ኮሮናቫይረስ፡ መድኃኒት ነው ስለሚባልለት ተክል ምን ያህል እናውቃለን?

የአርቲ ቅጠል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አፍሪካዊቷ አገር ማዳጋስካር ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ አገር በቀል የሆነ ተክልን በመጠቀም ለኮሮረናቫይረስ የሚሆን መድኃኒት ማግኘቷን ካስታወቀች በኋላ የዓለምን ትኩረት መሳብ ችላ ነበር።

አርትሚዝያ የተባለውና ከአርቲ ጋር የሚመሳሰለው ተክልን በመጠቀም የተሰራው የሚጠጣ 'መድኃኒት' በአገሪቱ ፕሬዝዳንት አንድሬይ ራጆሊና ሲሞካሽ ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በዋነኛነት የወባ በሽታን ለማከም ጥቅም ላይ ከሚውለው አርትሚዝያ ተክል የሚሰራው 'መድኃኒት' በትክክል ኮቪድ-19ኝን እንደሚያድን በሳይንሳዊ መንገድ እስካሁን አልተረጋገጠም ሲል ቆይቷል።

ለመሆኑ ስለዚህ ተክል ባህሪዎችና አጠቃላይ ሁኔታ ምን ያክል እናውቃለን?

አርትሚዝያ ከየት መጣ?

አርትሚዝያ ዋናው መገኛው ከወደ እሲያ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን በመላው ዓለም በሚገኙኛ ፀሐያማና ሞቃታማ የአየር ጸባይ ባላቸው አገራት በብዛት ይታያል። በዋነኛነት ተክሉ ቻይና ውስጥ ላለፉት 2 ሺህ ዓመታት ለባህላዊ መድኃኒትነት ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።

በዚህም እንደ ወባ፣ ትኩሳትና ሌሎች ህመሞችን ለማከም ያገለግል ነበር።

ይህ ተክል በቻይናውያን ዘንድ 'ኪንጋኦ' ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከመድኃኒትነት በተጨማሪ አርትሚዝያ የአልኮል መጠጦችም ውስጥ ይጨመራል።

የማዳጋስካሩ ፕሬዝዳንት ከአርቲ የተሰራውን ጭማቂ ይዘው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የማዳጋስካሩ ፕሬዝዳንት ከአርቲ የተሰራውን ጭማቂ ይዘው

አርትሚዝያ ኮቪድ-19ኝን ያክም ይሆን?

የማዳጋስካሩ ፕሬዝዳንት አንድሬይ ራጆሊና ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ ከአርትሚዝያ የተሰራው የሚጠጣ 'መድኃኒት' ላይ ሙከራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን በመግለጽ 'መድኃኒቱ' ኮቪድ-19ኝን ለማከም መዋል እንደሚችል ደርሰንበታል ብለዋል።

በያዝነው የፈረንጆቹ መስከረም ወርም ቢሆን ይህንኑ አስተያየታቸውን ደግመውታል። ነገር ግን በይፋ ሊታይ የሚችል ማረጋገጫ እስካሁን ድረስ ማዳጋስካር ማቅረብ አልቻለችም።

በተጨማሪም 'መድኃኒቱን' ለመስራት ምን አይነት ሂደት እንደተከተሉና ተክሉ ምን ያህል ጥቅም ላይ እንደዋለ የተገለጸ ነገር አለመኖሩ በርካቶች ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

ማዳጋስካር ግን እነዚህን ሁሉ አስተያየቶች ወደጎን በማለት እንደውም ይህንኑ ተክል በመጠቀም ለኮቪድ-19 የሚሆን የሚዋጥ መድኃኒት ማምረት የጀመረች ሲሆን በመርፌ መልክ የሚሰጥ መድኃኒትም በማዘጋጀት ላይ ናት።

ለእነዚህ 'መድኃኒቶች' ደግሞ ክሊኒካዊ ሙከራዋን አጠናክራ መቀጠሏን ማዳጋስካር አስታውቃለች።

የጀርመን እና የዴንማርክ ተመራማሪዎች ደግሞ አርትሚዝያ ምን ያክል ውጤታማ ሊሆን ይችላል የሚለውን እና እውን ኮቪድ-19ኝን ማከም ይችላል የሚለውን ለማረጋገጥ ጥናት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

አዲስ በሰሩት ጥናትም ተክሉ ኮቪድ-19ኝን የማዳከም አቅም እንዳለው ላቦራቶሪ ውስጥ ማረጋገጥ እንደቻሉ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን የተመራማሪዎቹ ጥናት በገለልተኛ ባለሙያዎች ባይገመገምም ከተክሉ የተወሰደው ቅንጣት የቫይረሱን እንቅስቃሴ መግታትና ማቀዝቀዝና ኃይለኛቱን መቀነስ እንደሚችል ተገልጿል።

ተመራማሪዎቹ በአሜሪካው ኬንተኪ ዩኒቨርሲቲ ስር ሆነው የሚሰሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ክሊኒካዊ ሙከራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።

ቻይናም ብትሆን በዚሁ ተክል ላይ ምርምሮችን ማድረግ እንደጀመረች አስታውቃለች። በባህላዊ መንገድ ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ተክል በዘመናዊ ምርምርና እውቅት በመደገፍ የሚደረገው ለኮሮናቫይረስ ፍቱን መድኃኒት የማግኘት ሥራም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ተመራማሪዎችም ቢሆኑ አርትሚዝያ ኮቪድ-19ኝን ምን ያክል ማከም ይችላል የሚለውን ማወቅ በማሰብ በላብራቶሪ ምርምር ማድረግ ከጀመረች ሰነባብታለች።

የዓለም ጤና ድርጅት ግን አሁንም ቢሆን ከአርትሚዝያ ስለተሰራው 'መድኃኒት' ከማደዳስካር የተብራራ መረጃ አላገኘሁም እያለ ነው።

የድርጅቱ የአፍሪካ አማካሪ ዢን ባፕቲስት ኒኬማ ለቢቢሲ እንደገለጹት ድርጅቱ በሚያገኘው መረጃ ላይ በመመስረት ክሊኒካል ሙከራዎች ላይ መሳተፍ እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

አሁን ግን የዓለም ጤና ድርጅት አርትሚዝያ ኮቪድ-19ኝን ስለማከሙ ማረጋገጫ የሚሆን መረጃ እንዳለገኘ ገልጿል።

ኮሮና
Banner