የሞት ቅጣት የምትጠባበቀው የብቸኛዋ አሜሪካዊት ፍርድ እንዲጸና ታዘዘ

በፌዴራል ደረጃ የሞት ቅጣት በምትጠባበቀው ብቸኛዋ ሴት ላይ የቀረበውን የይግባኝ ጥያቄ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ።

ይህች ሊሳ ሞንትጎመሪ የተባለችው ሴት ሞት የተፈረደባት ከ15 ዓመት በፊት ሚዙሪ ውስጥ አንዲት ነፍሰ ጡር ሴትን አንቃ በመግደልና ሆዷን በመቅደድ አሰቃቂ ድርጊት በመፈጸሟ ነው።

የሞት ፍርዱ ከጸና በ70 ዓመታት ውስጥ የተገደለች የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ፌደራል መንግሥት እስረኛ ትሆናለች።

የሊሳ የሞት ቅጣት የሚፈጸምበት ቀን ከአንድ ወር በፊት እንዲሆን ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ጠበቆቿ ኮቪድ -19 ስለያዛቸው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

ይህን ተከትሎም የፍትህ መምሪያው ፍርዱ ጥር 12 እንዲፈጸም ወስኗል። ነገር ግን የሊሳ ጠበቆች ቀኑ ሊወሰን እንደማይችል ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤት የጠበቆቿን ሐሳብ ተቀብሎ የእስር ቤቱ ዳይሬክተር የሞት ፍርዱ የሚከናወንበትን ቀን መቁረጡን ውድቅ አድርጎት ነበር።

ሆኖም ግን አርብ ዕለት የዳኞች ቡድን ዳይሬክተሩ የሞት ፍርዱ እንዲፈፀም የወሰነውን በሕጉ መሠረት ጠቅሶ ይተግበር የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

የሊሳ ጠበቆች ዳኞቹ የሰጡትን ውሳኔ እንደገና እንዲያጤኑት አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

በሞት ፍርድ መረጃ ማዕከል መሠረት፤ ሚዙሪ ግዛት ውስጥ በ1953 (እአአ) የሞት ፍርድ የተፈጸመባት ቦኒ ሄዲ ለመጨረሻ ጊዜ በአሜሪካ መንግሥት ውሳኔው የተፈጸመባት ሴት ናት።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ቅጣቱ እንዲጀመር ትዕዛዝ ከመሰጠታቸው በፊት የፌዴራል የሞት ፍርድ ለ17 ዓመታት ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቶ ነበር።

የሊሳ የሞት ፍርድ የሚከናወነው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ከመረከባቸው ጥቂት ቀናት በፊት ይሆናል።

የደላዌር ሴናተር ሆነው ለአስርት ዓመታት የሞት ቅጣትን ሲደግፉ የነበሩት ባይደን ስልጣናቸውን ከያዙ በኋላ ግን የሞት ፍርድን ለማስቆም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ሊሳ ሞንትጎመሪ ማን ናት?

በታኅሣስ 2004 (እአአ) ሊሳ ከካንሰስ ወደ ሚዙሪ ያቀናቸው ቦቢ ጆ ስቲንኔት ቤት ያሳደገውን ቡችላ ለመግዛት እንደነበር የፍትህ መምሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቋል።

"ሊሳ ወደ መኖሪያው ከገባች በኋላ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር የነበረችው ስቲኔት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ራሷን እንድትስት አድርጋለች" ይላል መግለጫው።

"ቢላ በመጠቀም የስቲኔትን ሆድ ስትቀድ ግለሰቧ በዚህ ወቅት ነበር። ሲታገሉ ሊሳ ባደረሰችባት ጥቃት ስቲንኔት ለሞት በቅታለች። ከዚያም ሊሳ ህፃኑን ከሆዷ በመውሰድ አገተቻች" ብሏል።

በ2007 (እአአ) በፌደራል እገታ እና ግድያ ጥፋተኛ ሆና ስለተገኘች የሞት ፍርድ ተላልፎባታል።

የሊሳ ጠበቆች ግን በልጅነቷ በደረሰባት ድብደባ የአንጎል ጉዳት የደረሰባት ሲሆን የአዕምሮ ህምተኛ ስለሆነችም የሞት ቅጣት ሊተላለፍባት አይገባም ብለው ተከራክረዋል።

የፌዴራል እና የግዛቶች የሞት ፍርዶች ልዩነት ምንድነው?

በአሜሪካ የፍትህ ሥርዓት መሠረት ወንጀሎች በአገር አቀፍ ደረጃ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወይም በግዛት ደረጃ ደግሞ በግዛቶቹ ፍርድ ቤቶች ሊታዩ ይችላሉ።

እንደ ሐሰተኛ ገንዘብ ማዘዋወር ወይም የመልዕክት ስርቆት ያሉ ወንጀሎች በፌደራል ደረጃ ይታያሉ።

የሞት ፍርድ መረጃ ማዕከል በተሰበሰበው መረጃ መሠረት በ1988 እና 2018 (እአአ) መካከል በፌዴራል ደረጃ 78 ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ሲሆን የተገደሉት ግን ሦስት ሰዎች ብቻ ናቸው።