በሕንድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያለ እድሜ ጋብቻን ማባባሱ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ራኒ 13 ዓመቷ ነው። የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ቤተሰቦቿ ሊድሯት ሲሉ ታግላ አስቁማቸዋለች።
ሕንድ ውስጥ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ሲጣል ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። የቲቢ ታማሚው የራኒ አባት በዚህ ወቅት ነበር ልጃቸውን ለመዳር ያሰቡት። ራኒ ግን ተቃወመቻቸው።
“ሴቶችን ለመዳር ምን እንደሚያጣድፋቸው አላውቅም። መማር፣ ሥራ መያዝና ራሳችንን መቻል እንዳለብን አያስቡም።”
በሕንድ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች መዳር ወንጀል ነው። ነገር ግን በርካታ ያለ እድሜ ጋብቻ ይፈጸማል። ቁጥሩ ከዓለም አንድ ሦስተኛውም ነው።
ዩኒሴፍ እንደሚለው፤ በየዓመቱ ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች ይዳራሉ።
ዘንድሮ ደግሞ ነገሮች ተባብሰዋል። ‘ቻይልድላይን’ የተባለው ድጋፍ ሰጪ እንደገለጸው፤ ከሰኔ እስከ ሐምሌ ልንዳር ነው ብለው ወደ ድርጅቱ የደወሉ ታዳጊዎች ቁጥር 17 በመቶ ጨምሯል።
በእንቅስቃሴ ገደቡ ሳቢያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራቸውን አጥተዋል። ይህም በኢ-መደበኛ ሥራ የተሰማሩትን ይጨምራል።
መንግሥት እንደሚለው ከ10 ሚሊዮን በላይ ስደተኛ ሠራተኞች ወደየቀያቸው ተመልሰዋል። በገጠር የሚኖሩ ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን መዳር ብቸኛ አማራጭ እንደሆነም ያስባሉ።
አገሪቱ ሰኔ ላይ እንቅስቃሴ ብትጀምርም አሁንም ብዙ ሥራዎችና ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ነው። ምጣኔ ሀብትቱም እየላሸቀ ይገኛል።
ሁኔታው ብዙ ታዳጊዎችን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል። ለታዳጊዎች ከለላ ይሰጡ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ቤተሰቦቻቸው ያለ እድሜያቸው ሊድሯቸው ያሉ ሴቶች ቀድሞ ከለላ የሚያገኙት ከመምህራኖቻቸው ነበር።
በአክሽን ኤድ የሚሠሩት ስሚታ ካንጆው “በጣም ድሀ በሆኑ ማኅበረሰቦች ዘንድ ሴቶች እንዲማሩ አይበረታቱም። ሴቶች ትምህርት ካቋረጡ በኋላ በድጋሚ እንዲጀምሩ ቤተሶቻቸውን ለማሳመን ከባድ ነው” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የታዳጊዎች ትግል
የራኒ ጓደኛ የተዳረችው በዚህ ዓመት ነበር። እሷንም ቤተሰቦቿ ሊድሯት እንደሆነ ስታውቅ ወደ የልጆች አደጋ ጊዜ ክፍል ደወለች።
አንድ የተራድኦ ድርጅት ከፖሊሶች ጋር ተጋግዞ ጋብቻውን አስቁሟል።
የራኒ አባት ብዙም ሳይቆይ አረፉ። ትምህርት ቤት ሲከፈት ትምህርት መጀመር እንዳለባትም ትናገራለች።
“አሁን ቤተሰባችንን ማስተዳደር የኔ ኃላፊነት ነው” ትላለች።
ታዳጊ ወንዶች ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ፋብሪካ ውስጥ እንዲሠሩ ይገደዳሉ። ሕንድ ውስጥ ልጆችን በጉልበት ሥራ ማሠማራት ሕገ ወጥ ቢሆንም፤ 2011 ላይ የተሠራ ጥናት ከ260 ሚሊዮን የሕንድ ልጆች 10 ሚሊዮኑ የጉልበት ሥራ እንደሚሠሩ ያሳያል።
ፓንካጅ ላል የ13 ዓመት ልጃቸውን ለሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ለመስጠት ተገድደዋል። ምንም ገቢ ሳይኖራቸው አምስት ልጆቻቸውን መመገብ አልቻሉም ነበር።
ልጃቸው ከመንደራቸው በ1000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ፋብሪካ ውስጥ እንዲሠራ ልከዋል። በወር 68 ዶላር ይከፈለዋል።
ልጃቸው ፋብሪካ እንዲሠራ መላካቸው ፓንካጅን እጅግ ያሳዝናቸወል።
“ልጆቼ ለሁለት ቀናት አልበሉም። ስለዚህ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪው እንዲወስደው አደረግኩ። ጠንካራ እጅ ያለው ሰው ነው የምንፈልገው ስላሉኝ እኔ መሄድ አልቻልኩም። እና ልጄ ከመላክ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም።”
ትራንስፖርት ላይ ገደብ ቢጣልም ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ልጆችን ከቦታ ቦታ እያንቀሳቀሱ ነው።
ሱርሽ ኩመር የእርዳታ ድርጅት ይመራሉ። ለ25 ዓመታት ታዳጊዎችን ከሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ሲያስጥሉ የነበሩት ሱርሽ ዝውውሩ በእጥፍ መጨመሩን ይናገራሉ።
“ለአዘዋዋሪዎች ያተረፍናቸው ልጆች ከአምና በእጥፍ ጨምሯል። ባለፉት ወራት ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ተጠናክረዋል።”
መንግሥት ሕገ ወጥ የልጆች ዝውውርን በተመለከተ ጥብቅ ሕግ አውጥቷል። የተለያዩ ግዛቶች ስለ ጉዳዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሰጡ፣ ሕጋቸውን እንዲያጠብቁ እንዲሁም በወረርሽኙ ወቅት ለሴቶችና ሕፃናት ማቆያ እንዲያዘጋጁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ከሆነ ግን ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ጉቦ እየሰጡ ከእስር ያመልጣሉ። ቤተሰቦች ጉዳዩን ለፖሊስ እንዳያመለክቱ ማስፈራሪያ ሊደርሳቸውም ይችላል።
ፓንካጅ እድለኛ ሆነው ልጃቸውን ይዞ ይጓዝ የነበረው አውቶብስ ተይዞ ልጃቸው በማቆያ እንዲገባ ተደርጓል። በቅርቡም ከቤተሰቡ ጋር ይቀላቀላል።
“ደካማ ሆኜ ነበር ልጄን የላኩት። ከእንግዲህ በትራፊ ብንኖርም ልጄን ወደ ሥራ አልክም።”

















