። የትዊተር ተጠቃሚዎች ግን ከ200 ሺህ እንደማይበልጡ ይነገራል።

ኢትዮጵያ ውስጥ አዲሱ መንግሥት ከመጣ በኋላ የመንግሥት ባለሥልጣናት ትዊተር መጠቀም ሲጀምሩ ተጠቃሚው ወደ ትዊተር እየሄደ ነው።

በርካታ የአፍሪካ አገራት ዋትስ አፕን ሲጠቀሙ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ብዙ ሰው የሚጠቀመው ቴሌግራምን ነው። ይሁን እንጂ የዋትስአፕ ተጠቃሚም እያደገ ነው።

ሌላ አንድ 'ሲግናል' የሚባል የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያም አለ። ይህ መተግበሪያ ከሌሎቹ የሚለየው መተግበሪያው የሚተዳደረው በበጎ አድራጎት ድርጅት አሊያም ለትርፍ በማይሰራ ድርጅት መሆኑ ነው።

ቢቢሲ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሰው የቴሌግራም ተጠቃሚ የሆነበት ምክንያት ምንድ ነው?

ብርሃን፡ምክንያቱ ይሄ ነው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። ገበያው መጠናት አለበት። እንደማስበው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቡድኖች አሉ። ቡድኑ ለማንም ክፍት ነው። በመሆኑም ብዙ ሰው ቴሌግራም የሚጠቀመው መተግበሪያው ብዙ ፊቸሮች [የምንፈልገውን ማድረግ የሚያስችሉን ነገሮች] ስላሉት እና ለሰው ደስ ስለሚለው ይመስለኛል።

ለምሳሌ በዋትስ አፕ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ ቡድን ውስጥ መኖር የሚችለው የሰው ቁጥር እስከ 250 ሰው ብቻ ነው። ቴሌግራም ግን እስከ 100 ሺህ ሰው ድረስ አንድ ቡድን ውስጥ ማካተት ይችላል። በዚህ ምክንያት ተመራጭ የሆነ ይመስለኛል።

ቢቢሲ፡ በመላው ዓለም 2.2 ሚለን አካባቢ የዋትስአፕ አዲስ ተጠቃሚዎች ወደ ሌሎች መተግበሪያዎች ፈልሰዋል ተብሏል። በትክክል ምንድን ነው የተፈጠረው?

ብርሃን፡ በፈረንጆች ጥር ስድስት ላይ ዋትስአፕ የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ ደኅንነት እንዴት እንደሚጠብቁ አዲስ ደንብ አውጥቷል።

ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራምና ፌስቡክ የሚመሩት በአንድ ድርጅት ማለትም በፌስቡክ ነው። ታዲያ በዚህ ፖሊሲ ላይ ሰዎች በ'ፋየር ፎክስ'፣ 'ኢንተርኔት ኤክስፕሎለር'፣ ጉግል ክሮም ላይ የመረጃ አሰሳ [ሰርች] ታሪክ መረጃ፤ ዋትስአፕ የምንጠቀምበት ቋንቋ፣ ያለንበትን አገር ሰዓት፣ የኢንተርኔት አድራሻ [የአይፒ አድራሻ]፣ የምንጠቀመው የሞባይል ኔትወርክ ፣ ኢንተርኔት አገልግሎቱን ከየት እንዳገኘን እና ሌሎች መረጃዎችን ለኢንስታግራምና ለፌስቡክ አጋራለሁ በማለቱ ነው ይህ የሆነው።

ለምሳሌ፡ የፌስቡክ አካውንት ከፍተን ስንጠቀም ለቤት ውስጥ ብቻ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት የኢንተርኔት ቁጥርን [አይፒ አድሬስ ]ይሰጣል። በመሆኑም በዚህ ኢንተርኔት ዋትስአፕ የምንጠቀም ከሆነ ፌስቡክና ዋትስአፕ መረጃዎች ሲቀባበሉ፤ እኛ እንደሆንን ያውቁናል።

