ኮሮናቫይረስ ፡ በአውሮፓ ሕብረት አገራት ውስጥ በሙሉ ዛሬ ክትባት መሰጠት ይጀምራል

የአውሮፓ ሕብረት በአባል አገራቱ ውስጥ 'አንድነትን ያንጸባርቃል' ያለውን የተቀናጀ የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ ዛሬ እንደሚጀመር አስታወቀ።

የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቫን ደር ሌይን እንዳስታውቁት የፋይዘር-ባዮንቴክ ክትባት ለ27ቱም የሕብረቱ አባል አገራት በሙሉ ቀርቧል።

አንዳንዳንድ የአውሮፓ አገራት ክትባቱ መሰጠት ይጀመራል የተባለበትን እሁድን ሳይጠብቁ ቀደም ብለው ቅዳሜ ዕለት ክትባት መስጠት መጀመራቸው ተነግሯል።

እስካሁን በወጣው መረጃ መሰረት በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ከ335 ሺህ በላይ ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል።

በተጨማሪም በአህጉሪቱ ውስጥ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ በሁሉም የሕብረቱ አገራት ውስጥ በሚባል ደረጃ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ እርምጃዎች አሁን ድረስ ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ።

ይህ የክትባት ዘመቻ በአውሮፓ ሕብረት አገራት ውስጥ የሚጀመረው ቀደም ካለው የኮሮናቫይረስ በበለጠ የመስፋፋት አቅም አለው ተባለ አዲስ የቫይረስ ዝርያ በበርካታ የሕብረቱ አገራት ውስጥ እንዲሁም በካናዳና በጃፓን ውስጥ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው።

በዚህም ሳቢያ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት አዲስ የጉዞ እገዳዎችን እየጣሉ ነው።

የክትባት ዘመቻ በአውሮፓ

ይህ ግዙፍ የኮሮናቫይረስ ክትባት ዘመቻ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ የሚገኙ 446 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ ያለመ ነው።

የክትባት ዘመቻው የሚካሄደው በጀርመንና በአሜሪካ ተቋማት በጥምረት የተዘጋጀውን ፋይዘር-ባዮንቴክ የኮሮናቫይረስ ክትባት ከአውሮፓ የመድኃኒቶች ኤጀንሲና ከአውሮፓ ኮሚሽን ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎ ነው።

የአውሮፓ ሕብረትም ክትባቱን ለዜጎቹ ለማቅረብ ከሁለት ቢሊዮን በላይ የክትባቱን ብልቃጦች ከተለያዩ የመድኃኒት አምራች ተቋማት ለማግኘት ውል ተፈራርሟል።

የክትባት ተስፋ

"ዛሬ አስቸጋሪ ከነበረው ዓመት ውስጥ ወሳኙን ገጽ መግለጥ እንጀምራለን። የኮቪድ-19 ክትባት ለአውሮፓ ሕብረት አገራት ቀርቧል። ክትባቱን መስጠትም ከዕሁድ ጀምሮ በመላዋ አውሮፓ መስጠት ይጀመራል" ሲሉ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቫን ደር ሌይን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ጨምረውም ይህም በሕብረቱ ውስጥ ባለው አንድነት ውስጥ የተለየ ጊዜ እንደሚሆን ገልፈው፤ ክትባቱ ከወረርሽኙ ለመውጣት ዘላቂው መፍትሄ እንደሆነ አመልክተዋል።

የጀርመን ጤና ሚኒስትር የንስ ስፋን ቅዳሜ ዕለት እንዳሉት "ይህ የመልካም ገና መልዕክት ነው። በአሁኑ ጊዜ የጭነት ተሽከርካሪዎች በሁሉም ስፍራ ክትባቱን እያደረሱ ነው። ይህም እሁድ ዕለት ይቀጥላል" ብለዋል።

የጣሊያኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዊጂ ዲ ማዮም የአገራቸው ዜጎች እንዲከተቡ ጥሪ አቅርበዋል። "ነጻነታችንን በማግኘት እንደገና ወደ ቀድሞው ሕይወታችን ለመመለስ ያስችለናል" ብለዋል።

በሰሜን ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ የሚገኙ የጤና ሠራተኞች ክትባቱን መስጠት ለመጀመር እስከ እሁድ ድረስ መጠበቅ ባለመፈለጋቸው ከቅዳሜ ጀምረው በእንክብካቤ መስጫ ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙ አዛውንቶች ክትባቱን መስጠት ጀመርዋል።

ሃንጋሪ ውስጥ ደግሞ ለአንድ ዶክተር ክትባቱን ቅዳሜ ዕለት በመስጠት ተጀምሯል። የስሎቫክ ባለስልጣናትም ክትባቱን መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።