የኢትዮጵያውያን ድምጽ ከሪያድ እና ጅዳ እስር ቤቶች ውስጥ

በተለያዩ የሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ እንግልት እንደሚደርስባቸው በመግለጽ መንግሥት ወደ አገር ቤት እንዲመልሳቸው ተማጽኗቸውን አቀረቡ።

ጂዳ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት የሚገኙ ሦስት ኢትዮጵያውያን ስለሚደርስባቸው ስቃይ ለቢቢሲ የገለፁ ሲሆን፣ በየጊዜው በፖሊስ ድብደባ እንደሚደርስባቸው፣ በቂ ምግብ እንደማይሰጣቸው እና መታረዛቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።

ወደ አገራችን መልሱን የሚሉት እነዚህ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ቆንስላ መጥቶ የሚጠይቃቸው ማንም እንደሌለ፣ በአንድ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ቅጽ ቢሞሉም ከዚያ በኋላ ግን ማንም እንዳላነገራቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው በየሳምንቱ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከኩዌይት፣ ከሌባኖስ እና ከሌሎችም የአረብ አገራት ኢትዮጵያውያን እየተመለሱ መሆኑን ገልፀው እስር ቤት ያሉና ቆንስላው ያላገኛቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ኋላ እንደቀሩና እነርሱም በጊዜ ሂደት ወደ አገራቸው እንደሚገቡ አስረድተዋል።

ከየመን ወደ ሳዑዲ ከገባ በኋላ ተይዞ እስር ቤት መግባቱን የሚናገረው ጀማል አሁን ያለበትን ሁኔታ ሲያስረዳ "ልብስ የለንም፤ ወደ አገራችን ይልኩናል በሚል ምግብ አንበላም ስንል ወታደሮች እየመጡ ይደበድቡናል" ይላል።።

"ከትናንት ወዲያ በአንድ እግራችን አቁመው እየደበደቡን አረፈዱ። ከዚያ በኋላ እንድንበላ ሆንን። የሚመጣውም ምግብ ዝም ብሎ ነው። እንዳንሞትም እንዳንድንም ሆነን ነው ያለነው" ብሏል።

እስር ቤት ከገባ ስምንት ወር እንደሆነው የሚገልፀው ጀማል፣ "ሪያድ ከርጅ የሚባል ስፍራ ታስረን ከርመናል። ከዚያ አስወጥተው ሃየር በሚባል እስር ቤት ከወሰዱን በኋላ ወደ ጂዳ አምጥተውናል" በማለት ከሁለት ወር በፊት ከሪያድ ወደ ጅዳ መዛወሩን እና ሪያድ ውስጥ መያዙን ገልጿል።

በዚያው እስር ቤት የሚገኘው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አሚን፣ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደሚፈልግ ይናገራል። "ተስፋ ቆርጠናል" የሚለው አሚን ድምጻቸው ተሰምቶ ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት እንዲመልሰው ይፈልጋል።

አሚን ሪያድ ለአንድ ወር ከሪ ከርጅ እስር ቤት መታሰሩን ከዚያ በኋላም ሪያድ ውስጥ ሃይር በሚባል እስር ቤት ለአራት ወር ያህል ከታሰሩ በኋላ አሁን ወዳለበት መዘዋወሩንና ባለበት እስር ቤት ውስጥም ለሦስት ወር እንደቆየ ገልጿል።

የእስር ቤቱ ጠባቂ ፖሊሶችን የታመሙ ታሳሪዎች ወደ ህክምና እንዲወሰዱ በሚጠይቁበት ጊዜ እንደሚደበደቡ፣ ወደ አገር ቤት እንዲመልሷቸው በሚጠይቁበት ጊዜ "መንግሥታችሁ አይፈልጋችሁም" የሚል ቅስምን የሚሰብር ምላሽ እንደሚሰጧቸው ያስረዳል።

ጀማል በበኩሉ ሪያድ እስር ቤት ውስጥ ሳሉ "ከአስከሬን ጋር እንውላለን እናድራለን። አስከሬን እንኳ የማይነሳበት ወቅት ነው የነበረው። በሦስት ቀናችን ነበር አስከሬን ይነሳ የነበረው። ሰው ሆኖ መፈጠር ያስጠላ ነበር" በማለት የቆይታቸውን አስከፊነት ለቢቢሲ ገልጿል።

ሌላው ከታሰረ ስምንት ወር እንደሆነው ለቢቢሲ የተናገረው አማረ ከኢትዮጵያ ከወጣ ሁለት ዓመት እንደሆነው ይገልጻል። በየመን አድርጎ ሳዑዲ አረቢያ ሲገባ ጧይት የሚባል ስፍራ ነው የተያዘው። እርሱ ባለበት እስር ቤት ውስጥ በአንድ ክፍል ከአንድ መቶ በላይ እስረኞች እንዳሉም ይናገራል።

"በጣም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። በየጊዜው ፖሊሶች እየገቡ ይደበድቡናል። ምግብም በአግባቡ አይገባልንም።"

ወደ ሳዑዲ ከጓዶኞቹ ጋር ሰርተን እንለወጣለን በሚል መምጣታቸውን የሚናገረው አበራ ደግሞ እስር ቤት ገብተው መቅረታቸውን እና በጣም ችግር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ወደ ኢትዮጵያ መልሱን ሲል የተማጽኖ ጥሪ ያሰማል።

"የሚጠይቀን፣ የሚጎበኘን የለም፤ ተዘግተን ቀረን" ሲል ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳል።

ከኤምባሲ ወደ አገር ቤት ትሄደላችሁ በሚል ቅጽ መሙላታቸውን የሚናገረው አበራ ከዚያ ወዲህ የጠየቀን የለም በማለት ሁኔታውን ያስታውሳል።

ከአንድ ወር በፊት ገንዘብ እየከፈለ የሚሄድ ካለ በሚል መጠየቃቸውን የሚናገረው አበራ፣ ገንዘብ ስለሌላቸው ግን እስር ቤት ውስጥ መቅረታቸውን ይገልጻል።

ዓለም አቀፎቹ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዋች በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልትና ስቃይ ላይ ባደጓቸው ማጣራቶች የስደተኞቹ ህይወት አደጋ ላይ መሆኑን አመልክተው የነበረ ሲሆን፣ የሞቱ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውንም በእስር ቤቶቹ ካሉ ስደተኞች መስማታቸውን ገልጸው ነበር።

የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶቱ ጨምረውም የሳዑዲ መንግሥት ስደተኞቹ ያሉበት አደገኛ ሁኔታ እንዲያሻሽል እንዲሁም ነጻ እንዲወጡ የጠየቁ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም የስደተኞቹ አያያዝ እንዲስተካከል ግፊት እንዲያደርግና ፈቃደኛ የሆኑትም ወደአገራቸው እንዲመለሱ የሚደረግበትን መንገድ እንዲፈልግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤትም በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን አስከፊ አያያዝና የሰብአዊ መብት ጥሰት በጽኑ የሚያወግዝ የውሳኔ ሐሳብ አስተላልፎ ነበር።