የአሜሪካና የእንግሊዝ ኤምባሲዎች ውጥረቱ እንዲረግብ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, U.S. Embassy Addis twitter page
የትግራይና የፌደራል መንግሥት የገቡበትን ውጥረት ሊያረግቡ እንደሚገባ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት በኤምባሲዎቻቸው በኩል ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በዛሬው ዕለት ጥቅምት 25/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ሁለቱም ወገኖች የገቡበትን ውጥረት እንዲያረግቡ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ለሰላማዊ ሰዎች ደህንነትና ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባልም ብሏል።
"ሁሉም ወገኖች ለሰላማዊ ሰዎች ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጡ እናበረታታለን" ብሏል መግለጫው።
የእንግሊዝ ኤምባሲም በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ ክልል ያለው ውጥረት በአፋጣኝ እንዲረግብ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ስም የጠየቀ ሲሆን የሰላማዊ ዜጎቻቸውን ደህንነት ሁለቱም ወገኖች እንዲያስጠብቁ ጠይቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ህወሃት በትግራይ የሚገኘው የመከላካያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ "ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል" ብለዋል።
የትግራይ ክልል መንግሥት በክልሉ የሚገኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላትና አዛዦች ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን ለመሰለፍ ወስኗል በማለት መግለጫ አውጥቷል።
መግለጫው ከዛሬዋ እለት ጀምሮ ጥቅትም 25/ 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ውስጥና ድንበር አካባቢ ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተከለከለ እንደሆነ አትቷል።












