ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በአፍሪካ የኮቪድ-19 ስርጭት ምን ደረጃ ላይ ነው?
በአፍሪካ በሕዝብ ብዛታቸው ቀዳሚ ከሆኑ አገራት ውስጥ የኮቪድ-19 ስርጭት ዳግም ከፍ እያለ መምጣቱን ያስተዋሉ የሕክምና ባለሙያዎች አህጉሪቱ ዳግም የቫይረሱን ወረርሽኝ ልታስተናግድ ይሆን የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።
የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር በበኩሉ በአህጉሪቱ "የሁለተኛው ዙር ስርጭት" እየመጣ መሆኑን መናገር ጀምሯል።
ቁጥሮችስ የሚያሳዩን ምን ይሆን?
ከመስከረም ወር መጨረሻ እና ጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከፍ ማለቱን ከየአገራቱ የሚወጡ የቁጥር መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ መረጃዎች ደግሞ ከአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር እንዲሁም ከዓለም ጤና ድርጅት ከሚወጡት መረጃዎች ጋር ስሙም ናቸው።
ባለፈው ወር በየአገራቱ በቫይረሱ የተያዙ አዲስ ሰዎችን ቁጥር የተመለከትን እንደሆነ በእያንዳንዱ ሳምንት በአማካይ 3.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ነገር ግን ከአገር አገር ከፍተኛ የሆነ ልዩነት መኖሩንም ማስተዋል ተገቢ ነው። አንዳንድ አገራት መጠነኛ ጭማሪ ሌሎች ደግሞ በተከታታይ ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳዩ አንዳንድ አገራት ግን አሁንም አነስተኛ የቫይረሱ ስርጭት መጠን ይታይባቸዋል።
ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ ከ60 በመቶ በላይ በየዕለቱ አዲስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ትይዛለች።
ለምን በደቡብ አፍሪካ ጭማሪ ታየ?
ለተከታታይ አራት ወራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ከታየ በኋላ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ስለ ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ ማውራት ጀምሯል።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው ከሆነ፣ አሁን በቫይረሱ በብዛት እየተያዙ ያሉት ሰዎች እድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ያሉ ታዳጊዎች ናቸው።
ይህ ሊሆን የቻለውም በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የተከበሩ ትልልቅ በዓላት መኖራቸው መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ በዓላት የፈተና እና የትምህርት ዘመን መጠናቀቅን አስመልክቶ የተዘጋጁ ነበሩ።
በደቡብ አፍሪካ የተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሳሊም አብዶል ካሪም ለቢቢሲ "አንዳንድ መጠጥ የሚሸጡ እና ሰፋፊ ስፍራዎች ያሏቸው ተቋማት በምሽት በሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞቻቸውን በአንድነት ያስተናግዳሉ። ይህም በግልጽ የተቀመጠውን ደንብ የጣሰ ነው" ብለዋል።
እንደ የአፍሪካ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ከሆነ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ብቻ በደቡብ አፍሪካ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ ሞት በ19 በመቶ ጨምሯል።
መንግሥት የቫይረሱን መስፋፋት ዳግም ለመከላከል በማሰብ ተጨማሪ ክልከላዎችን ያስቀመጠ ሲሆን በዚህም የተነሳ መጠጥ የሚሸጥበት ሰዓት ላይ ገደብ እንዲሁም የተወሰኑ የባህር ዳርቻዎች እንዲዘጉ አድርጓል።
በሌላ የአፍሪካ አገራትስ ምን እየሆነ ነው?
እስከ ሕዳር ወር መጀመሪያ ድረስ ባሉት ሳምንታት በሰሜን አፍሪካ አገራትም የቫይረሱ የስርጭት መጠን ጭማሪ አሳይቷል።
ባለፉት ሳምንታት ሞሮኮ በአህጉሪቱ ካሉ አገራት ሁሉ በቫይረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎችን በመመዝገብ ቀዳሚ የነበረች ሲሆን በዚህ ሳምንት ግን የስርጭቱ መጠን እየቀነሰ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
በናይጄሪያ፣ ግብጽ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኡጋንዳም ባለፉት አራት ሳምንታት ጭማሪ አሳይቷል።
በኬንያና በኢትዮጵያም ቢሆን፣ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት መቀነስ ቢያሳይም፣ የቫይረሱ ስርጭት መጠን ጭማሪ አሳይቶ ነበር።
የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ባልደረባ የሆኑት ጆን ንኬንጋሶንግ " በእርግጠኝነት ሁለተኛው ዙር ወረርሽኝ ደጃፋችን ላይ ነው" ብለዋል። እንደ እርሳቸው ከሆነ በጥር እና የካቲት ወራት ቫይረሱ ዳግም ጭማሪ ኣሳይቶ አህጉሪቱ በሐምሌ ወር የነበረችበት ደረጃ ላይ ትደርሳለች።
ከሌላ የዓለም ክፍል ጋር ሲነጻጸር በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተመዘገበው የሞት መጠን አነስተኛ ነው። ለዚህም ባለሙያዎቹ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች ሲያስቀምጡ አህጉሪቱ በአንጻራዊነት በወጣት ዜጎች የተሞላች መሆኗን (ዕድሜያቸው ከ25 በታች የሆነ ዜጎች ከ60 በመቶ ናቸው)፣ ከአገር አገር የሚያደርጉት ጉዞ የቀነሰ መሆኑን እና በብዛት ከቤት ውጭ የሚደረግ ቆይታ ከፍተኛ መሆን፣ ከሌሎች የኮሮናቫይረስ አይነቶች የተሸጋገረ የበሽታ መከላከልን ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን በአፍሪካ የሞት ምዝገባ አነስተኛ መሆን ይህንን መረጃ ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የተሰራ ጥናት እንዳመለከተው በርካታ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሲሆን ይህም በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ከተነገረው በላይ ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።
በአፍሪካ ምን ያህል የኮሮናቫይረስ ምርመራ እየተደረገ ነው?
የዓለም ጤና ድርጅት አፍሪካ አሁንም በእጅጉ አነስተኛ ቁጥር ያለው ሰውን እየመረመረች መሆኑን ይናገራል። በአህጉሪቱ ካሉት አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ካሜሮን፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ጋና የአህጉሪቱን አጠቃላይ ምርመራ 70 በመቶ ያህሉን መርምረዋል።
በአገራት መካከልም የመመርመር አቅም ልዩነት ያለ ሲሆን፣ አንዳንድ አገራትም የሚመረምሩትን ሰው ቁጥር ሲቀንሱ፣ የተወሰኑት ባሉበት ቀሪዎቹ ደግሞ ጭማሪ አሳይተዋል።
ከአፍሪካ ካላቸው ሕዝብ ብዛት አንጻር ከፍተኛ ምርመራ ያደረገችው ደቡብ አፍሪካ ስትሆን፣ በተቃራኒው ናይጄሪያ አነስተኛ ምርመራ ማድረጓን መረጃዎች ያሳያሉ።
በተጨማሪም አንዳንድ አገራት ስላካሄዱት ምርመራም ሆነ፣ በአገራቸው ስላለው የስርጭት መጠን ለመናገር የሚያስችል በቂ የተደራጀ መረጃ የላቸውም።