እስራኤል የበርካታ ፍልስጥኤማውያንን ቤቶች ማፍረሷን ተመድ ኮነነ

የፎቶው ባለመብት, OCHA
እስራኤል ለአስርት አመታት በወረራ የያዘችው ዌስት ባንክ ላይ የፍልስጥኤማውያንን ቤቶች ማፍረሷን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮንኗል።
በዮርዳኖስ ሸለቆ የሰፈሩ 73 ቤተሰቦች ቤት አልባ ሆነዋል፤ ከነዚህም ውስጥ 41 ህፃናት መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል በበኩሉ ቤቶቹ በህገወጥ መንገድ የተሰሩ ናቸው ብሏል።
ይህንን የእስራኤል ድርጊት በፅኑ የኮነነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአለምአቀፍ ህጎችንም የጣሰ ነው ብሎታል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አስተባባሪ ቢሮ እንደገለፀው 76 መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ፣ የእንስሳት መጠለያዎችና ሌሎች ንብረቶችም በእስራኤል ቡልዶዘሮች ማክሰኞ፣ ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም መፈራረሳቸውን አስታውቋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት በበኩላቸው በዚህ ቁጥር የማይስማሙ ሲሆን ሰባት ድንኳኖችና ስምንት የእንስሳት መጠለያዎች ብቻ ናቸው የፈረሱት ይላሉ።
ተቀማጭነቱን በእስራኤል ያደረገው የሰብዓዊ መብት ድርጅት ቢቲ ሴሌም ቤቶቹ ሲፈራርሱ የሚያሳይ ቪዲዮም አውጥቷል።
"ይህ ከፍተኛ ኢ-ፍትሃዊነት ነው" በማለትም ሃርብ አቡ አል ካባሽ ለእስራኤሉ ጋዜጣ ሃሬትዝ ተናግሯል።
"እንደሚመጡ ስላማናውቅ ቀድመን ለመዘጋጀት እድሉን አላገኘነም። በአሁኑ ሰዓት ቤት አልባ ሆነናል እየዘነበብን ነው" ብሏል።
የሰላማዊ ዜጎችን ጉዳይ የሚመለከተው የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ክፍል ባወጣው መግለጫ የፈረሱት ቤቶች ወታደራዊ ማሰልጠኛ አካባቢ "በህገወጥ መንገድ" የተሰሩ ስለሆኑ ነው የሚል ምክንያት ሰጥቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዚህ አይስማማም የእስራኤል ድርጊት አራተኛውን የጄኔቫ ድንጋጌ የጣሰ ነው ይላል።
በአለም አቀፉ ህግ መሰረት አገራት በወረሩዋቸው (በተቆጣጠሩዋቸው) ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ አለባቸው።
በጎሮጎሳውያኑ 1967 የተደረገውን የመካከለኛ ምስራቅ ጦርነት ተከትሎ ነው እስራኤል ዌስት ባንክ ግዛትን በመውረር በቁጥጥሯ ስር ያዋለችው።
በተለያየ ጊዜ የተፈፀሙ ስምምነቶችን ተከትሎ ፍልስጥኤማውያን የተወሰነውን የዌስት ባንክ ግዛት በተወሰነ መልኩ በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ቢያስችላቸውም መላውን ግዛት የምትቆጣጠረው እስራኤል ናት።
ቤቶቹ የፈራረሱባቸው ክርበት ሁምሳ ከፍልስጥኤማውያን ቁጥጥር ውጭ ነው።
በእስራኤል አገዛዝ ስር ያሉ የፍልስጥኤም ነዋሪዎች ቤቶችም ሆነ ህንፃ ለመገንባት ፍቃድ አይሰጠንም በማለት ይወቅሳሉ።