በዚህም ፌስቡክ ላይ ሼር የሚደረገው መረጃ ዋትስአፕ፤ ዋትስአፕ ላይ የሚጋራውን መረጃ ፌስቡክ ያውቀዋል ማለት ነው። በመሆኑም ሰው ለቆ እየወጣ ያለው ለዚህ ነው።

ድርጅቱም ከመጪው የካቲት ስምንት ጀምሮ መረጃዎችን እናጋራለን፤ የማትፈልጉ ከሆነ የእኛን መተግበሪያ ለቅቃችሁ መውጣት ትችላላችሁ ብሏል።

ቢቢሲ፡ ይህ መሆኑ ለምን ያሳስበናል? መረጃዎቻችንን ቢጋሩት ለምን እንፈራለን?

ብርሃን፡በምድር ላይ 53 በመቶው ሕዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው። ብዙዎቻችን ለትምህርትም ሆነ ለሥራ ጊዜያችንን የምናጠፋው ኢንተርኔት ላይ ነው።

ሕይወታችን ወደ ዲጂታል እየተቀየረ ነው። ስለዚህ አንድ የግል የሆነ፣ ለትርፍ የሚሰራ ድርጅት ይህን ሁሉ ግላዊ መረጃ ያውቃል።

የእኛን ግላዊ የሆነና ለሁሉም ሰው የማናጋራውን መረጃ ስንልክ፤ ያን በመሰብሰብ ከዚያ ጋር የሚገናኝ ማስታወቂያ ይላካል። የእኛን ሃሳብ የሚያስቀይር ማስታወቂያ ይላካል።

በተዘዋዋሪ ይህ መረጃ ተሰብስቦ ይሸጣል ማለት ነው። ፌስቡክ ገንዘብ የሚያገኘው ወይም በነጻ አገልግሎት ሰጠን የምንለው ምርቱ እኛ ስለሆንን ነው።

ለምሳሌ፡ ጫማ መግዛት እንደምንፈልግ ለጓደኛችን ጽፈን ከሆነ ይህን የግል መረጃ በመያዝና እኛን በመከታተል የጫማ ማስታወቂያዎችና ከዚህ ጋር የተያያዙ መረጃዎች ይላካሉ። ዕድሜያቸው ከ25-30 የሆኑ ከዚህ በፊት አዲስ ጫማ የገዙ እነማን ናቸው? በሚል ተፈልገን ሳንፈልግ ማስታወቂያዎች በገጻችን በኩል ይላካሉ።

የዚህ ውጤት በማስታወቂያ ብቻ ሳይሆን በምርጫ ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድርም ታይቷል። አንድ የግልና ትርፋማ ድርጅት የእኛን መረጃ ነው እየሰበሰበ የሚሸጠው።

ቢቢሲ፡ እነዚህ መተግበሪያዎች ስንጠቀም አንከፍልም። ለምንድን ነው ውለታ የሚውሉልን?

ብርሃን፡ ደግ ሆነው ሳይሆን እኛ ደግ ሆነን ነው። ፌስቡክ በቢሊየን ዶላር እያወጣ አፍሪካዊያን በኢንተርኔት አገልግሎት እንድንተሳሰር ይሰራል። ሌሎችም እንዲሁ።

ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ወደውን ወይም አፍቅረውን አይደለም። ከእኛ የሚያገኙት መረጃ ስለሚሸጥ ነው። ስለዚህ በነፃ የሚሰጡን ይመስለናል እንጂ የሚሸጠው የእኛው መረጃ ነው። ፌስቡክ የሚሰራው ማስታወቂያ በመሸጥ ነው።

ዓለም ላይ ያሉ ድርጅቶች በፌስቡክ ምርቶቻቸውን ያስተዋውቃሉ። ስለዚህ ፌስቡክ ገንዘቡን የሚያገኘው እኛ ቁጭ ብለን ስለምናይለት ነው። ከሌሎች ማስታወቂያዎች ለየት የሚያደርገውም ፌስቡክ ላይ የሚሰራው ማስታወቂያ ለእያንዳንዱ ሰው ተብሎ ተቀርጾ መሰራቱ ነው።

ለምሳሌ የሆነ ጊዜ መኪና ስለመግዛት ከጓደኛችን ጋር ተጻጽፈን ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ይህን መረጃ በመያዝ በግል ገጻችን ላይ የምናየው ማስታወቂያ ስለ መኪና ይሆናል። ልክ እንደሌሎቹ ማስታወቂያዎች ለጠቅላላው ሕዝብ የተሰሩ አይደሉም።

ቢቢሲ፡ ከእነዚህ መተግበሪያዎች ውጪ ኢንተርኔት ላይ ሌሎች መረጃዎችን ስንፈልግም፤ ከፈለግነው መረጃ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሌሎች መረጃዎች ይመጣሉ። ለምንድን ነው?

