ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዋትስአፕን መተው ለስልክዎ ደህንነት ይመከራል?
ዋትስአፕ የተሰኘው የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያን መረጃ መዝባሪዎች እየተጠቀሙበት እንደሆነ ያመነው በቅርቡ ነበር። ይህን ተከትሎ በርካቶች ዋትስአፕን ከዚህ በኋላ አንጠቀምም ሲሉ ቃል ገብተዋል። ባለሙያዎች ግን ለስጋትዎ ምላሹ ይህ አይደለም ይላሉ።
'ስፓይዌር' የመረጃ መዝባሪዎች ዋትስአፕ እና መሰል መተግበሪያዎችን ተጠቅመው የተጠቃሚዎችን መረጃ የሚመዘብሩበት ዘዴ ነው። ታድያ ዋትስአፕ ለዚህ የመረጃ ዝርፊያ ተጋልጫለሁ ካለ በኋላ በተለይ ህንድ ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎች ዋትስአፕን ከስልካቸው መንቀል [አንኢነስቶል] ማድረግ ተያያዙ።
የህንድ መንግሥት ያለስሜ ስም አትስጡኝ ሲል ቢቃወምም፤ አንዳንዶች እንደውም 'መንግሥት ከሚፈልጋቸው ሰዎች መረጃ መውሰድ ስለፈለገ ነው፤ እጁ አለበት' ሲሉ ጣታቸውን ቀሰሩ።
ከዋትስአፕ ይልቅ ሲግናል እና ቴሌግራም የተባሉት መተግበሪያዎች መረጃችንን አሳልፈው አይሰጡም ያሉ ሰዎች ፊታቸውን ወደእነዚህ አማራጮች አዞሩ።
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለመያዎች ግን በዓለም ዙሪያ 1.6 ቢሊዮን፤ በህንድ ደግሞ 400 ሚሊዮን ገደማ ተጠቃሚዎች ያሉት ዋትስአፕ ለመረጃ ምዝበራው ተጠያቂ አይደለም ይላሉ።
በተለይ ደግሞ የዋትስአፕን የቪዲዮ መደዋወያ መላን በመጠቀም ነው መዝባሪዎቹ የተጠቃሚዎች ስልክ ውስጥ ካሉበት ሆነው የሚበረብሩት። ይህ ደግሞ ስልኩን ከሚዘውረው ሶፍትዌር ወይም ኦፕሬቲንግ ሲስተም ጉደለት ነው ባይ ናቸው ባለሙያዎች።
ዋትስአፕ ራሱን ሲያስተዋውቅ እጅግ ደህንነቱ የተጠበቀ በማለት ነው። ለዚሀ ምክንያቱ ደግሞ መልዕክቶቹን ማንበበት የሚችሉ የላኪና ተቀባይ ስልኮች ብቻ መሆናቸው ነው። ይህንንም በቴክኖሎጂው አጠራር 'ኢንክሪፕትድ' ይሉታል።
ነገር ግን ስፓይዌር የተሰኘው መመዝበሪያ ስልክዎ ውስጥ ከገባ 'ኢንክሪፕትድ' ሆነ አልሆነ ምንም ለውጥ አይመጣም። በዚህ መንገድ ስልክዎ ከተጠለፈ የጠላፊው እንጂ የእርስዎ አይደለም ማለት ይቀላል። ዋናው ችግር ያለው 'ኦፕሬቲንግ ሲስተሙ' ላይ ነው በማለት ባለሙያዎች ይከራከራሉ።
ታድያ ዋትስአፕን ትቶ ወደ ሌሎች የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ማምራት ይመከራል? ሌሎቹስ መተግበሪያዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ ነውን? "አይመስለንም"፤ የባለሙያዎቹ ምላሽ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ዋትስአፕ ከሌሎች የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ያነሰ ደህንነት አለው ብሎ ለማመን የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም ይላሉ ባለሙያዎቹ።