2012፡ የኢህአዴግ መክሰም፣ የተማሪዎች እገታ፣ የምርጫ መራዘም፣ ግድያና እስር

በ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያውያንን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማኅበራዊ ሕይወት በበጎም ሆነ በአሉታዊ ሁኔታ የሚነኩ ነገሮች ተከስተዋል።

ከእነዚህ ክስተቶች የትኞቹ ጉልህና ወሳኝ ናቸው የሚለውን ለመለየት እንደምንጠቀምበት መመዘኛ የተለያየ ቢሆንም፣ ቢቢሲ በተለይ በለውጥ ሂደት ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው አንድምታ ከፍ ያለ ነው ያላቸውን ጥቂት ክስተቶችን መርጦ ቃኝቷል።

ኢህአዴግ መክሰምና ብልጽግና ውልደት

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አገሪቱን ሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በብቸኝነት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ህልውና የመራውና መሠረታዊ ለውጥ በማምጣት ረገድ የአራት የብሔር ድርጅቶች ግንባር የሆነው ኢህአዴግን ያህል የሚጠቀስ ቡድን የለም።

ነገር ግን ከሦስት ዓመት በፊት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሰበት ተቃውሞ ግንባሩ ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል ስላላስቻለው የለውጥ እርምጃዎችን ወስዶ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰይሞ፤ በ27 ዓመታት ሂደት ውስጥ የቆየበትን ገጽታውን ለመቀየር ሥራውን የጀመረው በዚህ ዓመት ነበር።

ግንባሩ ለዓመታት ሲንከባለል የነበረው አንድ ውህድ ፓርቲ የመሆን እቅዱን በፍጥነት ለማከናወን ወስኖ ከህወሓት ውጪ ያሉት ኦዲፒ፣ አዴፓ እና ደኢህዴን ስምምነት ላይ ደርሰው "ብልጽግና" የተሰኘውን አንድ ወጥ ፓርቲ መሰረቱ። ሂደቱም ከዚህ በፊት የኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎች የሚባሉትን ክልላዊ ፓርቲዎችን አንድ በአንድ በማካተት አገራዊ ቅርጽ ያዘ።

የኢህአዴግ መስራችና በግንባሩ ውስጥ ጉልህ ሚና የነበረው ህወሓት በአዲሱ ውህድ ፓርቲ ውስጥ ላለመሳተፍ ከወሰነ በኋላ በማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ የነበረው ተሳትፎ ቀስ በቀስ እየተዳከመ ከብልጽግና ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ፍጥጫ ውስጥ ገባ።

በዚህም ሳቢያ ህወሓት በገዢ ፓርቲነት በሚያስተዳድረው ትግራይ ውስጥ እንቅስቃሴውን በማጠናከር የብልጽግና ፓርቲ ተቀናቃኝ ሆነ። በቀሪው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችንም በማስተባበር "የፌደራሊስት ኃይሎች" የተሰኘ ስብስብን ፈጥሮ በሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲ በተቃራኒ ቆመ።

በዚህም በብልጽግናና በህወሓት መካከል በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ያለው አለመግባባት እየሰፋ መጥቶ፣ በግልጽ አስከ መወነጃጀል የደረሰ ሲሆን፤ ይኸው ፍጥጫ ተካሮ ትግራይ ክልል በተናጠል ምርጫ ለማካሄድ እስከመወሰን ደርሷል።

የጃዋር መከበብ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የተከፈተባቸው ክስና የተጣለባቸው እገዳ ተነስቶ ወደ አገር ቤት ከገቡ የፖለቲካ ቡድኖች መሪዎችና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ጃዋር መሐመድ በቤቱ አካካቢ ለደኅንነቱ ስጋት ነው ያለውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የፈጠረው አለመጋጋት ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኖ ነበር።

ጥቅምት 11/2012 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ገደማ መሃል አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ አካባቢው የጸጥታ ኃይሎች ያልተለመደ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሶ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት፣ ደጋፊዎቹ በቤቱ ዙሪያ ከመሰባሰባቸው ባሻገር በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

አለመረጋጋቱን ተከትሎም በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ80 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወት ሲጠፋ በንብረትም ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሶ ውጥረቱም ለቀናት ዘልቆ ነበር።

ሲዳማና ክልልነት ጥያቄ በደቡብ

ለዓመታት የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማዕከል ከሆነው የደቡብ ክልል በመውጣት ራሱን የቻለ ክልል ለመመስረት ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረው የሲዳማ ዞን፣ ቀደም ሲል ካጋጠመ ውዝግብ እንዲሁም ደም ካፋሰሰ ግጭትና ጥቃት በኋላ ኅዳር 10/2012 ዓ.ም በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ መቋጫ አግኝቷል።

