ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ጀርመንን ያጭበረበሩ ሁለት ናይጄሪያውያን በቁጥጥር ስር ዋሉ
ሁለት ናይጄሪያውያን የጀርመን ባለስልጣናትን 2. 8 ሚሊየን ዶላር በማጭበርበር በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ግለሰቦቹ ጀርመን ያዘዘችውን የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁስ አቅርቦትን ለማቅረብ በሚል በኢንተርኔት በፈፀሙት ወንጀል መጠርጠራቸውን ፖሊስ ገለጿል።
ሁለቱ ናይጄሪያውያን በሆላንድ የሚገኝ ኩባንያን ድረ ገጽ፣ አይ ኤልቢኤን ሆልዲንግስ ቢቪ (ILBN Holdings BV) አስመስለው በመስራት የሰሜን ጀርመን ተወካይን አጭበርብረዋል ተብሏል።
ተጠርጠሪዎቹ ስማቸው ባባቱንዴ አዴሳንያ፣ በቅጽል ስሙ ቴዲ እንዲሁም አከንፔሉ ሃሰን አባስ መሆኑን ፖሊስ የለየ ሲሆን እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አልቀረቡም።
የሰሜን ጀርመን አስተዳዳሪው ቮን ሃሃና 2.3 ሚሊዮን ዮሮ ድርጅቱ የኮቪድ-19 መከላከያ እንደያቀርብላቸው በመስማማት የከፈሉ ሲሆን በስምምነታቸው መሰረት ቁሳቁሶቹ ባለመድረሳቸው ወደ ድርጅቱ ዋና ቢሮ አምርተዋል።
ድርጅቱ ከግለሰቡ ጋር ምንም ዓይነት የንግድ ውል እንዳላደረገ በመግለጽ የተፈጠረው ጉዳይ ሲመረመር፤ ተመሳስሎ በተሰራ ድረገጽ መጭበርበራቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
የሆላንድ ፖሊስ ሁለቱን ተጠርጣሪዎች በአገሩ ውስጥ በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፤ ምርመራው ወደ ናይጄሪያ አምርቶ ሌሎች ተጫሪ ሰዎች በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል።
የናይጄሪያ ፖሊስ እንደገለፀው ግለሰቦቹ "ውስብስብ የገንዘብ ዝውውር ማጭበርበር ውስጥ በመሳተፍ" ተጠርጥረዋል።
ግለሰቦቹም በቅርቡ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ሲል ፖሊስ በተጨማሪ አስታውቋል።