ብርሃን፡መረጃውን ለመፈለግ የገባንበት ድረ ገጽ ላይ ኩኪዎች የሚባሉ አሉ። ልክ ጫማችን አቧራ ነክቶ ቤት ውስጥ ስንገባ የጫማ ዱካችን ቤቱ ወለል ላይ ይቀራል። ቤቱን ለቀን ብንሄድም ዱካው ያስታውቃል። በመሆኑም ሌላ መተግበሪያዎችን ስንከፍት ዱካችንን [ከዚህ በፊት ያሰስነውን] ይፈልጋሉ።

ከዚህ በፊት ከፍተን ያየነውን ነገር ድረ ገጾቹ እርስ በርስ ይነጋገራሉ። "ከዚህ በፊት የፈለጉት ይህ ነበር። የሚያሳስባቸው ጉዳይ ይህ ነው" በማለት መረጃ ይለዋወጣሉ። ስለዚህ የሚመጣው በየቦታው ዱካ እየጣልን የሄድነው ነው።

ቢቢሲ፡ የመብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች መንግሥት ክትትል የሚያደርግባቸው አካላት ይህ ጉዳይ ያስጨንቃቸዋል። የመረጃ መለዋወጫ መንገዶቻቸውንም ይመርጣሉ። እንደ ማበረሰብ መረጃዎቻችንን ቀላል ዋጋ እየሰጠን እንዳናጋራ የትኛውን መተግበሪያ መጠቀም አለብን? ሌሎች ማድረግ ያሉብን መሰረታዊ ጥንቃቄዎችስ?

ብርሃን፡የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞች ሲሆኑ እነሱ ጋር ያለው አደጋ ከሌላው ኅብረተሰብ የተለየ ነው። እነሱ የተለየ መፍትሔ ነው መፈለግ ያለባቸው። ነገር ግን ሁላችንም እንደዜጋ ማሰብ ያለብን ብዙዎቻችን ስልካችንና ኮምፒዩተራችን ላይ መሆናችንን ነው። ስለዚህ የምንተወው መረጃ በጣም አሳሳቢ ነው።

መንግሥት ከፈለገ የአንድን ሰው የቀን ውሎ ማወቅ ይችላል። መተግበሪያዎቹ እኛ የማናስታውሰውን መረጃ እንኳን ይዘው ነው የሚቀመጡት። ለምን ያህል ጊዜ ይዞ እንደሚቆይ አናውቅም። ስለዚህ የምናጋራው መረጃ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ከዚህም ባሻገር በየትኛውም ዘመናዊ ስልክ የደኅነንት መጠበቂያዎች አሉ። ለምሳሌ አንድን መተግበሪያ ወደ ስልካችን ስናወርድ እኛ ያለንበትን ቦታ መረጃ እንድናጋራ ይጠይቃል። ስለዚህ ስናወርድ ግድ ሲሆን ብቻ ነው ይህን የማደርገው የሚለውን መምረጥ አለብን።

ሌላኛው የሰውን የግል መረጃ የሚጠብቅና የሚከላከለው 'ሲግናል አፕ' መረጃ ለመለዋወጥ ጥሩ አማራጭ ነው። የሚያስተዳድረው ድርጅት ለትርፍ ያልተቋቋመ በመሆኑ የእኛን መረጃ አይፈልግም።

በተጨማሪም የኢሜይል እና የሌሎች መተግበሪያዎችን የይለፍ ቃል [ፓስወርድ] ተመሳሳይ አለማድረግም ይመከራል።