ታሊባን እና የአፍጋን መንግሥት ለሰላም ድርድር ኳታር ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለወራት ዘግይቶ የቆየው በአፍጋኒስታን መንግሥት እና በታሊባን መካከል የሚደረገው የሰላም ድርድር በባህረ ሰላጤዋ አገር ኳታር ዛሬ ይጀመራል።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ ደግሞ የሰላም ድርድሩ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ለመታደም ወደ ዶሃ ጎዞ ጀምረዋል። ፖምፔዮ የሰላም ድርድሩን “ታሪካዊ” ሲሉ ጠርተውታል።
አሜሪካ ከወራት በፊት ከታሊባን ጋር የደህንነት ስምምነት ከደረሰች በኋላ ነው በአፍጋን መንግሥት እና በታሊባን መካከል የሰላም ድርድር እንደሚካሄድ የተገለጸው።
የአፍንጋኒስታን መንግሥትን የሚወክለው ልዑክ ትናንት ምሽት ወደ ዶሃ ያቀና ሲሆን የልዑኩ መሪ አብዱላህ አብዱል “ሰላምን ለማግኘት ነው የምንጓዘው” ብለዋል።
ከአፍጋኒስታን መንግሥት ልዑክ ጋር የሴቶችን መብት እና ፍላጎት መከበሩን የሚያረጋግጡ ስድስት ሴቶች ወደ ዶሃ መጓዛቸው ተነገሯል። ታሊባን በበኩሉ ከትናንት በስቲያ ስድስት እሰረኞች መለቀቃቸውን እንዳረጋገጥን በሰላም ድርድሩ ላይ እንሳተፋለን ብሏል።
እነዚህ ስድስት የታሊባን እስረኞች እንዳይለቀቁ ፈረንሳይ እና አውስትራሊያ ጥያቄ አቅርበዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው እኚህ የታሊባን እስረኞች በዜጎቻቸው ግድያ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው በሚል ነው።
ይህ በታሊባን እና በአፍንጋኒስታን መንግሥት መካከል የሚደረግ የመጀመሪያ የፊት ለፊት ውይይት እንደሆነ ይታመናል። ታሊባኖች የአፍጋን መንግሥት “ደካማ” እና “የአሜሪካ አሻንጉሊት ነው” በሚል ለድርድር ለመቀመጥ ፍላጎት ሳያሳዩ ቆይተዋል።
እአአ 1979 የሶቪየት ወረራን ተከትሎ የተጀመረውን ግጭት ለማስቆም ሁለቱም ወገን ተስፋ ሰንቀዋል። ይህ ውይይት ለወራት ዘግይቶ ነው የሚካሄደው። ለዚህ ደግሞ ምንክያቱ አሜሪካ እና ታሊባን ከወራት በፊት በደረሱት የሰላም ስምምነት ላይ የእሰረኞች ልውውጥ እንዲካሄድ የደረሱት ስምምነት እስካሁን ተፈጻሚ ሳይሆን በመቅረቱ ነው።
በዛ ስምምነት መሰረት ታሊባን ይዞ የሚገኘውን 1 ሺህ የአፍጋኒስታን ወታደሮችን ለመፍታት የተስማማ ሲሆን የአፍጋኒስታን መንግሥት ደግሞ 5 ሺህ የታሊባን ወታደሮችን እንደሚፈታ አሜሪካ ማረጋገጫ ሰጥታለች።
በአሜሪካ እና ታሊባን ስምምነት ላይ አሜሪካ እና የሰሜን አትላንቲክ የቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አጋሮች ሁሉንም ወታደሮቻቸውን በ14 ወራት ውስጥ ለማስወጣት ተስማምተዋል።
አሜሪካ ጨምራ በታሊባን ላይ ጥላ የሚገኘውን ማዕቀብ ታነሳለች። የተባበሩት መንግሥታትም በታሊባን ላይ ጥሎት የሚገኘው ማዕቀብ እንዲነሳ አሜሪካ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር አብራ ለመስራት ተስማምታለች።
በምላሹ ደግሞ ታሊባን በሚቆጣጠራቸው አከባቢዎች አል-ቃኢዳ ወይም የትኛው ጽንፈኛ ቡድን እንዲንቀሳቀስ አይፈቅድም።













