ናጎርኖ-ካራባህ ግጭት፡ የአዘርባጃን ሁለተኛ ከተማ በአርሜኒያ ኃይሎች መመታቷ ተገለፀ

የፈራረሱ ህንፃዎች

የፎቶው ባለመብት, Azerbaijan's defence ministry

በናጎርኖ-ካራባህ ግዛት ይገባኛል በቀድሞ ሶቪየት ሪፐብሊክ አካል በነበሩት አዘርባጃንና አርሜኒያ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ቀጥሎ የአዘርባጃን ሁለተኛ ከተማ የሆነችው ጋንጃ በአርሜኒያ ኃይሎች መመታቷ ተገለፀ።

የአዘርባጃን ኃይሎች የግዛቷን ዋና ከተማ ስቴፓናከርት ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ የራስ ገዝ አስተዳደሯ ባለሥልጣናት የአዘርባጃን የጋንጃን የጦር አየር ማሪፊያ መምታታቸውን አስታውቀዋል።

ከሳምንት በፊት ግጭቱ ከቀሰቀሰ አንስቶ እስካሁን ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።

በሁለቱም ወገን የደረሰው ጉዳት በገለልተኛ ወገን ስላልተጣራ የሟቾቹ ቁጥር ከተገለፀው በላይ ሊሆን እንደሚችል ስጋት አለ።

አርሜኒያና አዘርባጃን ከ2016 ወዲህ ለተቀሰቀሰው ከባድ ግጭት እርስ በርሳቸው ይወቃቀሳሉ።

የአዘርባጃን ጦር ከእሁድ ዕለት ጀምሮ ሰባት መንደሮችን እንደገና መቆጣጠሩን አስታውቋል። ናጎርኖ-ካራባህ ደግሞ ወታደሮቿ የፊት አሰላለፋቸውን ማሻሻላቸውን ተናግራለች።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አርሜኒያ በፈረንሳይ፣ ሩሲያና አሜሪካ አሸማጋይነት ተኩስ አቁም ስምምነት ምክክር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆን አስታውቃ ነበር።

በቱርክ የምትደገፈው አዘርባጃን ግን የአርሜኒያ ወታደሮች ከናጎርኖ -ካራባህና ሌሎች አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ ጠይቃለች።

ሁለቱ የቀድሞ የሶቭየት ሪፐብሊክ አገራት በግዛቷ ላይ ከጎርጎሮሳዊያኑ 1988-94 ድረስ ጦርነት አካሂደዋል።

በኋላ ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ያደረጉ ቢሆንም ስምምነት ላይ ደርሰው አያውቁም።

ናጎርኖ-ካራባህ ግዛት በይፋ የሚታወቀው የአዘርባጃን አካል እንደሆነ ቢሆንም፤ የሚተዳደረው ግን በአርሜኒያዊያን ነው።

ስለ ናጎርኖ- ካራባክህ

  • ተራራማ አካባቢ ሲሆን 4 ሺህ 400 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አለው
  • ክርስቲያን አርሜኒያዊያንና ሙስሊም ቱርካዊያን ይኖሩበታል።
  • በቀድሞ የሶቭየት ሕብረት ጊዜ በአዘርባጃን ሪፐብሊክ ሥር ራሷን የቻለች ክልል ነበረች።
  • የአዘርባጃን ግዛት እንደሆነችም ዓለም አቀፍ እውቅና አላት፤ ነገር ግን አብዛኞቹ ሕዝቦቿ አርሜኒያዊያን ናቸው።
  • ከጎርጎሮሳዊያኑ 1988-1994 ድረስ በተካሄደው ጦርነት አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን 30 ሺህ የሚጠጉ ደግሞ ተገድለዋል።
  • ተገንጣይ ኃይሎች ተጨማሪ የአዘርባጃንን ግዛት ይዘዋል።
  • ቱርክ አዘርባጃንን በግልፅ ትደግፋለች
  • ሩሲያ ደግሞ በአርሜኒያ ወታደራዊ ካምፕ አላት