የእድሜ ባለጸጎችና ህሙማን በከፍተኛ ሁኔታ ለኮሮና ተጋላጭ ናቸው ተባለ

የቻይና የጤና ዘርፍ ኃላፊዎች ስለ ኮቪድ-19 (በኮሮናቫይረስ የሚከሰተው በሽታ) ዝርዝር መረጃ የያዘ ጥናት ይፋ አደረጉ።

የቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲሲዲሲ) ባወጣው ጥናት መሰረት፤ የእድሜ ባለጸጎችና ህሙማን ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናቸው። የህክምና ባለሙያዎችም በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው ሰፊ እንደሆነ ተመልክቷል።

በኮቪድ-19 ቫይረስ በዋነኛነት በተስፋፋበት ሁቤይ ግዛት የሞት መጠን 2.9 በመቶ ሲሆን፤ በተቀረው ቻይና ደግሞ 0.4 በመቶ መሆኑ ተገልጿል።

ይፋ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፤ እስካሁን በበሽታው ሳቢያ 1,868 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ 72,436 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል። ባለፉት 93 ቀናት 98 ሰዎች ሲሞቱ 1,886 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ከእነዚህ 1,807ቱ በሁቤይ ግዛት የተመዘገቡ ናቸው።

የቻይና ኃላፊዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ ከ12,000 በላይ ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

ጥናቱ ቫይረሱ መሰራጨት ከጀመረ ወዲህ በበሽታው የተያዙ እንዲሁም ተይዘዋል የተባሉትን በአጠቃላይ ከግምት ያስገባ ነው። ከህሙማኑ 80.9 በመቶው መጠነኛ ስጋት ውስጥ፣ 13.8 በመቶው አስከፊና 4.7 በመቶው ደግሞ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በከፍተኛ ደረጃ ለበሽታው የተጋለጡት እድሜያቸው 80 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ናቸው። እስካሁን ከዘጠኝ ዓመት በታች የሆነ ልጅ ሕይወት አለማለፉና፤ እስከ 39 ዓመት የሆናቸው ሰዎች የመሞት እድላቸው 0.2 በመቶ መሆኑንም ተመልክቷል።

ወንዶች በበሽታው የመሞት እድላቸው 2.8 በመቶ የሴቶች ደግሞ 1.7 በመቶ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል። ከደም ዝውውር ጋር የተያያዘ ህመም ያለባቸው ሰዎች ለበሽታው የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ሲሆን፤ ስኳር እና ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተገናኘ በሽታ ያለባቸው ሰዎችም በቫይረሱ ሊያዙ እንደሚችሉ በጥናቱ ተጠቁሟል።

እስካሁን 3,019 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ እንደተያዙና ከእነዚህ አምስቱ መሞታቸውም ተገልጿል።

ይፋ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፤ ቫይረሱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከጥር 23 እስከ 26 ስርጭቱ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን፤ ወደ የካቲት 11 አካባቢ ቀንሷል።

በሽታው በስፋት የተሰራጨባቸውን ከተሞች መለየት እንዲሁም ሰዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል መውሰድ የሚገባቸውን ጥንቃቄ (እጅ መታጠብ፣ አፍና አፍንጫ የሚሸፍን ጭንብል ማጥለቅ) ማሳወቅ፤ ስርጭቱ እንዲቀንስ እየረዳ እንደሚገኝ ጥናቱ ያሳያል።