ኮሮናቫይረስ ፡ በአራት ቀናት ውስጥ 10 ኬንያዉያን ዶክተሮች በኮቪድ-19 ሞቱ

ባለፉት አራት ቀናት 10 ኬንያዊያን ዶክተሮች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ሐኪሞች ማኅበር የሥራ ማቆም አድማ እንደሚጠራ አሳወቀ።

በቀናት ውስጥ በርካታ አባላቱን በወረርሽኙ ያጣው ማኅበሩ የሥራ ማቆም አድማውን ከማድረጉ ከ21 ቀናት በፊት መስጠት የሚገባውን ማስጠንቀቂያ ይፋ አድርጓል።

ዶክተሮቹ የኬንያን መንግሥት ለኮቪድ-19 እንድንጋለጥ አድርጎናል በሚል ከሰዋል። በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ህሙማን ጋር ንክኪ ይኑራቸው አይኑራቸው ግልጽ ባይሆንም ባለፈው አርብ ብቻ አራት ዶክተሮች ሞተዋል።

የሐኪሞቹ ማኅበር ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ምዋቾንዳ ቺባንዚ እንዳሉት፤ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ ካላገኙ የጠሩትን የሥራ ማቆም አድማ እንደማይሰርዙት ገልጸዋል።

ማኅበሩ መንግሥት በግል ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሰሩትን ጨምሮ በሁሉም የጤና ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ደረጃቸውን የጠበቁና በቂ የመከላከያ አልባሳት እንዲያቀርብ ጠይቋል።

በተጨማሪም ለሁሉም የጤና ባለሙያዎች መንግሥት አጠቃላይ የህክምና ዋስትና ሽፋን እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበዋል።

ከአድማው በፊት ባሉት ሦሰት ሳምንታት ውስጥ ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን ገልጾ "ይህ ካልሆነ ግን አባሎቻችንን አስተባብረን አገር አቀፍ የሥራ ማቆም አድማ እናካሂዳለን" ብለዋል ምዋቾንዳ።

የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ሙታሂ ካግዌ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የጤና ባለሙያዎች መካከል እየተስፋፋ ስላለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ስብሰባ እንደሚካሄድ አሳውቀዋል።

እስካሁን ድረስ ኬንያ በግዛቷ ውስጥ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው መገኘታቸውን ያረጋገጠች ሲሆን፤ በወረርሽኙ ምክንያትም 1ሺህ 269 ዜጎቿ ሞተውባታል።