ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ላይ የጉዞ ዕገዳ ጣለች
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሳዑዲ አረቢያ በተወሰኑ አገራት ላይ ጥላው የነበረውን የበረራና የጉዞ ዕገዳ በማስፋት ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 አገራትንና የአውሮፓ ኅብረትን ማካተቱ የአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አሳወቁ።
አዲሱ የሳዑዲ ዕገዳ ከአውሮፓ ኅብረት አገራት በተጨማሪ ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ሱዳንን፣ ኬንያን፣ ጂቡቲን፣ሶማሊያን፣ ስዊትዘርላንድን፣ ህንድን፣ ፓኪስታንን፣ ሲሪላንካንና ፊሊፒንስን የሚያካትት ነው።
በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ በሳውዲ የሚገኙ ስደተኛ ሠራተኞች መካከል አብዛኞቹ እገዳው ከተጣለባቸውና ከተጠቀሱት አገራት የሄዱ እንደሆኑ ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።
የእገዳ ውሳኔው ከፊሊፒንስና ከህንድ የመጡ የጤና ባለሙያዎችን የማይመለከት ሲሆን በተጨማሪም አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ የተደረገባቸው ዜጎችን ለማስወጣት የሚደረጉ በረራዎች፣ የመርከብ ጉዞዎችና የንግድ በረራዎች ዕገዳው አይመለከታቸውም ተብሏል።
ይህ ተጨማሪ ዕገዳ ይፋ እንዲሆን ምክንያት የሆነው ተጨማሪ አገራት በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ማግኘታቸውን ካሳወቁ በኋላ ሲሆን የጉዞ እና የበረራና ዕገዳው የተጣለባቸውን አገራት 45 እንዳደረሰው ሮይተርስ ዘግቧል።
የሳዑዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው በሽታው በተገኘባቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ የሳዑዲ ዜጎች በ72 ሠዓታት ውስጥ ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉም ተገልጿል።
ሳዑዲ አረቢያ ጎረቤቶቿን አረብ አገራትን ጨምሮ ቀደም ሲል በ19 አገራት ላይ የጉዞ ዕገዳን ጥላ የነበረ ሲሆን፤ ወደ አገሪቱ በሚያስገቡ በሮች ላይ የጤና መረጃቸውንና የጉዞ ዝርዝራቸውን ለመግለጽ የማይፈልጉ ሰዎች 133 ሺህ ዶላር እንደሚቀጡም ተገልጿል።
ሳዑዲ በሽታውን ለመከላከል አብዛኛው በበሽታው የተያዙ ሰዎች የተገኙበትና የነዳጅ ዘይት አምራች ከሆነው ቃጢፍ ከተባለው ክልል መግባትም ሆነ መውጣት ከልክላለች።
በተጨማሪም ሳዑዲ ሐይማኖታዊ ጉዞን ያገደች ሲሆን በመላዋ አገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ሲኒማ ቤቶች እንዲዘጉ አድርጋለች። እንዲሁም የተለያዩ ጉባኤዎችና ስፖርታዊ ውድድሮች የተሰረዙ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የቡድን 20 የሚኒስትሮች ስብሰባም ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።