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በመራው በሲዳማ ዞን ውስጥ በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ድምጻቸውን ከሰጡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች፤ ማለትም 98.51 በመቶው፤ ዞኑ ክልል እንዲሆን የሚያስችለውን ድምጽ መስጠታቸውን ይፋ ሆኖ ሲዳማ 10ኛው የአገሪቱ ክልል መሆን ችሏል።

ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች በተለየ ከ50 በላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የያዘው የደቡብ ክልል ለሲዳማ ጥያቄ ምላሽ ቢሰጥም ከአስር የማያንሱ ሌሎች ዞኖችም የክልልነት ጥያቄ አቅርበዋል።

በተለይ የሲዳማ ክልልነት በይፋ ከደቡብ ክልል መውጣቱ ሰኔ ወር ላይ ከተገለጸ በኋላ፣ የክልልነት ጥያቄ ያቀረቡት ዞኖች ውስጥ እንቅስቃሴዎች በጉልህ ከመታየታቸው ባሻገር አንዳንዶች መለያችን ነው የሚሉትን ባንዲራ የሚያሳዩ ምስሎችን በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በስፋት ሲያሰራጩ ነበር።

ዓመቱ በተለይ የወላይታ ዞን ተወካዮቹ ከደቡብ ምክር ቤት መውጣታቸውንና ዞኑ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጠው ግፊት ማድረጉን አጠናክሮ በመቀጠሉ ውጥረት ተከስቶ ነበር።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአካባቢው አመራሮች ሌሎችም በስብሰባ ላይ እንዳሉ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር በመዋላቸው አለመረጋጋት ተቀስቅሶ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተዘግቧል።

የተማሪዎች እገታ

በ2012 ዓ.ም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተከሰቱ ግጭቶች ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዚህ ሳቢያ በተፈጠረው ስጋት በዩኒቨርስቲዎቹ ይካሄድ የነበረው ትምህርት በተደጋጋሚ ተስተጓጉሏል።

በዓመቱ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖ ብዙ የተባለለትና እስካሁንም መቋጫ ያላገኘው የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እገታ ጉዳይ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።

በዩኒቨርስቲው ባጋጠመ የጸጥታ መደፍረስ ሳቢያ ትምህርት በማቋረጡ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ የነበሩ 18 የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መታገታቸው ከተነገረና በኋላ ለወራት የት እንደደረሱ ሳይታወቅ እስካሁን ደብዛቸው እንደጠፋ ይገኛሉ።

የተማሪዎቹ ወላጆች ከራሳቸው ከልጆቻቸው ተደውሎላቸው ችግር እንደገጠማቸው የሰሙት ኅዳር 24/2012 ዓ.ም ቢሆንም ክስተቱ ተገቢውን ትኩረት ለማግኘት ሳምንታትን ወስዷል።

ቢቢሲ ስለተማሪዎቹ እገታ የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብ ዘገባዎችን የሰራ ቢሆንም ከክልልና ከፌደራል የመንግሥት አካላት መረጃ ለማግኝት ሳይችል ቆይቷል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚወጡት መረጃዎችም አንዳንዶቹ ዕገታው እንዳልተፈጸመ ሲያስተባብሉ ሌሎቹ ደግሞ እርስ በርስ የሚጣረሱ ሆነው ቆይተዋል።

በመጨረሻም መንግሥት የተማሪዎቹን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን በመጥቀስ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቋጫ እንደሚያገኝ ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ከወራት በኋላ ከተማሪዎቹ እገታ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ የተባሉ አስራ ሰባት ሰዎች ላይ ሐምሌ 10/2012 ዓ.ም የሽብር ወንጀል ክስ እንደተመሰረተባቸው ብሔራዊው ቴሌቪዥን ዘግቧል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፤ በዚህም ያሉበት ያልታወቁና አብዛኞቹ ሴት ተማሪዎችን በማገት፣ በመጥለፍና በሽብር ወንጀል ተከስሰዋል።

በክሱ ላይ ተማሪዎቹ በተጠርጣሪዎቹ አማካይነት በምዕራብ ኢትዮጵያ ይንቀሳቀሳል ለሚባለው አማጺ የኦነግ-ሸኔ ቡድን ተላልፈው እንደተሰጡ ቢጠቀስም እስካሁን ግን የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አይታወቅም።

ምርጫ መራዘም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ምርጫ ቦርድን ነጻና ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ እንዲዋቀር በማድረግ በ2012 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ምርጫ ከዚህ በፊት ከተካሄዱት ሁሉ የተለየ እንዲሆን እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ተናግረው ነበር።

በዚህም መሠረት የቀድሞዋ ፖለቲከኛ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ኃላፊነቱን ይዘው ቦርዱ የሚተዳደርባቸው የሕግና የመዋቅር መሻሻያዎች ተደርገው፤ ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሚካሄድበት የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶ፣ በመጀመሪያ ነሐሴ 10 ከዚያም ማሻሻያ ተደርጎ ነሐሴ 23/ 2012 ዓ.ም የድምጽ መስጫ ቀን እንዲሆን ቀን ተቆርጦ ነበር።

የኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱን ተከትሎ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን ማካሄድ የማይችል መሆኑን በመግለጽ ለምርጫው መከናወን ያለባቸው ሥራዎች ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑን መጋቢት 22/2012 አስታወቀ።

በዚህም መሠረት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ተወግዶ የሚኖረውን ተጨባጭ ሁኔታ እንደገና ገምግሞ አዲስ የምርጫ ሥራ ዝግጅት ዕቅድና የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴውን እንደሚያስጀምር አሳውቋል።፡

ይህንንም በማስመለከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ጠቅሶ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቨማቅረብ፣ ምክር ቤቱ የቦርዱን የውሳኔ ሐሳብ በመቀበል በጉዳዩ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲካሄድ መጠየቁ ይታወሳል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በወረርሽኙ ምክንያት ምርጫ በወቅቱ ማካሄድ ባለመቻሉ እንዲሁም የምክር ቤቶችንና የአስፈፃሚ አካላትን የሥራ ዘመን አስመልክቶ በቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም መሰረት የበሽታው ስጋት እስካለ ድረስ የፌደራልና ክልል ምክር ቤቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ወሰነ።

ምርጫውም ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት ወረርሽኙን አስመልክተው የሚያወጡትን መረጃ መሰረት በማድረግ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም በሽታው የሕዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ምርጫው እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ ተወሰነ።

ከዚህ በተቃራኒ ግን በምንም ምክንያት ምርጫው ሊራዘም አይገባም ያለው የትግራይ ክልል ግን በዚህ ዓመት በተናጠል ምርጫ ለማካሄድ ሲዘጋጅ ቆይቶ ረቡዕ ጳጉሜ 04 መራጮች ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ምርጫው ሕግን የጣሰ በመሆኑ ተቀባይነት ስለሌለው እንዳልተካሄደ ይቆጠራል ሲል ለምርጫው እውቅና እንደማይሰጥ ገልጿል።

እንደተባለው ምርጫው በትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄድ ከሆነ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚኖረው ግንኙነትን የበለጠ ስለሚያበላሸው ውዝግቡ ወደ 2013 መሸጋገሩ አይቀርም።

የሃጫሉ መገደልና እስር

ዓመቱ ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት ሲቀሩት የተፈጸመው የታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ካመጡት ክስተቶች መካከል ቀዳሚው ነው። አንዳንዶች የሃጫሉ ግድያና እሱን ተከትሎ የተከሰተው ውጥረትና አለመረጋጋት ውጤቱ ለወራት ሊቆይ እንደሚችል ይገምታሉ።

ሰኞ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም ምሽት የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እንደተሰማ ወዲያው ነበር በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሁከትና ተቃውሞ የተቀሰቀሰው። ከድምጻዊው ግድያ በተጨማሪ የአስከሬን ሽኝትና ቀብሩ የሚፈጸምበት ቦታ ያስከተለው ውዝግብ የተፈጠረውን ውጥረት በከፍተኛ ሁኔታ አጡዞታል።

በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ሰበብነት በተለያዩ ስፍራዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ150 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። በአንዳንድ ከተሞች ላይ ደግሞ ሆቴሎች፣ የንግድ ተቋማት፣ የመንግሥት ቢሮዎች፣ የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶችና ሌሎችም በተፈጸመባቸው ጥቃት ወድመዋል።

ከሰኔ 23 2012 ከሰዓት በኋላ ጀምሮም በርካታ ፖለቲከኞችና በሺህዎች የሚቆጠሩ በሁከቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋል ጀመሩ።

በዚህም መሠረት ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋ እና ሌሎችም ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፤ ሁከቱን በማባባስ በኩል አስተዋጽኦ አድርገዋል የተባሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በጸጥታ ኃይሎች እንደተዘጉ የተነገረ ሲሆን ጋዜጠኞችም ከታሰሩት መካከል ይገኙባቸዋል።

የሃጫሉ መገደልን ተከትሎ የተፈጠሩት ነገሮች አገሪቱ የጀመረችውን ነገሮች ወደኋላ ሊመልሱት ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች የተበራከቱ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞና አለመረጋጋት እየተከሰተ ነው።

የቀናት ዕድሜ በቀረው በዚህ ዓመት በርካታ ጉልህ ነገሮች በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰታቸው ይታወቃል። ነገር ግን በቢቢሲ ምርጫ ከብዙ በጥቂቱ በ2012 ዓ.ም ከተከሰቱት ዋነኛ ናቸው ያልናቸውን እነዚህን መለስ ብለን ቃኝተናል።

እናንተስ በዓመቱ ከተከሰቱት ውስጥ የትኞቹን በጉልህነት ትመለከቷቸዋላችሁ?