አርሜኒያና አዘርባጃን የጦር ማቆም ስምምነት አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አርሜኒያና አዘርባጃን ከባድ ጦርነት ላይ ነበሩ ባለፉት ሳምንታት፡፡
ሩሲያ ሁለቱን አገሮች በማደራደር ተሳክቶላታል፡፡ ቢያንስ ጊዜያዊ የጦር አውርድ ስምምነት ለማድረግ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ናቸው ይህን መልካም ዜና ይፋ ያደረጉት፡፡
የአዘርባጃንና የአርሜኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሞስኮ 10 ሰዓታት የፈጀ ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው ይህ ውጤት የተገኘው፡፡
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ሁለቱ አገራት ባደረጉት ጦርነት በትንሹ 300 ዜጎቻቸውን አጥተዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡
አሁን ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም ስምምነቱ ዛሬ ቅዳሜ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜም የጦር ምርኮኞቻቸውን ይለዋወጣሉ፡፡
የሟች ወታደሮችን ሬሳ በወጉ የመለየትና ግብአተ መሬቱን የመፈጸም ሂደትም ይኖራል ተብሏል፡፡
ሁለቱን ጎረቤት አገራት ለጦርነት የዳረጋቸው ናጎርኖ ካራባህን የምትባል ግዛት የይገባናል ጥያቄ ነው፡፡
ናጎርኖ ካራባህን በአዘርባጃን ግዛት ውስጥ ያለች ቦታ ብትሆንም የሚኖሩባት የአርመን ዝርያ ያላቸው ዜጎች ናቸው፡፡
የምትተዳደረውም በአርሜኒያ ብሔር ተወላጆች ነው፡፡ በአርሜኒያ ድጋፍ ራሳቸውን እንደ ነጻ ግዛት ነው የሚቆጥሩት፡፡
ሆኖም ናጎርኖ ካራባህን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአዘርባጃን ግዛት እንደሆነ ነው የሚያውቀው፡፡ ግዛቱ የሚገኘውም በአዘርባጃን አገር ውስጥ ነው፡፡
አርሜኒያና አዘርባጃን የቀድሞው የሶቭየት ሪፐብሊክ አካል የነበሩ ናቸው፡፡
ሩሲያ በአርሜኒያ የጦር ቀጠና ያላት ሲሆን ከአዘርባጃንም ጋር ጥሩ ወዳጅ ናት፡፡ ቱርክ በበኩሏ ጭልጥ ያለ ድጋፏን ለአዘርባጃን ሰጥታለች፡፡

የፎቶው ባለመብት, EPA
አዘርባጃንና ቱርክ የዝርያና የሃይማኖት ቅርርብ እንዳላቸው ይነገራል፡፡
ይህን ተከትሎ ጦርነቱ ከሁለቱ አገራት አልፎ ሩሲያን፣ ኢራንን እንዲሁም ቱርክን ሊያካትት ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮ ነበር፡፡
ይህ የጥቂት ሳምንታት ጦርነት ናጎርኖ ካራባህ ነዋሪ የሆነውን ግማሽ ሕዝብ ያፈናቀለ ሆኗል፡፡ ከ150ሺህ የግዛቲቱ ነዋሪዎች 70ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡
አርሜኒያና አዘርባጃን ይህን ጦርነት ሲያደርጉ የመጀመርያቸው አይደለም፡፡
እንደ አውሮጳዊያኑ በ1988 ጀምሮ ለስድስት ዓመታት የዘለቀ ጦርነት አድርገው ያውቃሉ፡፡
ያን ጦርነትም እንዲሁ በተኩስ አቁም ስምምነት ነበር የደመደሙት እንጂ ወደ ጦርነት ላስገባቸው ግዛት ባለቤትነት ቁርጥ ስምምነት አላደረጉም ነበር፡፡
አሁን ከዓመታት በኋላ ወደ ጦርነት የተመለሱትም ለዚሁ ነው፡፡
አዘርባጃን 10 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት የነዳጅ ዘይት እያበለጸጋት ያለች አገር ናት፡፡ የባሕር በር የሌላት አርሜኒያ የሕዝብ ቁጥሯ 3 ሚሊዮን አካባቢ ብቻ ነው፡፡
















